ፈልግ

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ምጣኔ ሃብታዊ ጽሑፍ የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ምጣኔ ሃብታዊ ጽሑፍ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ አሳታፊ እና ተንከባካቢ የኤኮኖሚ ጎዳናን መጓዝ እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ዓመት በአውታረ መረብ ማካይነት በሚካሄደው ዓመታዊ “የቅዱስ ፍራንችስኮስ የምጣኔ ሃብት” ስብሰባ ላይ ለሚሳተፉ ወጣት የምጣኔ ሃብት ጠበብት መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፥ የምጣኔ ሃብት ጠበብቱ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ የምጣኔ ሃብት ሥርዓቱ ፍትሃዊ እንዲሆን ለማድረግ በሚያደርጉትን ጥረት ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የ “ቅዱስ ፍራንችስኮስ የምጣኔ ሃብት” እንቅስቃሴን ለተቀበሉ ወጣት የምጣኔ ሃብት ጠበብት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኤኮኖሚያዊ ምኅዳሩን ለመቀየር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ያሉ ተቃርኖዎችን እና የተለያዩ አመለካከቶችን በማንሳት ተናግረዋል።

የተቃርኖዎች አንድነት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የተቃርኖዎች አንድነት” ጽንሰ-ሐሳብ በማስመልከት በሰጡት አስተያየት፥ እውነታው ብዙውን ጊዜ እንደ ትልቅ እና ትንሽ፣ ጸጋ እና ነጻነት፣ ፍትህ እና ፍቅር የመሳሰሉ የሚቃረኑ አስተሳሰቦችን ያቀፈ መሆኑን በማሰላሰል፥ አንዱን ጎን መርጠው ሌላውን ከማስወገድ ይልቅ ውጥረቱ የሚቀርበትን የውህደት አቅጣጫን የመፈለግ ምርጫን እንደሚደግፉ ገልጸዋል። ይህ አስተሳሰብ የምጣኔ ሃብታዊ ቅራኔዎችን በመጋፈጥ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ያግዘናል ብለዋል። ልዩነቶች እያደጉ ባለበት ዓለም ውስጥ ይህ አካሄድ ሚዛናዊነትን፣ ትብብርን እና ሁለቱም ወገኖች ለጋራ ጥቅም አብረው ሊቆሙ እንደሚችሉ እውቅና መስጠትን ይጠይቃል ብለዋል።

ሌሎችንም እንዲያካትቱ የቀረበ ጥሪ

ወጣት የምጣኔ ሃብት ጠበብት አመለካከቶቻቸውን እንዲያሰፉ እና ለተለያዩ ድምፆች በተለይም ለረጅም ጊዜ በማኅበረሰቡ ለተገለሉት ቦታ እንዲሰጣቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሳስበው፥ ግንዛቤአቸው ትኩረታቸውን ከቁሳዊ ነገሮች ትርጉም ወዳለው ማኅበራዊ ግንኙነት፣ ከሃብት ክምችት ወደ ፍትሃዊ ክፍፍል እና ከረቂቅ አስተሳሰብ ወደ ተጨባጭ እውነታዎች ሊያሸጋግር እንደሚችል ተናግረዋል።በኢኮኖሚያዊ ፅንሰ-ሀሳብ እና ተግባር ውስጥ ሁሉም ድምፆች ዋጋን እና ተሰሚነትን በማግኘት ወደ መካተት ጥልቅ ለውጥ መድረስ እንደሚገባ ተመልክተዋል።

የጉዞ ላይ ምጣኔ ሃብት

ከኢየሱስ ክርስቶስ እና ከደቀ መዛሙርቱ ልምድ በመነሳት የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ "የጉዞ ላይ ምጣኔ ሃብት” አስፈላጊነትን በማጉላት፥ ይህ ጽንሰ-ሀሳብ እምነትን፣ ተጋላጭነትን እና በጉዞ ወቅት በሌሎች ላይ ጥገኛነትን መሆንን እንደሚያጎላ አብራርተዋል። የምጣኔ ሃብት ትምህርት ከሌሎች የትምህርት ዘርፎች የተነጠለ ሳይሆን ነገር ግን ከሌሎች ዘርፎች ጋር በመቆራኘት ተግባራዊነትን እና ተሳትፎን የሚጠይቅ መሆኑን አስታውሰዋል።

እንደ መንፈሳዊ ንግደት በተግዳሮቶች እና በተለያዩ ውጣ ውረዶች የተከበበ በመሆኑ፥ የጋራ ጥቅምን ለማስከበር በርትቶ መሥራት እና መልፋት እንደሚያስፈልግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወጣት የምጣኔ ሃብት ጠበብት አሳስበዋል። መንፈሳዊ ንግደት ሰላም ፈጣሪ እና በምጣኔ ሃብታዊ መስክ የፍትህ ተሟጋቾች እንዲሆኑ የሚያበረታታ መሆኑን አስረድተዋል።

ትዕግስት እና ጽናት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ላይ እንደተናገሩት፥ ለውጡ ጊዜ የሚወስድ እና ብልሃትን የሚጠይቅ እንደሆነ ግልጽ ነው ብለው፥ አዳዲስ ምጣኔ ሃብታዊ አቀራረቦችን ከነባር ሥርዓቶች ጋር ማቀናጀት እንደሚቻል፥ ነገር ግን ይህ ሊያደናቅፈን እንደማይገባ፥ ጥረታችን ቀስ በቀስ እንዲዳብር እና ዘላቂ ግንኙነቶችን ለመመሥረት ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳደግ ትዕግስት እና ጽናት ሊኖር ይገባል” ብለው፥ የበለጠ ፍትሃዊ እና ሁሉን አቀፍ ምጣኔ ሃብታዊ ዓለምን ለማየት ጽናት ያላቸው በጎ ምግባሮች ሊኖሩ እንደሚገባ አስረድተዋል።

07 October 2023, 17:29