ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የፓራጓይ ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ሳንቲያጎ ፔኛ ፓላሲዮስን በቫቲካን ሲቀበሏቸው ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የፓራጓይ ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ሳንቲያጎ ፔኛ ፓላሲዮስን በቫቲካን ሲቀበሏቸው  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የፓራጓይ ፕሬዝዳንት በቫቲካን ተቀብለው አነጋግረዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ኅዳር 17/2016 ዓ. ም. ጠዋት የፓራጓይ ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ሳንቲያጎ ፔኛ ፓላሲዮስን በቫቲካን ተቀብለው ተወያይተዋል። ክቡር አቶ ሳንቲያጎ ፔኛ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር 25 ደቂቃ ከወሰደው ውይይታቸው በተጨማሪ፥ በቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ባደረጉት ጉብኝትም የጋራ ግንኙነቶችን ማጠናከር፥ አዲሱ የፓራጓይ መንግሥት ድህነትን ለመዋጋት በሚያደርጋቸው ጥረቶች፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በአገሮች መካከል ሰላምን ማስፈን የሚሉ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። ርዕሠ መስተዳድሩ በአገር ውስጥ የተሠሩ ቅርጻ ቅርጾች እና የተለመዱ ባሕላዊ ምርቶችን ጨምሮ በርካታ ስጦታዎች ለር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ አበርክተውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከፓራጓይ ፕሬዝደንት ከክቡር አቶ ሳንቲያጎ ፔኛ ፓላሲዮስን ጋር ሰኞ ኅዳር 17/2016 ዓ. ም. ጠዋት በቅድስት ማርታ የጳጳሳት መኖሪያ ውስጥ ለ25 ደቂቃ ያህል መወያየታቸውን የቅድስት መንበር ቃል አቀባይ አቶ ማቴዮ ብሩኒ ተናግረዋል። በአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ቀዳዊት እመቤትን ጨምሮ አሥራ ሦስት የልኡካን ቡድን አባላት መገኘታቸው ታውቋል።

በቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት የተደረግ ውይይት

የፓራጓይ ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ሳንቲያጎ ፔኛ ፓላሲዮስን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ካደረጉት ውይይት ቀጥለው በሐዋርያዊ ሕንጻ ውስጥ ከቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ከሆኑት ከብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ጋር እና በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዋና ጸሐፊ ከሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ጋር መወያየታቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

ሁለቱ ወገኖች ቅን ውይይቶችን ማካሄዳቸውን የገለጸው መግለጫው፥ በቅድስት መንበር እና በፓራጓይ ሪፐብሊክ መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እና እስካሁን በነበራቸው ግንኙነትም መርካታቸውን አስታውቋል።

በአዲሱ የፓራጓይ መንግሥት ዕቅድ ላይ ያተኮረው ውይይቱ፥ የፓራጓይ መንግሥት ድኅነትን ለመዋጋት ባለው ቁርጠኝነት እና በተጨማሪም በአንዳንድ የጋራ ጉዳዮች ማለትም የአካባቢ ጥበቃ፣ የአገራት ግንኙነት እና በመካከላቸው ሰላምን ማስፈን በሚሉ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን መግለጫው አክሎ አስታውቋል።

የስጦታ ልውውጥ

የፓራጓይ ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ሳንቲያጎ ፔኛ ፓላሲዮስን ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በርካታ ስጦታዎችን ያበረከቱላቸው ሲሆን፥ በመጀመሪያ ደረጃ በፓራጓይ የእጅ ሞያተኞች የተሠራ አገር በቀል የብርሃነ ልደቱን ትዕይንት የሚያሳይ ቅርጻ ቅርጽ፣ የአገሩ ባሕላዊ ልብስ፣ የተለመዱ የምግብ ምርቶች፣ ከእንጨት የተሠራ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስል እና ከብር የተሠራ መቁጠሪያ በስጦታ መልክ አበርከተውላቸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ለክቡር ፕሬዝደንት አቶ ሳንቲያጎ ፔኛ ፓላሲዮስን ባበረከቱት ስጦታ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ አምዶች ሥር የሚገኝ እና ልጇን የተሸከመች እናት ስደተኞችን ከያዘ መርከብ ጎን ቆማ የሚያሳይ እና ከሥሩም "እጆችን በሌላ እጆች እንሙላ" የሚል ጽሑፍ የተጻፈበትን እና ሁለት እጆች ሲጨባበጡ የሚያሳይ ከነሐስ የተሠራ ቅርጽ አበርክተዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም በተጨማሪ ለዘንድሮው የዓለም የሰላም ቀን ያስተላለፉትን መልዕክት የያዘ ሠነድ እና ሌሎች ሠነዶችንም ለፓራጓይ ፕሬዝደንት ለክቡር አቶ ሳንቲያጎ ፔኛ ፓላሲዮስን በስጦታ አበርክተውላቸዋል።

 

28 November 2023, 16:36