ፈልግ

የመስቀል ሽልማት ታዋቂ የዳኞች ቡድን ከሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ጋር ሆነው የመስቀል ሽልማት ታዋቂ የዳኞች ቡድን ከሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ጋር ሆነው 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ወጣት መሪዎች እንደ እግዚአብሔር ትልቅ ዓላማ ሊኖራቸው ይገባል አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሰሜን ጣሊያን ሚላኖ ከተማ ሊሚገኝ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በላኩት የማበረታቻ መልዕክት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን ወደ ራሱ ለመጥራት የሄደበትን መንገድ በመከተል መሪነትንም ራስን ከሌሎች በላይ ለማድረግ ሳይሆን ለአገልግሎት ዝቅ ማድረግን እንዲያውቁ በማሳሰብ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥቅምት 2/2016 ዓ. ም. ለወጣት መሪዎች በጻፉት መልዕክት፥ “ወጣቶች እንደ እግዚአብሔር ትላልቅ ዓላማዎች መኖራቸው አስፈላጊ ነው” ብለዋል። በሰሜን ጣሊያን ሚላኖ ከተማ በሚገኘው ቅዱስ ቄርሎስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተባባሪነት ለተዘጋጀው የወጣት መሪዎች ጉባኤ ቅዱስነታቸው መልዕክታቸውን የላኩት ዓርብ ጥቅምት 2/2016 ዓ. ም. እንደ ነበር ታውቋል።

ቅዱስነታቸው ለወጣት መሪዎች በላኩት መልዕክት፥ "በዚህ ጊዜ ዓለምን መለወጥ የሚችል እንዴት አስተዋጽዖ እንዴት ማድረግ እንደሚገባ ራስን መጠየቅ አስፈላጊ እና አዎንታዊ ነው” ብለዋል። "ማለምን ከማያቋርጡ አረጋውያን ጋር መገናኘት እና መወያየት አስፈላጊ ከመሆኑ በተጨማሪ፥ አረጋውያን ሕልምን እንዴት መፍታት እና እንዴት መገንዘብ እንደሚቻል ያግዛሉ” ብለው፥ ወጣቶች ሕልማቸውን ከእግዚአብሔር ሕልም ጋር ማስተያየት እንደሚገባ አስስበዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ የለውጥ አጋዥ ነው!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጉባኤው ተካፋዮች በላኩት መልዕክት የለውጥ ተዋናይ ለመሆን አንዱ አስፈላጊ እርምጃ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን ወደ ራሱ ለመጥራት የሄደበትን መንገድ ሳያቋርጡ ማወቅ ይገባል ብለዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ነገር እንደሚለውጥ እና እንደሚያድስ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን የዓለማችን ኃያላን መሪዎች ትላንትም ሆነ ዛሬ ካላቸው ሥልጣን የተለየ እንደሆነ ገልጸው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ክርስቶስ ነገሮችን አዲስ ለማድረግ የሚሄድበት መንገድ የተጋነነ ሳይሆኑ ነገር ግን የሚያነቃቃ፣ የሚያስጨንቅ ሳይሆን ነገር ግን ነጻ የሚያወጣ መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል። ወጣት መሪዎች ዕድገታቸው ራሳቸውን ከሌሎች በላይ ለማድረግ ሳይሆን እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ራስን ዝቅ በማድረግ እና በእርሱ በመተማመን ሌሎችን ማገልገል ሊሆን እንደሚገባ አደራ ብለው፥ ለዚህም ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

"መንፈሳዊ ስሜቶች"

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጉባኤው መሪ ሃሳብ አምስቱንም የስሜት ሕዋሳት በመጠቀም መልካም መሪ መሆን የሚል እንደሆነ በመጥቀስ፥ ይህም ብልህነት እንደሆነ እና እውነታ ከሃሳብ እንደሚበልጥ አስረድተዋል። ከእውነታ ጋር መገናኘት ግልጽነትን፣ ትኩረትን፣ ርህራሄን እና ሁለንተናዊ ስሜትን ከመጠየቅ በተጨማሪ መንፈሳዊ ስሜቶችን እንደሚያካትት ተናግረዋል። “እነዚህን ነገሮች የምነግራችሁ ተቋማችሁ ካቶሊካዊ ተቋም ስለሆነ እና ‘ካቶሊክ’ ማለት በሁሉም አቅጣጫ ለሰው ልጅ ግልጽ እና ሁሉን አቀፍ ራእይ ያለው በመሆኑ” በማለት አጥብቀው ተናግረዋል።

የመልዕክታቸው ማጠቃለያ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሰሜን ጣሊያን ሚላኖ ከተማ ለሚገኝ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የላኩትን የማበረታቻ መልዕክት ሲያጠቃልሉ፥ ወጣት መሪዎች ትምህርት ቤቱ ለሚሰጣቸው ዕድሎች ዋጋን እንዲሰጡት አደራ ብለው፥ ይህን ዕድል እንደ ቀላል መመልከት እንደሌለባቸው አሳስበዋል።

በዓለም ውስጥ የሚገኙ በርካታ እኩዮቻቸው በተለይም ሴት ልጆች የመማር ዕድል እንደሌላቸው እና ለመብታቸው እንኳ ቢሆን መቆም እንደማይችሉ ተናግረው፥ ወጣቶቹ የተሻለ ዓለምን ለመገንባት ላሳዩት ቁርጠኝነት አመስግነው ቡራኬያቸውን ከሰጡ በኋላ የጸሎት ዕርዳታቸውን በመጠየቅ መልዕክታቸውን አጠናቅቀዋል።

 

14 October 2023, 17:21