ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ ከምዕመናን ጋር ያቀረቡትን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከመኖሪያቸው ሆነው መርተዋል ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ ከምዕመናን ጋር ያቀረቡትን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከመኖሪያቸው ሆነው መርተዋል  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ.ፍራንችስኮስ፥ ወጣቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ደስተኛ ተዋናዮች እንዲሆኑ አበረታቱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እሑድ ኅዳር 16/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር በኅብረት ካቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በመቀጠል ባሰሙት ንግግር፥ “ሆሎዶሞርን” ተብሎ የሚጠራውን የዘር ጭፍጨፋ መታሰቢያ ለታደሙት ዩክሬናውያን ጸልየዋል። ቀጥለውም በእስራኤል እና ፍልስጤም መካከል ስለተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት እግዚአብሔርን አመስግነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የላቲን ሥርዓተ አምልኮን በምትከተል ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ እሑድ ኅዳር 16/2016 ዓ. ም. የተከበረውን የክርስቶስ ንጉሥ በዓል በማስታወስ ባሰሙት ንግግር፥ ወጣቶች በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ደስተኛ ተዋናዮች እንዲሆኑ ብርታትን ተመኝተውላቸውል።

የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በምትመራበት የአምልኮ ቀን አቆጣጠር እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባዘጋጁት አዲሱ መርሃ ግብር መሠረት ዓመታዊው የወጣቶች ቀን በዓለም ዙሪያ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ሀገረ ስብከቶች ዘንድ ከክርስቶስ ንጉሥ በዓል ጋር በአንድነት ይከበራል። በመሆኑም የዘንድሮው የወጣቶች ቀን እሑድ ኅዳር 16/2016 ዓ. ም. ተከብሯል።

ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ ዕለቱን በማስታወስ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ወጣቶች የዓለማችን የአሁኑ እና የወደፊቱ ተስፋዎች ናቸው” ብለው፥ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ደስተኛ ተዋናይ እንዲሆኑ ጋብዘዋል።

“ሆሎዶሞርን” በማስታወስ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1930ዎቹ በሶቪዬት ኅብረት ሥር በምትገኝ ዩክሬን ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በረሃብ ምክንያት ለህልፈት የተዳረጉበትን መታሰቢያ በዓል አስታውሰዋል። በሩስያ እና በዩክሬን መካከል የቀጠለውን ጦርነት አስመልክተው እንደተናገሩትም፥ “ያለፈውን ቁስል ከመፈወስ ይልቅ፥ ጦርነት ውድ በሆነው የሰው ሕይወት ላይ እያደረሰ ያለው አሰቃቂ ድርጊት የበለጠ የሚያሳምም ነው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው፥ “ጸሎት የጥላቻን እና የበቀል አዙሪት የሚሰብር፣ ያልተጠበቁ የዕርቅ ጎዳናዎችን የሚከፍት የሰላም ኃይል በመሆኑ፥ በዓለም ዙሪያ በግጭት ምክንያት ለሚፈናቀሉት እና ለሚበታተኑ ሕዝቦች በሙሉ የሚደረግ ጸሎት እንዲቀጥል በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ስለ ተኩስ አቁሙ ስምምነት እግዚአብሔርን ማመስገን

ቅዱስነታቸው ሃሳባቸው ወደ ቅድስት አገር በማዞር ባደረጉት ንግግር፥ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት በሁለቱም ተፋላሚዎች ዘንድ የሚገኙ እስረኞች ተፈትተው ወደየአገሮቻቸው እንዲመለሱ በመደርጉ እግዚአብሔርን አመስግነዋል።

ሁሉም በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጸሎት እንዲደረግ ጠይቀው፥ ቤተሰቦቻቸውንም በጸሎታችን እንድናስባቸው አሳስበውናል። በተጨማሪ ሰብዓዊ ዕርዳታ ወደ ጋዛ እንዲደርስ ጠይቀው፥ ለውይይት አስፈላጊነት አጽንኦትን በመስጠት፥ “ውይይትን የማይፈልጉ ሰላምን አይፈልጉም!” ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ (COP28) ጉባኤ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችኮስ በመጨረሻም፥ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከተማ በሆነች ዱባይ ውስጥ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የሚካሄደውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (COP28) አስታውሰዋል።

"ዓለማችን ከጦርነት በተጨማሪ በሌላ ታላቅ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ ላይ ትገኛለች፤ ይህም በምድር ላይ ያለውን ሕይወት በተለይም የወደፊቱን ትውልድ አደጋ ላይ ይጥላል" በማለት አስጠንቅቀው፥ የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ሁሉንም ነገር ለሕይወት የፈጠረውን የእግዚአብሔር ዕቅድ የሚጻረር ነው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጭው ዓርብ ኅዳር 21/2016 ዓ. ም. ወደ አረብ ኤሚሬቶች ሲደርሱ፥የተባበሩት መንግሥታት አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን የሚካፈሉ የመጀመሪያው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ይሆናሉ። ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ ይህን ጉዞአቸውን በጸሎት ለሚደግፉት በሙሉ ያላቸውን አድናቆቱን ገልጸው፥ የጋራ መኖሪያ ምድራችን ከጉዳት ለመከላከል እና ለመጠበቅ ልባዊ ቁርጠኝነታቸውን ያሳዩትንበ ሙሉ አመስግነዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በሚገኙ ሀገረ ስብከቶች ለ38ኛ ጊዜ ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን እንዲሆን፥ “በተስፋ ደስ ይበላችሁ!” በሚል ርዕሥ ማክሰኞ ኅዳር 4/2016 ዓ. ም. መልዕክት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። በዚህ መልዕክታቸው፥ ክርስቲያናዊ ተስፋ እግዚአብሔር በመካከላችን መኖሩን እንድናውቅ የሚያደርገን እንደሆነ ገልጸው፥ ይህንን አዎንታዊ አመለካከት ጨለማ በበዛበት ዓለም ውስጥ ጠብቆ ለማቆየት እና ለመጋራት የሚያግዙ ስልቶችንም ጠቁመዋል።

"በተስፋ ደስ ይበላችሁ!" የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የሀገረ ስብከት ወጣቶች ቀን መልዕክት ዋና ጭብጥ፥ ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮም ሰዎች በጻፈው መልዕክት ላይ በማስተንተን፥ “ወጣትነት በተስፋ እና በህልም የተሞላ፣ ሕይወትን የሚያበለጽጉ በርካታ ውብ ነገሮች እንዳሉት፥ እነርሱም፥ በእግዚአብሔር የፍጥረት ግርማ፣ በጓደኝነት፣ ከሚወዳቸው ሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት እና በሌሎች በርካታ መልካም ነገሮች የተሞላ ነው” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

 

28 November 2023, 16:19