ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የኢየሱስ ታናናሽ እህቶችን በቫቲካን ሲቀበሏቸ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የኢየሱስ ታናናሽ እህቶችን በቫቲካን ሲቀበሏቸ  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የኢየሱስ ታናናሽ እህቶችን ለአገልግሎታቸው አመሰገኑ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የኢየሱስ ታናናሽ እህቶች ማኅበር አባላትን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። በቅዱስ ቻርል ዴ ፉኮው ሕይወት በመማረክ የፍቅር ሥራን በማበርከት ላይ ለሚገኙ የኢየሱስ ታናናሽ እህቶች ማኅበር አባላት ባደረጉት ንግግር፥ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር ተቀብለው ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ለማገልገል እራሳቸውን እንዲሰጡ ጋብዘው፥ የማኅበሩ እህቶች በተደበቀ ሕይወታቸው በኩል በሚያቀርቡት አገልግሎት ይበልጥ መለኮታዊ እንደሚሆኑ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እግዚአብሔርን መፈለግ፣ የወንጌል ምስክርነት እና ለተሰወረው ሕይወት ፍቅርን መግለጽ፥ እነዚህ የቅዱስ ቻርል ዴ ፉኮው የሕይወት ልምድ የሚያሳዩ መሆናቸውን፥ የማኅበራቸውን ጠቅላላ ምዕራፍ ስብሰባን ላካሄዱት የኢየሱስ ታናናሽ እህቶች ማኅበር አባላት ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለደናግሉ ባደርጉት ንግግር፥ በመጀመሪያ ደረጃ በአምልኮ ወቅት በመንበረ ታቦት ፊት የእግዚአብሔርን ቃል ማዳመጥ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረው፥ በዚህ መንገድ የሰው ልብ የእግዚአብሔርን መንገድ ለመከተል ክፍት እንደሚሆን እና ዓመፅን ሳያነሳ ነገር ግን በፍቅር ስሜት ለአገልግሎት እንደሚነሳ አስረድተዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅሩን እንደሚያቀርብላቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ አንዳንድ ተስፋ አስቆራጭ ነገሮችን ወደ ጎን በመተው ፈተናን መቀበል እንደሚገባ እና እግዚአብሔር ሕይወታቸውን በስጦታ ባቀረቡት ሰዎች መካከል ፍቅርን እንደሚያበዛ አስረድተዋል። በቃሉ ብርሃን በኩል የኢየሱስ ክርስቶስን ፍላጎት ለይቶ ማወቅ እና ከዚያ በኋላም እንደገና በመጓዝ በአለቆች የተቀመቱ ግቦችን ማሳካት እንደሚቻል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተናግረዋል።

ለሌሎች እየተንከባከቡ ወንጌልን መመስከር

የወንጌል ምስክርነትን በተመለከተ፣ በበጎ አድራጎት ሥራዎች፥ በወንድማማችነት እና ለሌሎች ስጦታ በመሆን፣ ሁሉም የታናናሽ እህቶች ማኅበር አባላት የቅዱስ ቻርል ዴ ፉኮው ጥሪን እንዲመሰክሩ አሳስበዋል። ቅዱስ ወንጌልን በማስቀደም፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወታቸው እንዲገለጽ በማድረግ እና በጸሎት፣ በፍቅር ሥራ እና በመልካም አርአያነት እራስን ለሌሎች መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሌሎችን መንከባከብ እና የተቸገሩትን መርዳት እነዚህ የፍቅር ምልክቶች ናቸው ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ይህም በትንሹ የመተሳሰብ እና የመቀራረብ ባህርያት መገለጫዎች ናቸው ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም በዛሬዎቹ ማኅበረሰቦች መካከል ሃብትን ለመልካም ተግባር የማያውሉ ከሆነ ልብን ማደንደን እና መዝጋት እንደሚሆን አስረድተዋል።

የግዴለሽነት ፈተና

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለኢየሱስ ታናናሽ እህቶች ማኅበር አባላት ባደረጉት ንግግር፥ ግዴለሽነትን በመዋጋት በአንድነት የእግዚአብሔር ልጆች በመሆን ለዓለም በሁሉ ወንድማማችነትን መመስከር እንደሚገባ አሳስበዋል። የምሥክርነት ልብ፥ ምጽዋዕት መስጠት፣ የዋህ መሆን እና ከሰው ሁሉ ጋር ትሑት መሆን፥ እነዚህ በሙሉ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተማርናቸው በመሆናቸው ከሁሉም ጋር በሰላም መኖር እንደሚገባ አሳስበዋል።

ወደ ቅድስት ከተማ ናዝሬት የሚወስደው መንገድ

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም ለተደበቀ ሕይወት ያለው ፍቅር፥ ቻርል ዴ ፉካው ከሞተ ከሃያ ዓመታት በኋላ እህት መቅደሊን ሁቲን እና እህት አን ካዶሬት ለጀመሩት ተነሳሽነት ወደ ቅድስት ከተማ ናዝሬት የሚወስድ የአንድነት መንገድ ቅዱስነታቸው ገልጸው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ የትንንሾችን ሕይወት ለመካፈል ራሱን ትንሽ ማድረጉን አስረድተዋል። የእህቶች ማኅበር አገልግሎቱን ይበልጥ በስውር ባቀረቡት መጠን የበለጠ መለኮታዊ እንደሚሆን ቅዱስነታቸው ተናግረው፥ አገልግሎታቸውን ማዳበር እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

ወንጌላዊ ርህራሄ

“የኢየሱስ ታናናሽ እህቶች ማኅበር በዓለም ውስጥ ትናንሽ የወንጌል ርኅራኄዎችን ለመዝራት የሚረዳ ውድ መሣሪያ ነው” በማለት የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የኢየሱስ ታናናሽ እህቶችን በማበረታታት፣ ማኅበሩ “የጥሪ እጥረት ቢታይበትም፣ አንዳንድ የማኅበር ቤቶች ቢዘጉም፥ የእህቶች ዕድሜ እጨመረ ቢመጣም ከኢየሱስ ክርስቶስ እና ከድሆች ጋር በመዋደድ ለጋስነታቸውን ዘወትር እንዲቀጥሉ ብርታትን ተመኝተው ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ ማኅበሩ ከጊዜ በኋላ ፍሬን እንደሚያፈራ በመናገር፥ መነኮሳቱ በሮም ሀገረ ስብከት ውስጥ ለሚያበረክቷቸው አገልግሎቶች ምስጋናቸውን አቅርበው፥ እህት ጄኔቪቭ በማኅበረሰቡ የተገለሉ ሰዎችን ብዙ ጊዜ እንደሚጎበኟቸው አስታውሰዋል።

02 October 2023, 17:49