ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የማኅበሩ መሥራች ከሆኑት አባ ሉዊጂ ቾቲ ጋር ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የማኅበሩ መሥራች ከሆኑት አባ ሉዊጂ ቾቲ ጋር   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ከማፊያ ቡድን ተለይተው የወጡ ሴቶችን በድፍረታቸው አደነቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሕይወታቸውን ከማፊያ የወንጀለኞች ቡድን የመለሱ የጣሊያን ሴቶችን በቫቲካን ተቀብለው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ለአባሉት በደረጉት ንግግር፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁል ጊዜም ከጎናቸው መሆኑን ተገንዝበው ያለ ፍርሃት በድፍረታቸው እንዲጸኑ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ጣሊያን ውስጥ ከቤተሰቦቻቸው ርቀው ማፊያ ከተባለ የተደራጀ ቡድን ሆነው የወንጀል ድርጊቶችን ሲፈጽሙ የቆዩ አሁን ግን ተለይተው የወጡ የጣሊያን ሴቶች ቡድን አባላትን ሰኞ ጥቅምት 19/2016 ዓ. ም. በቫቲካን አቀባበል አድርገውላቸዋል። ቡድኑን ወደ ቫቲካን የመሩት፥ "ሊበራ" የተሰኘውን የጸረ ማፊያ ማኅበር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1995 ዓ. ም. የመሠረቱት ጣሊያናዊ ካኅን አባ ሉዊጂ ቾቲ እንደነበሩ ታውቋል።  

ማኅበሩ ከወንጀለኞች የተነጠቀውን መሬት እና ንብረት በማስተዳደር የሀገር ውስጥ የኅብረት ሥራ ማህበራትን፣ ፀረ አደንዛዥ ዕጽ ፕሮጄክቶችን እና የማኅበረሰብ ማዕከላትን በማቋቋም እንዲሁም ከወንጀሉ እራሳቸውን ላገለሉት ሰዎች የሥራ ዕድልን ለመፍጠር ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ እንደሆነ ታውቋል።

"ሊበራ" የተሰኘው ማኅበሩ፥ ሙስናን እና የተደራጁ ወንጀሎችን ለመቃወም በሚደረገው ጥረት መካከል ማኅበራዊ ፍትህን እና ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር የሚንቀሳቀሱ ማኅበራትን፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን፣ ሕዝባዊ ድርጅቶችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ሌሎች ልዩ ልዩ ማኅበራዊ እና የቤተ ክርስቲያናት ተቋማትን ያካተተ እንደሆነ ታውቋል።

ሴቶቹ ብቸንነት ሊሰማቸው አይገባም

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከወንጀል ቡድኑ እራሳቸውን ላገለሉት የቡድኑ አባላት ባደረጉት ንግግር፥ ሴቶቹ ብቻቸውን እንዳልሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ከጎናቸው መሆኑን በማወቅ ያለ ፍርሃት በምርጫቸው እንዲጸኑ አሳስበዋል። ከኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መካከል እንደ ወንዶቹ ሁሉ ፍጹማን ያልሆኑ አንዳንድ ሴቶችም እንደነበሩ አስታውሰው፥ በሕይወት የተፈተኑ፥ አንዳንዴም በክፉት የተበከሉ ሴቶች እንደነበሩ ተናግረዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚያን ሴቶች በርኅራኄ እና በገርነት ተቀብሎ መፈወሳቸውን አስታውሰው፥ ሴቶቹ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የነጻነት ጎዳና መጓዛቸውን አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው በማከልም፥ “አንድ ሰው ነጻ የሚሆነው በምትሃታዊ ሳይሆን ወደ እግዚአብሔር በመመለስ፣ በመስቀሉ ውስጥ በማለፍ እና ወደ ትንሳኤ የሚመራ እርምጃውን እና መንገዱን በመካፈል ነው" በማለት አስረድተዋል።

ኢየሱስ በሕይወት መንገድ ዘወትር ከእኛ ጋር ይጓዛል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለቡድኑ አባላት በለገሱት ምክር፥ ትንሿ የቅዱስ ወንጌል መጽሐፍ እንዳትለያቸው፥ በየዕለቱ በእርጋታ በማንበብ ከኢየሱስ ክርስቶስ እና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር መሆናቸውን ማሰብ እንዳለባቸው አሳስበዋል። “በእርግጥም በሕይወት መንገድ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር አብሮን ይጓዛል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “መስቀሉ ለመስቀላችን ትርጉም የሚሰጥ፥ ትንሳኤውም የተስፋ ምንጫችን ነው” በማለት አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ፥ የሴቶች ቡድኑ ላደረገው ጉብኝት ምስጋናቸውን አቅርበው፥ የቡድኑን አባላት፥ ወዳጆቻቸውን በተለይም ልጆቻቸውን በጸሎት እንደሚያስታውሳቸው ተናግረው፣ የእግዚአብሔርን ቡራኬ እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥበቃን በጸሎታቸው ጠይቀዋል።

የ "ሊበራ" ማኅበር

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1995 ዓ. ም. የመሠረተው "ሊበራ" የተሰኘ ጸረ ማፊያ ማኅበር በአሁኑ ወቅት በመላው ጣሊያን ከ270 በላይ ማኅበራት ያሉት ሲሆን፥ ዓለም አቀፍ ቅርንጫፎቹም በአውሮፓ፣ በአፍሪካ እና በደቡብ አሜሪካ በሚገኙ 35 አገራት ውስጥ 80 የሚያህሉ ማኅበራት እንዳሉት ታውቋል።

31 October 2023, 16:32