ፈልግ

የእስራኤል የአየር ጥቃትን ተከትሎ በማጋዚ የስደተኞች ካምፕ በሕይወት የተረፈ ሰው ፍለጋ ሥራ የእስራኤል የአየር ጥቃትን ተከትሎ በማጋዚ የስደተኞች ካምፕ በሕይወት የተረፈ ሰው ፍለጋ ሥራ  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በቅድስት አገር ተኩስ እንዲቆም እና ታጋቾች እንዲፈቱ በማለት ጥሪ አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በእስራኤል ጦር ሠራዊት እና በሐማስ ታጣቂዎች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ በማለት ከዚህ በፊት ያቀረቡትን ጥሪ በማደስ፥ ዩክሬንን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በጦርነት የሚሰቃዩ ሰዎችን በማስታወስ ጸሎት አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከዚህ በፊት በእስራኤል ጦር ሠራዊት እና በሐማስ ታጣቂዎች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ያቀረቡትን ጥሪ በማደስ እሑድ ጥቅምት 25/2016 ዓ. ም. በሁለቱ ወገኖች መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲቆም ተማጽነዋል። “በጦርነት አደጋ ውስጥ የሚገኙ ሕጻናትን እናስታውስ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ዩክሬንን ጨምሮ ግጭቶች ውስጥ የሚገኙ ሌሎች አገሮችንም በማስታወስ፥ የወደፊት ሕይወታቸው በጦርነት እየጠፋ እንደሆነ ገልጸዋል።

“ጦርነትን እንድታቆሙ በእግዚአብሔር ስም እለምናችሁኋለሁ” በማለት የተመጸኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ግጭቱ እንዳይባባስ እና ለቆሰሉት ሰዎች የሕክምና ዕርዳታ እንዲደረግላቸው፥ ሰብዓዊ ቀውስ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ለሚገኝ የጋዛ ሕዝብ ዕርዳታ እንዲደርሰው ለማድረስ መንገዶች እንደሚመቻቹ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር በማያያዝ፥ መስከረም 26/2016 ዓ. ም. በሃማስ ታጣቂዎች ታፍነው የተወሰዱ ከ200 በላይ እስራኤላውያን ታጋቾች እንዲፈቱ ጥሪያቸውን አቅርበው፥ ከእነርሱም መካከል የሚገኙ በርካታ ሕጻናት ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ በማለት ተማጽነዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ጥቅምት 25/2016 በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባሰሙት ንግግር፥ ጦርነቱ እንዲቆም ሁሉም ሰው ድምጹን የሚያሰማበት ድፍረት እንዲኖረው በማሳሰብ፥ "ጦርነት ይብቃ!” ለማለት የሚያስችል ጥንካሬ እንዲኖረን እንጸልይ" በማለት ጥሪያቸውን አጠናቀዋል።

ጋዛ ውስጥ ያለው ሁኔታ

እስራኤል በሰሜናዊው የጋዛ ክልል የሚኖረው ሕዝብ ወደ ደቡብ እንዲሄድ በማሳሰብ፥ በመላው ጋዛ ውስጥ በሚገኙ የሃማስ ታጣቂዎች ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ መቀጠሏ ተነግሯል። ጋዛ ውስጥ ከሆስፒታል ውጭ ሲጓዝ በነበረ አምቡላንስ ላይ በተከፈተው ጥቃት 15 ሰዎች መገደላቸውን የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማኅበር አስታውቋል። እንደ ዘገባው ከሆነ፥ ሃማስ ይጠቀምበት የነበረውን አምቡላንስ ማጥቃቷን እስራኤል ተናግራለች። የሃማስ ታጣቂዎች እስራኤል ውስጥ ከ1,400 በላይ ሰዎችን ከገደሉ እና ከ200 በላይ ሰዎችን ካገቱ በኋላ እስራኤል ጋዛን በቦምብ ማጥቃት መጀመሯ ይታወሳል።

በሌላ በኩል የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ አንቶኒ ብሊንከን ቅዳሜ ጥቅምት 24/2016 ዓ. ም. በእስራኤል በተያዘች “ዌስት ባንክ” ውስጥ ከፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ጋር መገናኘታቸው ታውቋል። የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ አንቶኒ ብሊንከን ቀደም ብሎ፣ ከሊባኖስ፣ ከኳታር እና ከዮርዳኖስ መሪዎች ጋር አማን ውስጥ ተገናኝተው ባደረጉት ውይይት ሰብዓዊ ዕርዳታን ማድረስ እንዲቻል ጦርነቱ ሊቆም እንደሚገባ መፈለጋቸውን ገልጸዋል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፥ ጋዛ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም የእስራኤል ታጋቾች እስካልተፈቱ ድረስ ከሃማስ ጋር ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደማይኖር ተናግረዋል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ አንቶኒ ብሊንከን ለጋዜጠኞች ባደረጉት ንግግር፥ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ የተገደሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዕርዳታ ሠራተኞችን በማስታወስ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።

06 November 2023, 15:54