ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የወንጌል ደስታን የሚሰብክ ክርስቲያን እርሱ ታማኝ ነው!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ረቡዕ ኅዳር 5/2016 ዓ. ም. ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍልን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በዛሬው ዕለት ያቀረቡት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከዚህ ቀደም፥ “ለስብከተ ወንጌል ያለው ፍቅር፡- የምእመናን ሐዋርያዊ ቅንዓት” በሚል ዓብይ አርዕስት ሥር ሲያቀርቡት የነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል 26 እንደነበር ታውቋል። “ወንጌልን ማብሰር ደስታ ነው” በሚለው አርዕስት ሥር ባቀረቡት የዛሬው አስተምህሮ፥ “የወንጌል ደስታን የሚሰብክ ክርስቲያን ዘወትር ታማኝ ነው!” በማለት አስገንዝበዋል። ክቡራት ክቡራን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት ያቀረቡትን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! በርካታ የወንጌልን መልካም ዜና የማወጅ ምስክርነቶችን ከተመለከትን በኋላ፣ ይህን በተከታታይ ሲቀርብ የነበረውን እና “የወንጌል ደስታ” የሚለውን ሐዋርያዊው ቃለ ምዕዳን መሠረት በማድረግ ስለ ሐዋርያዊ ቅንዓት የሚያብራራ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮዬን በአራት ነጥቦች ጠቅለል አድርጌ ለማቅረብ እፈልጋለሁ። ‘የወንጌል ደስታ’ የተሰኘው ሐዋርያዊው ቃለ ምዕዳን በያዝነው ወር አሥረኛ ዓመቱን እንደሚያከብር ይታወቃል።

ዛሬ የምናየው የመጀመሪያው ነጥብ፥ የወንጌል ምስክርነት ከሚዛመድባቸው ይዘቶች አንዱ የሆነውን ደስታ ነው። መልአኩ ለእረኞቹ ከተናገረው ቃል እንደሰማነው፣ ለክርስቲያኖች የተነገረው መልዕክት፥ ‘ታላቅ ደስታን’ ማወጅ ነው (ሉቃስ 2፡10)። ለዚህ ታላቅ ደስታ ምክንያት ምንድን ነው? የምስራች መሆኑ ነው? አስገራሚ መሆኑ ነው? መልካም ክስተት መሆኑ ነው? ከሁሉም በላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ! እርሱ ስጋን ለብሶ ሰው የሆነው፣ እኛን ሁል ጊዜ የሚወደን፣ ለእኛ ሲል ነፍሱን አሳልፎ የሰጠ እና የዘላለምን ሕይወት ሊሰጠን የሚሻ አምላክ ነው። የማይጠፋ የደስታ ምንጭ የሆነው እርሱ ወንጌላችን ነው! ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እንግዲያውስ ጥያቄው የወንጌልን የምስራች ስለ ማወጅ ሳይሆን እንዴት ማወጅ እንደሚቻል እና ይህ ‘እንዴት’ የሚለው ጥያቄ ‘በደስታ’ የሚለውን መልስ እንድንሰጥ ያስችለናል።

ለዚህ ነው በአገልግሎቱ የማይደሰት፣ ዘወትር የሚያዝን፣ የማይረካ ወይም ከዚህም በበለጠ የሚቆጣ ወይም የሚናደድ ክርስቲያን ታማኝ የማይሆነው። ስሜታችንን በትኩረት መከታተል አስፈላጊ ነው። በተለይ ቤተ ክርስቲያን በተወሰነ መልኩ ማኅበራዊ እውቅናን በማታገኝበት ወቅት፥ ተስፋ መቁረጥ ወይም የመገለል ዝንባሌ ባለበት ሁሉ ዘወትር ስጋት አለ። ይህ መልካም አይደለም። ጥሩ ያልሆነ ወይም የማያስደስት ነገር የሚመጣው ጫናን በማድረግ እንጂ የወንጌል ምስክርነት ሲጓደል አይደለም። ታማኝነት እና ሃላፊነት ያለበት የወንጌል ምስክርነት የሚታወቀው በደስታ እና በየዋህነት የተሞላ ሕይወት ሲኖር ነው። ኢየሱስን ማግኘት የሚቻለው በመረጋጋት እና በየዋህነት ነው። ሳይገባን በነጻ የተቀበለውን ለሌሎች መስጠት የሚቻለው ቅን ልቦና ሲኖረን ነው።

በታሪክ ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ እንደ ደስታ ምንጭ የምንመለከትተው ከሆነ፥ የዚህ ደስታ ፍጻሜው የእርሱ ትንሳኤ ነው። ይህንንም በአስደናቂው የደቀ መዛሙርቱ የኤማሁስ ጉዞ ታሪክ ላይ እናገኘዋለን (ሉቃስ 24:13-35)። በሉቃስ ወንጌል ምዕ. 24 ላይ የተጻፈውን የደስታ ወንጌል ማንበብ መልካም ነው። ወደ ኤማሁስ ይጓዙ የነበሩ የሁለቱ ደቀ መዛሙርት ታሪክ፥ አንድ ሰው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከሆነ ከጭንቀት ወደ ብርሃነ ትንሳኤው ደስታ እንዴት እንደሚሸጋገር ያሳያል። በተለይ ጭንቀት በነገሠበት ወቅት፣ በተለያዩ ቦታዎች የእምነት ቀውስ በተፈጠረበት ወቅት፣ እኛም አንዳንድ ጊዜ ተስፋን በመቁረጥ፥ በሐዘን እና ተስፋን በመቁረጥ ከእየሩሳሌም ወጥተው እንደሚሄዱ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት በሽንፈት ስሜት ልንሸፈን እንችላል። ኤማሁስ በምትኩ ሁሉም ነገር ያለቀ በሚመስልበት፣ ከሞት ከተነሳው ከኢየሱስ ክርስቶስ ደስታ ጋር እንደገና መወለድን ገልጦልናል።

ይህም ወንጌል መጀመሪያ ሊሰበክላቸው የሚያስፈልጋቸው ደቀ መዛሙርት እንደሆኑ እና ኢየሱስ ክርስቶን እንደ ህያው አካል እንጂ እንደተለመደው ርዕሥ መመልከት እንደሌለብን ይነግረናል። እነዚያ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ቅዱሳት መጻሕፍትን እያብራራላቸው አብረዋቸው ከሚጓዘው ኢየሱስ ክርስቶስ እየተመሩ፣ ያልበሰለ እምነታቸው እና ምድራዊ አስተሳሰባቸው፥ ዓለማዊ ስኬትን ከመጠበቅ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው።ከዚያ በኋላ ግን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመገናኘታቸው፣ ይህም ማለት፣ ልብን በሚያቃጥል ቃሉ እና በተሰበረ ኅብስቱ ውስጥ ባለው አፍቃሪነቱ ተነሳሽነትን ሊያገኙ ችለዋል። በውስጣዊ ስሜት ተነሥተው ቀናተኛ የወንጌል አብሳሪዎች ለመሆን በቅተዋል። ‘በዚያች ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ’ ይላል (ሉቃ. 24:33)። እንዲህ ነው፡ የክርስቲያን ደስታ ከእኛ የሚመጣ ሳይሆን ከሙታን የተነሣው የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መንፈስ ስጦታ ነው።

ስለዚህ ወንጌል በመጀመሪያ ሊሰበክልን የሚገባን እኛ ክርስቲያኖች ነን። በዛሬው ፈጣን እና ግራ በሚያጋባን ዓለም ውስጥ ሆነን፣ እኛም ወንጌል ከእንግዲህ ወዲህ እንደማይሰማ እና ለመስበክ መጣር እንደሌለብን ራሳችንን በማሳመን በክህደት ስሜት ውስጥ ልንገኝ እንችላለን። ሌላው ቀርቶ ‘ሌሎች’ በሚፈልጉት እና በሚወዱት በራሳቸው መንገድ እንዲሄዱ በመፍቀድ ፈተና ልንፈተን እንችላለን። ይልቁኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ለዘላለም የሚኖር እና የማያቋርጥ አዲስ ምንጭ’ መሆኑን ለማወቅ ወደ ቅዱስ ወንጌል የምንመለስበት ጊዜ ይህ ነው (የወንጌል ደስታ ቁ. 11)። ልብ ሲደክም እና አድማሱ ሲጨልም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የምንገናኝበት ጊዜ ነው። በሚያብረቀርቅ ውበት፣ እጅግ ብሩህ እና አስደሳች፣ ከዚያም በደመ ነፍስ ሆነን በዙሪያችን ካሉ ሰዎች ጋር ልናስተዋውቀው እንፈልጋለን። ምክንያቱም እያንዳንዱ ትክክለኛ የእውነት እና የጥሩነት ልምድ በተፈጥሮው በውስጣችን ሊያድግ ይፈልጋል (የወንጌል ደስታ ቁ. 9)።

ስለዚህ ወደ ኤማሁስ ይጓዙ እንደ ነበሩት ሁለቱ ደቀ መዛሙርት፣ አንድ ውድ ሃብት ባገኘ ጊዜ በጉጉት ወደ ዕለታዊ ሕይወት ይመለሳል። ሰብዓዊነት የተስፋ ቃልን ከሚጠባበቁ ወንድሞች እና እህቶች ጋር ግንኙነት ያለው መሆኑን ይገነዘባል። አዎን! የወንጌል የምስራች ቃል ዛሬም ይጠበቃል። በዕቅድ የተደረሰ አለማመን እና ተቋማዊ የዓለማዊነት ስልጣኔን ጨምሮ በዘመናት ሁሉ ሰዎች ወንጌልን ይፈልጉታል። በእርግጥ በተለይም ሃይማኖት ትርጉም ባጣበት ማኅብረተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችም ቢሆኑ ወንጌልን ይፈልጉታል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም በሙሉ የሚሰበክበት ትክክለኛ ጊዜው አሁን ነው። ስለዚህ ለሁሉም ሰው በድጋሚ ማለት የምፈልገው ይህ ነው፥ ‘የወንጌል ደስታ’ ኢየሱስ ክርስቶስን በሚያገኙት ሁሉ ልብ እና ሕይወት ውስጥ ይሞላል። የእርሱን የድኅነት ስጦታ የተቀበሉ በሙሉ ከኃጢአት፣ ከሐዘን፣ ከውስጣዊ ባዶነት እና ከብቸኝነት ነፃ ወጥተዋል። ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ደስታ ሁል ጊዜ ያለማቋረጥ አዲስ ሆኖ ይወለዳል። ክርስቲያኖች በሙሉ በየትኛውም ቦታ እና በማንኛውም ጊዜ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አዲስ ግኑኝነትን እንዲፈጥሩ እጋብዛለሁ (የወንጌል ደስታ ቁ. 1፣ 1.3) ኢየሱስ ክርስቶስ የወንጌል ስርጭት መጀመሪያ እና የደስታ ምንጭ ነው”

 

 

15 November 2023, 16:29