ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የአገራት መሪዎች የሰላም ጎዳናን ለመፈለግ እንዲነሳሱ ወደ ቅድስት ማርያም ተማጸኑ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጦርነት እና በስቃይ በተሰበረ ዓለም ውስጥ ምዕመናን አብረዋቸው ለሰላም እና ለእርቅ እንዲጸልዩ ጠይቀው፥ ልጇ ሲሰቃይ የተመለከተች የሰላም ንግሥት ቅድስት ድንግል ማርያም ለዓለማችን መፅናናትን እና ተስፋን ትሰጠው ዘንድ ተማጽነው፥ መላውን ዓለም በተለይም በጦርነት ውስጥ የሚገኙትን አገሮች ለእመቤታችን ማርያም በአደራ አቅርበውላታል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሕይወታችንን፣ ቤተ ክርስቲያንን እና መላውን ዓለም የሰላም ንግሥት ለሆነች እመቤታችን ቅድስት ማርያም አቅርበው፥ በጥላቻ የታሠሩትን ሰዎች ልብ እንድትነካ እና ግጭት የሚቀሰቅሱትን ከድርጊታቸው እንድትመልሳቸ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እናት ቅድስት ማርያም ዘንድ ጸሎታቸውን አቅርበዋል። የአገራት መሪዎች ወደ ሰላም መንገድ ለመመለስ እንዲነሳሱ፥በክፋት ተታልለው በኃይል እና በጥላቻ የታወሩ ልጆችን እንድታስታርቅ በማለት የሕዝቦች ሁሉ ንግሥት ወደ ሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ለሰላም የተመደበ የጸሎት፣ የጾም እና የንስሐ ቀን

ር ዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጸሎታቸውን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ያቀርነሱት በቅድስት አገር እየተከሰተ ያለውን አስከፊ የዓመፅ ድርጊት በማስመልከት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ዓርብ ጥቅምት 16/2016 ዓ. ም. በተዘጋጀው የጸሎት፣ የጾም እና የንስሐ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደሆነ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 18/2023 ባስተላለፉት መልዕክት፥ ልዩ ልዩ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች እና የሃይማኖቶች ተከታዮች በተመደበው የጸሎት ቀን ኅብረታቸውን እንዲገልጹ በማለት ጥሪያቸውን ማቅረባቸው ይታወሳል። የወንጌል ንባባት፣ ጸሎቶች፣ አስተንትኖ፣ የመቁጠሪያ ጸሎት እና የቅዱስ ቁርባን ስግደት የነበረበትን ሥነ-ሥርዓት የመሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ምዕመናኑ በጸሎት ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፊት እንዲቀርቡ በማለት አሳስበዋል። በዚህ የጨለማ ሰዓት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ጭንቀታችንን እና ፍርሃታችንን ለሚያውቅ ለእናት ልብህ እራሳችንን እና ችግሮቻችንን በአደራ እናቀርባለን” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ብቻችን ልንወጣው አንችልም

ቅድስት ማርያምን የብርሃን እና የተስፋ ምንጭ ብለው የጠሯት ቅዱስነታቸው፥ “ማርያም ሁል ጊዜ በእርጋታ፣ በፍቅር እና በይሁንታ ፈተናዎች እንዴት ማለፍ እንደቻለች ሁሉ፥ የብርሃነ ትንሳኤው  የተስፋ ሌሊትን በሐዘን ያሳለፈች ቅድስት ድንግል ማርያም እንድትረዳ” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።ቅዱስነታቸው በማከልም፥ እነዚህን የግጭት ጊዜያት በራሳችን ብቻ መቋቋም ባለመቻላችን ለኛ በመቆም እንድታግዘን በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ጸሎታቸው፥ ከሰላም መንገድ ርቀው ግጭት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ልብ ሰላማችን የሆነው ልጅሽ ጌታች ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲለውጠው በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

የልጆቿን እንባ እንድታብስ፥ ከአቅመ ደካሞች እና ብቻቸውን ከቀሩ ሰዎች፣ ከቆሰሉት፣ ከታመሙት፣ ቤታቸውን እና የሚወዷቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ከተገደዱት ጋር በመሆን ተስፋቸው እንድትሆናቸው በማለት ወደ እመቤታችን ማርያም ዘንድ ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ጸሎታቸውን ወደ እመቤታችን ማርያም ንጹሕ ልብ ዘንድ አቅርበዋል

ራሳችንን እና ያለንን ሁሉ በሙሉ ለእመቤታችን ማርያም ንጹሕ ልብ እንሰጣለን” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ለዓለም በሙሉ ስለ ኢየሱስ ፍቅር በመመስከር የሰላም መሣሪያ እና የመግባባት ምልክት ትሆን ዘንድ ቤተ ክርስቲያንንም ለእመቤታችን ማርያም ንጹሕ ልብ እናቀርባለን ብለዋል።መላውን ዓለም በተለይም በጦርነት ውስጥ የሚገኙትን አገሮች እና አካባቢዎችን ለማርያም ንጹሕ ልብ እናቀርባለን" ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጸሎታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ “የብርሃን ጭላንጭል የጨለማውን የግጭት ምሽት እንዲያበራ እና የአገራት መሪዎችም የሰላም ጎዳናን እንዲፈልጉ” በማለት ጸሎት አቅርበዋል።

“የሕዝቦች ሁሉ ንግሥት ሆይ! በክፉ ተታልለው በኃይል እና በጥላቻ የታወሩ ልጆችን እንድታስታርቃቸው በመለመን፥ ለሁሉም ቅርብ የሆነች እናታችን ሆይ! በጥላቻ የተራራቁትን በአንድነት እንድትሰብስባቸው፥ ለሁሉም የምትራሪ ማርያም ሆይ እርስ በርሳችን እንድንተሳሰብ አስተምሪን፤ የእግዚአብሔርን ርኅራኄ እና ፍቅር የምትገልጪ እናታችን ሆይ! የእርሱ የመጽናናት እና የሰላም ምስክሮች አድርጊን፤ የሰላም ንግሥት ሆይ! የእግዚአብሔርን የመግባባት ስጦታ በልባችን ውስጥ እንዲፈስ አድርጊልን በማለት ጸሎታቸውን ደምድመዋል። 

 

 

28 October 2023, 18:30