ፈልግ

ር. ል. ጳ. ፍራንችስኮስ በጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ላይ ር. ል. ጳ. ፍራንችስኮስ በጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ላይ   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ጦርነት ለሚካሄድባቸው ቦታዎች ሰላም መጸለይ እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ረቡዕ ኅዳር 5/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ሳምንታዊ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ባቀረቡበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ምእመናን በጦርነት ውስጥ የሚገኙ አገራትን በሙሉ ዘወትር በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለታዳሚዎች ባቀርቡት ሳምንታዊው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማጠቃለያ ላይ ዘወትር እንደሚናገሩት፥ ሃሳባቸውን በጦርነት አሰቃቂ መከራ ውስጥ ወደሚገኙ አገራት በማዞር፥ በጦርነት ውስጥ ለሚገኙ አገራት በሙሉ በየቀኑ የሰላም ጸሎት እንዲቀርብ ጠይቀዋል።

መከራ ውስጥ የምትገኝ ዩክሬን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ረቡዕ ኅዳር 5/2016 ዓ. ም. ባስተላለፉት መልዕክት፥ በተለይም በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ለምትገኝ ዩክሬን ጸሎት እንዲደረግላት ጠይቀዋል። ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረችበት ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከካቲት 2022 ዓ. ም. ወዲህ ከ9,600 በላይ ሰዎች መገደላቸው እና ከ17,500 በላይ ሰዎች መቁሰላቸው ታውቋል።

ሰላም በቅድስት ሀገር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተጨማሪም በፍልስጤም እና በእስራኤል መካከል በመካሄድ ላይ ያለውን ጦርነት በማስታወስ በቅድስት አገር ሰላም እንዲወርድ ጸሎት ማድረግ እንደሚገባ አደራ ብለዋል። የሃማስ ታጣቂዎች መሰከረም 26/2016 ዓ. ም. በፈጸሙት ጥቃት 1,200 እስራኤላውያን መገደላቸው ይታወሳል።ከዚያን ጊዜ በኋላ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ከ11,000 በላይ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ 2,500 ያህሉ ደግሞ መጥፋታቸው ይነገራል።

ሱዳን ፈጽሞ መረሳት የለባትም

ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው መጨረሻ ሱዳንን በማስታወስ በሁለቱ ተቀናቃኝ ወታደራዊ ቡድኖች መካከል ሚያዝያ ወር ላይ በተቀሰቀሰው አስከፊ ጦርነት በ9,000 የሚገመቱ ሰዎች ሲገደሉ በ 5.6 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች ደግሞ ቀያቸውን ጥለው መሰደዳቸው ታውቋል። የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት "ሰብዓዊ ጥፋት" ተብሎ የተገለጸ ሲሆን፥ በስውር የዘር ጭፍጨፋ እየተካሄደ መሆኑን የሚገልጹ ምልክቶች እየታዩ ነው ተብሏል።

“ጦርነት የሚካሄድባቸው ቦታዎች የትም ይሁኑ በጸሎት እናስብ” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት፥ “በሚያሳዝን ሁኔታ በዓለማችን ውስጥ በርካታ ጦርነቶች እየተካሄዱ ናቸው!” ብለው፥ ምእመናኑ በየቀኑ ጊዜን በመስጠት ለሰላም መጸለይ እንደሚገባ በማሳሰብ እና “ሰላም ያስፈልገናል” በማለት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

 

 

 

 

15 November 2023, 16:51