ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “እግዚአብሔርን እና ባልንጀራን መውደድ የሁሉ ነገር መሠረት ነው” አሉ

በቫቲካን ከመስከረም 23 እስከ ጥቅምት 18/2016 ዓ. ም. ድረስ የተካሄደው 16ኛ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በተካሄደው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ተገባዷል። እሑድ ጥቅምት 18/2016 ዓ. ም. የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የመሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሲሆኑ፥ በሥነ-ሥርዓት ወቅት ባሰሙት ስብከት፥ “እግዚአብሔርን እና ባልንጀራን መውደድ ለሁሉም ነገር መሠረታዊ ነው” በማለት አስረድተዋል። ክቡራት ክቡራን፥ ቅዱስነታቸው ያቀረቡትን ቃለ ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው ቀርቧል:-

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አንድ የሕግ መምህር ኢየሱስን ሊፈትነው ፈልጎ ጥያቄን አቀረበ። ጥያቄው አንዳንድ ጊዜ በልባችን እና እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የሚነሳ ጠቃሚ ጥያቄ ነበር። ከሕጎቹ የትኛይቱ ትዕዛዝ ትበልጣለች?’ የሚል ነበር (ማቴ 22፡36)። እኛም፥ ‘እጅግ አስፈላጊው ነገር የቱ ነው? የሚገፋፋን ኃይል የቱ ነው? የሁሉ ነገር መመሪያ ሊሆን የሚችለው የቱ ነው?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። የኢየሱስ ክርስቶስ መልስ ግልጽ ነበር፡- ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ሐሳብህ ውደድ…፤ ሁለተኛይቱም ይህን ትመስላለች፡ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ’ የሚል በማለት መለሰ (ቁ.37,39)።

ወንድሞቼ ካርዲናሎች፣ ጳጳሳት እና ካህናት፣ ገዳማውያት እና ገዳማውያን፣ የተወደዳችሁ ምዕመናን፤ በ16ኛ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ መደምደሚያ ላይ ሁሉም ነገር በአዲስ መልክ የሚጀምርበትን መርህ እና መሠረት መመልከት አስፈላጊ ነው። ይህም መውደድ የሚል ነው። እግዚአብሔርን በሙሉ ሕይወታችን መውደድ እና ባልንጀሮቻችንን እንደ ራሳችን አድርገን መውደድ ማለት ነው። ዋናው የእኛ ዘዴ፣ ስሌት እና ዓለማዊ መንገድ ሳይሆን የእግዚአብሔር እና የባልንጀራን ፍቅር የሁሉ ነገር መሠረት ነው። ይህን ፍቅር እንዴት ለሌሎች ማስተላለፍ እንችላለን? በዚህ አጋጣሚ መግለጽ የምፈልጋቸው ሁለት ቃላት ወይም ልባዊ ተነሳሽነቶች አሉኝ። እነርሱም ስግደት እና አገልግሎት ናቸው። ለእግዚአብሔር በመስገድ እና እርሱን በማገልገል ፍቅራችንን እንገልጽለታለን። የስግደት እና የአምልኮው አስደናቂነት በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ በተለይም በዘመናችን ውስጥ የተዘነጋ ጉዳይ ነው። እግዚአብሔርን ማምለክ ማለት እርሱ ብቻ ጌታ እንደሆነ እና የሕይወታችን እና የቤተ ክርስቲያን ጉዞ መሠረት እና የመጨረሻው የታሪክ ውጤት በፍቅሩ ርኅራኄ ላይ የተመሠረተ መሆኑን በእምነት መቀበል ማለት ነው። እግዚአብሔር ሕይወታችን ትርጉም እንዲኖረው ያደርጋል።

እግዚአብሔርን ብቻ በማምለክ ነፃነታችንን በድጋሚ እናረጋግጣለን። ለዚህም ነው ቅዱሳት መጻሕፍት የእግዚአብሔርን ፍቅር ማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮን ከመዋጋት ጋር ደጋግሞ የሚያይዘው። እግዚአብሔርን የሚያመልኩት ጣዖትን ይጠላሉ። ምክንያቱም እግዚአብሔር ነፃ ያወጣቸዋል። ጣዖትን ማምለክ ግን ባሪያዎች ያደርጋቸዋል። ጣዖታት ያታልሉናል፤ የገቡትን ቃል አይፈጽሙም። ምክንያቱም እነርሱ የሰው እጅ ሥራ ናቸውና (መዝ 115: 4)። ቅዱሳት መጻሕፍት ለጣዖት አምልኮ የማታጠፉ አይደሉም። ምክንያቱም ጣዖታት የሚከናወኑት በሰዎች ነው። ሕያው አምላክ እግዚአብሔር ግን ያለና የሚኖር ነው። እርሱ እኛ ከማስበው በላይ የሆነ እና ከእርሱ በምንጠብቀው ነገር ላይ የማይመካ ሕያው የሆነ አምልክ ነው። ስለ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ትክክለኛ አመለካከት እንደሌለን የሚገልጽ ማስረጃ ቅሬታ እንዲያድርብን ያደርጋል። እግዚአብሔር እንዲህ ያደርጋል ብሎ ማሰብ ይልቁንም ስህተት ነው። ምክንያቱም በዚህ መንገድ የምናስብ ከሆነ እርሱ እኛ በምንሰጠው አስተያየት ነገሮችን እንዲሠራልን እንፈልጋለን ማለት ነው። ወደ ጣዖት አምልኮ እንመለሳለን ማለት ነው። እግዚአብሔርን መቆጣጠር እንደምንችል፣ ፍቅሩን በራሳችን አጀንዳ መገደብ እንደምንችል የምናስብ ከሆነ ሁልጊዜም አደጋ ላይ እንሆናለን ማለት ነው። ከዚህ ይልቅ እርሱ የሚወስደው መንገድ ሁልጊዜ ሊተነበይ የማይችል እና ከምናስበው በላይ የሆነ በመሆኑ አድናቆትን እና ስግደትን ማቅረብ ይጠይቃል። በእርሱ ሥራ መደነቅ በጣም አስፈላጊ ነው! ከሁሉም ዓይነት የጣዖት አምልኮ ጋር ያለማቋረጥ መታገል አለብን። ብዙውን ጊዜ ከከንቱ ውዳሴ የሚመነጩት ዓለማዊ ጣዖቶች ብቻ ሳይሆኑ ለስኬት መሮጥ፣ ለራስ ወዳድነት እና ዲያቢሎስ “በኪስ” በኩል መግባት እንደሚፈል ዘንግተን በገንዘብ መጎምጀት የለብንም።

የሙያ ማበረታቻዎች እንደሚያባብሉን መዘንጋት የለብንም። ነገር ግን ከእነዚያ የጣዖት አምልኮ ዓይነቶች ማለትም ከግል ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ፣ ከግል የሐዋርያዊ አገልግሎት ችሎታ እና ከእግዚአብሔር ይልቅ ራስን ማዕከል ከማድረግ ፈተና እንጠንቀቅ። እግዚአብሔርን በእውነት ወደማምለክ እንመለስ። ሐዋርያዊ እረኞች ለሆንን በሙሉ እግዚአብሔርን ማምለክ ቀዳሚ ዓላማ ይሁነን። በየቀኑ መልካሙ እረኛ ወደ ሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ለመቅረብ እና በመንበረ ታቦት እርሱን ለማገልገል ጊዜን እንስጥ። ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን ታወድስ። በየሀገረ ስብከቱ፣ በየቁምስናው፣ በእያንዳንዱ ማኅበረሰብ መካከል ለእግዚአሔር እንስገድ! ይህን በማድረግ ብቻ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንመለሳለን። በጸጥታ ለእርሱ ብቻ በመስገድ የእግዚአብሔር ቃል ከቃላችን ጋር እንዲዋሃድ እናደርጋለን። በእርሱ ፊት ብቻ በመንፈሱ እሳት መንጻት፣ መለወጥ እና መታደስ እንችላለን። ወንድሞቼ እና እህቶቼ ጌታች ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ እናክብረው!

ሁለተኛው ቃል ማገልገል የሚለው ነው። ማገልገል ማለት መውደድ ማለት ነው። በታላቁ ትእዛዝ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርን እና ባልንጀራን አንድ በማድረግ ፈጽሞ እንዳይለያዩ አድርጎአቸዋል። የዓለማችንን ጩሄት የማይሰማ እውነተኛ የሃይማኖት ልምድ ሊኖር አይችልም። ለባልንጀሮቻችን ተጨንቀን እንክብካቤን ሳናደረግን እግዚአብሔርን እንወደዋለን ማለት አንችልም። ያለበለዚያ ፈሪሳዊ የመሆን አደጋ ያጋጥመናል። ቤተ ክርስቲያናችንን ለማሳደግ የሚያግዙ ብዙ መልካም ሃሳቦች ሊኖሩን ይችላል። እግዚአብሔርን ማምለክ፣ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በፍቅር መውደድ፣ እነዚህ በሙሉ ታላቅ እና ዘላቂ የተሃድሶ መንገዶች መሆናቸውን እናስተውል። እግዚአብሔርን የምታመልክ እና የምታገለግል ቤተ ክርስቲያን ለመሆን፥ የቆሰለውን የሰው ልጅ እግር ማጥብ፣ አቅመ ደካሞችን መደገፍ፣ በኅብረተሰቡ የተገለሉ ድሆችን በፍቅር መቅረብ ያስፈልጋል። እግዚአብሔር ይህን እንድናደርግ ማዘዙን በመጀመሪያው ንባብ ሰምተናል።

ወንድሞቼ እና እህቶቼ! የጦርነት ግፍ ሰለባ የሆኑትን አስባለሁ፣ የስደተኞችን ስቃይ፣ የብቸኝነት ሕይወት የሚኖሩትን እና በስውር የድህነት ሕይወት የሚኖሩትን፣ የተጨቆኑትን እና ድምፅ የሌላቸውን ሰዎች አስባለሁ። ከጥሩ ቃላት እና ማራኪ ተስፋዎች በስተጀርባ የሚበዘበዙ ሰዎችን እና ይህ እንዳይከሰት ምንም ዓይነት ጥረት ያልተደረገላቸውን ሰዎች አስባለሁ። አቅመ ደካሞችን መበዝበዝ ከባድ ኃጢአት ነው። ወንድማማችነትን የሚያበላሽ እና ኅብረተሰቡን የሚጎዳ ከባድ ኃጢአት ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን፣ ልዩ እርሾ የሆነውን ቅዱስ ወንጌል ወደ ዓለም ማምጣት እንፈልጋለን። እግዚአብሔርን ማዕከል በማድረግ እና ከእርሱ ጋር በመሆን በተለይ እርሱ የሚወዳቸውን ድሆች እና አቅመ ደካሞችን ማስቀደም እንፈልጋለን።

ወንድሞቼ እና እህቶቼ! እንድንመኛት የተጠራነው ቤተ ክርስቲያን ይህች ናት። በኅብረተሰቡ መካከል ዝቅተኛ የሆኑ ወንድሞችን እና እህቶችን ጨምሮ የሁሉም አገልጋይ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ይህች ናት። ሞገስን የማትፈልግ ነገር ግን ሁሉን ሰው ያለ ልዩነት ተቀብላ የምታገለግል፣ የምትወድ እና ይቅር የምትል ቤተ ክርስቲያን ልትኖረን ይገባል። የምሕረት መሸሸጊያ እና በሮችዋ የተከፈቱባት ቤተ ክርስቲያን ልትኖረን ይገባል። ከቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል አንዱ የሆነው ጆን ክሪሶስተም በስብከቱ፥ “መሃሪ ሰው ለተቸገሩት መሸሸጊያቸው ነው። ከመርከብ አደጋ የተረፉትን የሚቀበል፥ ክፉዎችን ሆኑ ደጎችን ከአደጋ ነፃ ያወጣቸዋል። በችግር ውስጥ የሚገኙ ማንኛቸውንም ዓይነት ሰዎች ወደ መጠለያው ይቀበላቸዋል። አንተም እንደዚሁ በምድር ላይ በሰባራ የድህነት መርከብ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ስታይ ጭንቀታቸውን በመጋራት አግዛቸው እንጂ አትፍረድባቸው” በማለት ተናግሯል። (pauperem Lazarum, II, 5)

ወንድሞቼ እና እህቶቼ! የሲኖዶሱ ጠቅላላ ጉባኤ አሁን ተጠናቅቋል። በዚህ የመንፈስ ውይይት የእግዚአብሔርን ፍቅራዊነት በማጣጣም የወንድማማችነትን ውበት ተላብሰናል። እርስ በርሳችን አንዱ ሌላውን አዳምጠናል። ከሁሉም በላይ በተለያዩ አስተዳደጎቻችን እና ጭንቀቶቻችን መካከል መንፈስ ቅዱስን አዳምጠናል። የዚህ ሂደት ፍሬ ዛሬ አናየውም። ነገር ግን በአርቆ አስተዋይነት ከፊት ለፊታችን የሚከፈተውን አድማስ ለማየት እንጠባበቃለን። እግዚአብሔር ይመራናል፤ የበለጠ ሲኖዶሳዊ እና ሚሲዮናዊ ቤተ ክርስቲያን እንድንሆን  ይረዳናል። እግዚአብሔርን የምታመልክ፥ የዘመናችንን ሕዝቦች በሙሉ የምታገለግል፣ ሁሉም የሚያፅናና የወንጌል ደስታን ለማዳረስ የምትወጣ ቤተ ክርስቲያን እንድንሆን እግዚአብሔር ያግዘናል።

ወንድሞቼ እና እህቶቼ! በሲኖዶስ ጉባኤ ወቅት ስላደረጋችሁት እና ወደፊትም ለምታደርጉት ሁሉ አመሰግናችኋለሁ። አብረን በኅብረት ስላደረግነው ጉዞ፣ እርስ በእርስ በመደማመጥ ላደረጋችሁት የጋራ ውይይት ምስጋናዬን በመግለጽ፣ ለእግዚአብሔር በምናቀርበው አምልኮ እና ለባልንጀሮቻችን በምናደርገው አገልግሎት ማደግ እንድንችል ሁላችንም በጸሎቴ ላስታውሳችሁ እፈልጋለሁ። በደስታ ወደ ፊት እንጓዝ! እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን።

30 October 2023, 18:31