ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ታማኝ የወንጌል መስካሪዎች ልንሆን እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እሑድ ጥቅምት 25/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በዕለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው ለምዕመናኑ ባቀረቡት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ፥ ታማኝ የቅዱስ ወንጌል ምስክሮች ልንሆን ይገባል በማለት አሳስበዋል። ክቡራት ክቡራን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ጥቅምት 25/2016 ዓ. ም. ያቀረቡት የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል ምንባብ አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል:-

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እንደምን አረፈዳችሁ! ከማቴ. 23: 1-12 ተወስዶ የተነበበው የዕለቱ ምንባብ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሕዝቡ የሃይማኖት መሪዎች  ስለ ሆኑት ጸሐፍትና ፈሪሳውያን የተናገራችውን አንዳንድ ቃላት እንመለከታለን። በሥልጣን ላይ ያሉትን እነዚህን ሰዎች በተመለከተ ኢየሱስ ክርስቶስ ከባድ ቃላትን በመጠቀም ይናገር ነበር። ‘ይሰብካሉ ነገር ግን የሚሰብኩትን ወይም የሚናገሩትን በተግባር አይፈጽሙትም’ (ማቴ 23፡3) ‘ሥራቸውን የሚሠሩት ሌሎች ሰዎች እንዲያዩላቸው በማለት ብቻ ነው’ (ቁ. 5)። ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ይህንን ነው:- ይሰብካሉ ነገር ግን የሚሰብኩትን በተግባር አይለማመዱትም፤ በተግባር የሚያደርጉት ካለ ሰዎች እንዲያዩላቸው ብለው እንጂ ለሌላ አይደለም።

እንግዲህ በእነዚህ ሁለት ገጽታዎች ማለትም በመናገር እና በመሥራት መካከል ያለውን ርቀት ቆም ብለን እንመልከት። ውጫዊው ገጽታ ከውስጣዊው ገጽታ በልጦ የተገኘበትን ሁኔታ እንመልከት። በመናገር እና በመሥራት መካከል ያለው ርቀት ማለት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ለሌሎች እናስተምራለን በማለት ራሳቸውን ክብር እንደሚገባቸው የቤተ መቅደስ ባለ ሥልጣናት አድርገው የሚናገሩትን የእስራኤል መምህራን ሕይወት ሁለት ገጽታዎች ይሟገታል።

እነዚህ መምህራን ስለ አንደ ነገር ይሰብካሉ፤ ነገር ግን የሚኖሩት የሚሰብኩትን ሳይሆን ሌላ ሕይወት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገራቸው ቃላት የነቢያትን በተለይም የነቢዩ ኢሳይያስን ንግግር ያስታውሳሉ፡- ‘ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባል፥ በከንፈሮቹም ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው’ (ኢሳ 29፡13)። ልብን ለሁለት የመክፈል አደጋ ይህ ነው። ልብን ለሁለት መክፈል የምሥክርነታችንን ትክክለኛነት እንዲሁም እንደ ሰው ወይም እንደ ክርስቲያኖች ያለንን ታማኝነት አደጋ ላይ ይጥለዋል።

ከደካማነታችን የተነሳ ሁላችንም በምንናገረው እና በምንሠራው መካከል የተወሰነ ርቀት ያጋጥመናል። ነገር ግን ወደ ሌላ ያዘነበለ ወይም የተባዛ ልብ መያዝ ሌላ ነገር ነው። ይህ ማለት አንድ እግራችንን በአጥሩ ሁለቱ በኩል ማቆም እንደ ማለት ነው። በተለይ ይህን ምሳሌ የኃላፊነት ሚናን እንድንጫወት ከሚሰጠን አደራ ጋር በማዛመድ እንመልከተው። በሕይወታችን፣ በህብረተሰብ ወይም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ካለን ሃላፊነት ጋር በማዛመድ እንመልከተው። ‘ሁለት ዓይነት ሰው መሆን አይገባም!’ የሚለው ሕግ በካህን፣ በሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ በተሰማሩት ሰዎች፣ በፖለቲከኛ፣ በአስተማሪ ወይም በወላጅ ዘንድ ዘወትር ይሠራል። የምትናገረውን እና ለሌሎች የምትሰብከውን በተግባር ለመኖር መጀመሪያ በራስህ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ያስፈልጋል። ትክክለኛ አስተማሪዎች ለመሆን ከፈለግን በቅድሚያ ታማኝ ምስክሮች መሆን ያስፈልጋል።

ሁለተኛው ውጫዊው ገጽታ ከውስጣዊው ገጽታ በልጦ የተገኘበትን ሁኔታ እንመልከት። እንደ እውነቱ ከሆነ፥ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን በሁለት ማንነት የሚኖሩት ስማቸውን ከውርደት ለማዳን እና ማንነታቸውን መደበቅ እንዳለባቸው በማሰብ ነበር። በእርግጥም ሕዝቡ ልባቸው ውስጥ ያለውን ነገር ቢያውቅ ኖሮ ያፍሩ ነበር። ታማኝነታቸውንም ያጡ ነበር። እኛ እንደምንለው ‘ጻድቅ ለመምሰል’ ነበር የሞከሩት። ራሳቸውን ከውርደት ለማዳን ጥረዋል። ይህ ብልሃት ወይም ዘዴ በጣም የተለመደ ነው። ፊታቸውን ይኳኳላሉ። ሕይወታቸውን እና ልባቸውምን ጭምር ይኳኳላሉ። እነዚህ ሰዎች እውነተኛ ሕይወትን እንዴት መኖር  እንደሚቻል አያውቁም። ብዙ ጊዜ እኛም ሁለት ዓይነት ሰው የመሆን ፈተና ያጋጥመናል።

ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውንን ማስጠንቀቂያ ተቀብለን ራሳችንን እንዲህ በማለት እንጠይቅ፦ የምንሰብከውን በተግባር ለመኖር እንጥራለን? ወይስ የሐሰት ሕይወት እንኖራለን? የምንናገረውን ትተን ሌላ ነገር እንሠራለን? ጭንቀታችን ከውስጣዊው ማንነታችን ይልቅ ውጫዊው ማንነታችን እንከን እንዳይኖርበት ነው?

እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በቅንነት እና በትሕትና የኖረች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታማኝ የወንጌል መስካሪዎች እንድንሆን ታግዘን።”

06 November 2023, 15:45