ፈልግ

የቫቲካን ዋና ጸኃፊ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን የቫቲካን ዋና ጸኃፊ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን   (ANSA)

ካርዲናል ፓሮሊን፡ የጳጳሱ የዱባይ ጉብኝት ሙሉ በሙሉ በሙሉ ባለማገገማቸው ተሰርዟል አሉ።

በጣሊያን ምክር ቤት በተዘጋጀው ዝግጅት ላይ የቫቲካን ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን እንደተናገሩት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጤና ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን እና ሙሉ በሙሉ ማገገማቸውን ለማረጋገጥ ወደ ዱባይ ለ COP28 ጉባኤ ሊያደርጉት የነበረው ጉዞ መሰረዙን አረጋግጠዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

"የቅዱስ አባታችን ሁኔታ የተረጋጋ ነው፣ ትኩሳት የላቸውም፣ ነገር ግን ከመተንፈሻ አካላት ጋር ተያይዞ የሚመጣው የሳንባ እብጠት አሁንም ቀጥሏል፣ የአንቲባዮቲክ ሕክምና ይቀጥላል" ሲሉ መናገራቸውም ተዘግቧል።

የቅድስት መንበር የዜና ማሰራጫ ጽ/ቤት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮን የጤና ሁኔታ አስመልክቶ አጭር ዘገባ ረቡዕ አመሻሽ ላይ ይፋ ማድረጉም ይታወሳል።

ቀደም ባሉት ጊዜያት ጳጳሱ ከጉንፋን እና ከሳንባ እብጠት በጥሩ ሁኔታ እያገገሙ መሆናቸውን ያረጋገጡት የቫቲካን ዋና ጸሐፊ የሆኑት ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ቅዱስነታቸው በመጪው ሳምንት ወደ ዱባይ የሚያደርጉትን ጉዞ ለመሰረዝ ወስነዋል ሲሉ ተናግረዋል።

"ጳጳሱ በማገገም ላይ ናቸው፣ የሐኪሞቹን ምክር በመቀበል ራሳቸውን ለአደጋ ማጋለጥ አልፈለጉም” ብለዋል ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በ COP28 የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አርብ ኅዳር 21/2016 ዓ.ም ወደ ዱባይ እንዲሄዱ ታቅዶ ነበር።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በጣሊያን ምክር ቤት በተዘጋጀው ዝግጅት ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “ይህን ምርጫ ቅዱስነታቸው ያደረጉት ያገረሸባቸውን ሁኔታ ለማስወገድ ነው ብዬ አምናለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ማክሰኞ ማምሻውን የቅድስት መንበር የዜና ማሰራጫ ጽ/ቤት ዳይሬክተር በኩል እንዳስታወቁት ጳጳሱ በዱባይ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ የሚሳተፉበትን “ዘዴዎችን” በማጥናት ላይ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

"በእዚህ ላይ እየሰራን ነው። ከፓሪስ ጀምሮ እና ከእዚያን በመቀጠል በተካሄዱት “COP” (የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አመታዊ የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ ‘የፓርቲዎች ኮንፈረንስ’ ወይም ‘COP’ በመባል የሚታወቀው የአየር ንብረት ለውጥን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል የአለም መሪዎችን፣ ሚኒስትሮችን እና ተደራዳሪዎችን ያሰባስባል) ጉባኤዎች ላይ ተሳትፌያለሁ ስለዚህ በዚህም ጊዜ የምሄድ ይመስለኛል፣ ግን በግልፅ ጉብኝቴን በተቻለ መጠን አሳጥራለሁ” ብለዋል ካርዲናል ፓሮሊን።

የቫቲካን ልኡካን ቡድን በዱባይ ለሁለት ሳምንታት በሚቆየው ውይይት እና ጉባኤ ላይ እንደሚሳተፍ የቫቲካን ዋና ጸሐፊ ካርዲናል ፒትሮ ፓሮሊን የገለጹ ሲሆን "እኔ የምሳተፈው በመጀመሪያው ክፍል  ላይ ብቻ ነው" ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት እና የሁለትዮሽ ስብሰባዎች

ቫቲካን ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ጋር የምታደርገውን ውይይት በበላይነት የሚቆጣጠረው ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ሚጌል አንጄል አዩሶ በጉባኤው ላይ ለመሳተፍ ወደ ዱባይ እንደሚያቀኑ ይጠበቃል።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን የሃይማኖታዊ ውይይት ክፍልን ማለትም በኤግዚቢሽኑ አካባቢ የእምነት ፓቪሎን ምረቃን ምክንያት በማድረግ ለታህሳስ ወር የታቀደውን ሰነድ ለመፈረም ወደ እዚያ እንደሚያቀኑ ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ቅዳሜ ኅዳር 21/2016 ዓ.ም በታቀዱት የሁለትዮሽ ስብሰባዎች ላይ በርካታ የሀገር መሪዎች እና የመንግስት መሪዎች በዝግጅቱ ላይ ተገኝተው መሳተፍ ባለመቻላቸው የቫቲካን ዋና ጸሐፊ የሆኑት ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ማዘናቸውን ገልጸዋል ።

"ብዙ የፖለቲካ መሪዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን ለማየት ጠይቀው ነበር" ብሏል። "እንደ አለመታደል ሆኖ ይህ ሊሆን አይችልም" ሆኖም “ሊቃነ ጳጳሳቱን ለማየት የጠየቁ ብዙ ሰዎች መኖራቸው ከወዲሁ ጥሩ ምልክት ነው” እናም ይህንን ያመለጠውን እድል ለማካካስ እንደሚጥሩም ጠቁመዋል።

 

30 November 2023, 13:31