ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጳጳሳት መኖሪያ ቤታቸው የእሑዱን ሳምንታዊ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ሲመሩ  ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጳጳሳት መኖሪያ ቤታቸው የእሑዱን ሳምንታዊ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ሲመሩ   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጉንፋን ሕመም በማገገም ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ

የሳንባ ምች ሊሆን ይችላል በሚል ግምት ቅዳሜ ኅዳር 15/2016 ዓ. ም. የሕክምና ዕርዳታ የተደረገላቸው ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በጉንፋን ሕመም ምክንያት የመተንፈስ ችግር አጋጥሟቸው እንደ ነበር የቫቲካን መግለጫ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው አሁን የሚገኙበት የጤና ሁኔታ ጥሩ እና ቋሚ እንደሆነ አቶ ማቴዮ ብሩኒ ገልጸው፥ የተደረገላቸው የሕክምና ዕርዳታ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን የፀረ ባክቴሪያ መድኃኒት በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትኩሳት የለባቸውም፣ የአተነፋፈስ ሁኔታም መሻሻልን አሳይቷል” ያሉት የቫቲካን መግለጫ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ማትዮ ብሩኒ፣ የቅዱስነታቸውን ወቅታዊ የጤና ሁኔታን በማስመልከት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፥ ቅዱስነታቸው እሑድ ኅዳር 16/2016 ዓ. ም. ማለዳ ከቅድስት ማርታ የጳጳሳት መኖሪያ ውስጥ ሆነው በመሩት ሳምንታዊ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ወቅት እንደተናገሩት፥ “በጉንፋን ምክንያት ያጋጠመኝ የሳንባ ማበጥ ነው” ማለታቸውን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዳሜ ኅዳር 15/2016 ዓ. ም. ረፋዱ ላይ በሮም በሚገኝ “ኢሶላ ቲቤሪና” ሆስፒታል ገብተው ያደረጉት የምርመራ ውጤት፥ “የሳንባ ምች ሳይሆን በጉንፋን ምክንያት የመተንፈስ ችግርን ያስከተለው የሳንባ ማበጥ ነው” በማለት አቶ ማቴዎ ብሩኒ አረጋግጠዋል። ከሆስፒታሉ ያገኙት የሕክምና ዕርዳታ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን፥ የፀረ ባክቴሪያ መድኃኒት በመርፌ እንዲሰጣቸው ተደርጓል” ሲሉ የቅድስት መንበር ቃል አቀባይ አቶ ማቴዮ ብሩኒ ተናግረዋል።

አቶ ማቴዮ ብሩኒ በመጨረሻም፥ የቅዱስነታቸውን የማገገሚያ ጊዜ ለማመቻቸት ለእነዚህ ቀናት የታቀዱ አንዳንድ ሐዋርያዊ ተግባራት ለሌላ ጊዜ መተላለፋቸውን ገልጸው፥ ይህም ጉልበት እንዲሰጣቸው እና ሌሎች ተቋማዊ ተግባራት አሁን ካለው የጤና ሁኔታ አኳያ ቀላል በመሆናቸው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

እንደተጠቀሰው ሁሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ረፋዱ ላይ ሳምንታዊውን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከቅድስት ማርታ የጳጳሳት መኖሪያቸው ውስጥ ሆነው በቪዲዮ ምስል አማካይነት መርተዋል። በዚህ የበልግ ወቅት መገባደጃ ሮም ላይ ያለው የሙቀት መጠን ያለፈው ቅዳሜ እና እሁድ በከፍተኛ መጠን መቀነሱ ታይቷል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁዱ ኅዳር 16/2016 ዓ. ም. የመሩትን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት 12 ሺህ ምዕመናን ጋር እንዳቀረቡ እና በርካቶችም ከቤታቸው ሆነው መከታተላቸውን ከምስጋና ጋር ገልጸው፥ በሮም በተከሰተው ከባድ ብርድ ምክንያት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ሆነው ለሚጠባበቋቸው ምዕመናን ከፍታ ካለው ፎቅ በመስኮት በኩል ያልታዩ መሆናቸውን ገልጸው፥ ነገር ግን ለዕለቱ ያዘጋጁትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በንባብ ያቀርቡላቸውን የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ብራይዳን አመስግነዋል።

 

 

27 November 2023, 16:57