ፈልግ

የብጹ ዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ የብጹ ዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የጻፉት አዲስ መጽሐፍ ለንባብ መብቃቱ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ቅዱስ እንጂ ዓለማዊ አይደለም” በሚል አርዕስት የጻፉት አዲስ መጽሔፍ ለንባብ መብቃቱን የቫቲካን አሳታሚ ድርጅት አስታውቋል። አዲሱ መጽሐፍ ቅዱስነታቸው ከዚህ በፊት ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1991 ዓ. ም. “የእግዚአብሔር ጸጋ ከውስጣዊ ሙስና ያድነናል” በሚል አርዕስት የጻፉትን የመጀመሪያን ርዕስ እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በነሐሴ 2023 ዓ. ም. ለሮም ሀገረ ስብከት ካኅናት ያስተላለፉትን መልዕክት በማካተት በእንግሊዝኛ ትርጉም መታተሙን አሳታሚ ድርጅቱ ገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በዚህ መሐፋቸው፥ የክርስትና ሕይወት ትግል ያለበት፣ እራስን ለሌሎች ዝግ የማድረግ ፈተናን ለማሸነፍ እና ዘወትር ደስተኞች እንድንሆን የሚፈልገው የእግዚአብሔር ፍቅር በውስጣችን እንዲኖር ለማድረግ የሚደረግ ውስጣዊ ውጊያ መሆኑን አስረድተዋል። “እግዚአብሔር በውስጣችን ሆኖ ድል እንዲንነሳ ስንፈቅድ ልባችን በደስታ ስለሚሞላ እና ሕይወታችንም በማያልቅ ብርሃን ስለሚበራ ውጊው የሚያምር ነው” ብለዋል። “የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ሆነን የምናደርገው ውጊያ ጣዖትን የሚመስል ዓለማዊነትን በክርስትና ሕይወት በመሸፈን የምናደርገው ውጊያ፥ ከሁሉ በፊት ከመንፈሳዊ ዓለማዊነት ጋር የሚደረግ ውጊያ ነው” በማለት አስረድተዋል።

ምንም እንኳን በቅድስና ቢገለጽም፣ ፍጻሜው ጣዖት ስለሆነ፥ ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ሕይወታችንን እና የዓለም ታሪክን ነጻ እንደሚያወጣ የሚያውቅ በመሆኑ የሥጋዊ ምኞታችን ሰለባ ያደርገናል ብለዋል። ይህ በመሆኑ፥ ዓለማዊ መንፈሳዊነትን በርተትን መታገል እንዳለብን በማሳሰብ፥ ነገር ግን ውጊያችን ከንቱ ወይም ያለ ተስፋ እንዳልሆነ ገልጸዋል። ውጊያችን የኃጢአትን ኃይል በሞቱ ባሸነፈው በኢየሱስ ክርስቶስ ድልን በመቀዳጀት በትንሣኤው አዲስ ሰዎች እንድንሆን አስችሎናል ብለዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ድል፥ከሁሉ አስቀድሞ መስቀሉ ከክፉ ነገር ስለሚሰውረን ስም አለው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ፍቅሩ ወሰን እንደሌለው፣ ትሁት እና ቆራጥ መሆኑንም አስረድተዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ጥርጣሬ በማይዘን ሁኔታ በመስቀል ላይ በውርደት እስኪሞት ድረስ እንደወደደን እና እጆቹ ለኃጢአተኞች እንኳን ሳይቀር ክፍት መሆናቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰው፥ ይህ ዘላለማዊ ፍቅርሩ የክርስቲያኖችን እና የቤተ ክርስቲያንን ሕይወት እንደሚመራ ተናግረው፥ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል የእምነት ምርጫዎች ሁሉ መመዘኛ እንደሆነም አስረድተዋል።

በአልጄሪያ የኦራን ሀገረ ስብከት ጳጳስ የነበሩት ብጹዕ አቡነ ፒዬር ክላቬሪ ያቀረቡት ስብከት የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ቤተ ክርስቲያን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በሚገባ ካልቀረበች እንደምትሞት አምናለሁ” ያሉትን አስታውሰው፥ ጥንካሬ እና ኃይል፣ ተስፋ እና የክርስቲያን ሕይወት እና የቤተ ክርስቲያን ፍሬያማነት የሚመጣው ከሌላ ሳይሆን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ይበልጥ በመቅረብ እንደሆነ አስረድተዋል።

“የቀረው ሁሉ በዓይናችን ውስጥ እንደ ጭስ የሚመላለስ ዓለማዊ ቅዠት ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ቤተ ክርስቲያን በሃያላን መካከል እራሷን እንደ ሃያል ከቆጠረች፥ እራሷን እንደ አንድ ሰብዓዊ ድርጅት ከቆጠረች ወይም ለታይታ ብቻ እንደተመሠረተ ወንጌላዊ እንቅስቃሴ አድርጋ ከተመለከተች እራሷን የካደች እንደምትሆን አስረድተዋል። ብርሃኗ እጅግ የሚያንጸባርቅ ቢሆንም፥ በመኃልየ መኃልይ መጽሐፍ ውስጥ እንደተጠቀሰው፥ ‘እንደ ሞት የበረታ” ቢሆንም ነገር ግን በእግዚአብሔር የፍቅር እሳት የማያቃጥል መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ ጊዜያት የታተሙ ሁለት ጽሑፎችን ለመሰብሰብ የፈለጉበት ምክንያት አንደኛው፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1991 ዓ. ም. የቦነስ አይረስ ከተማ ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ጊዜ ሙስናን እና ኃጢአትን በማስመልከት የጻፉትን፥ ሁለተኛው ለሮም ሀገረ ስብከት ካህናት የላኩት መልዕክት በአንድ መጽሐፍ ውስጥ ለማካተት መፈለጋቸውን ተናግረዋል።

እነዚህን መልዕክቶች አንድ ላይ በማድረግ ይፋ ለማድረግ የፈለጉትም፥ ምዕመናን ነቅተው በመጠበቅ እና ማንኛውንም ዓይነት መንፈሳዊ ዓለማዊነትን በመቃወም በጸሎት እንዲበረቱ እና በብርቱ እንዲዋጉት እግዚአብሔር ለመላው ቤተ ክርስቲያኑ የላከው ታላቅ ጥሪ እንደሆነ ስለተሰማቸው መሆኑን ገልጸዋል።

“የመንፈሳዊ ዓለማዊነት ውጊያ ስም አለው ያሉት” ቅዱስነታቸው፥ ስሙም ቅድስና እንደሆነ በመግለጽ፥ ቅድስና አንድ ሰው ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የደረሰበት የበረከት ደረጃ አለመሆኑን አስረድተዋል። ቅድስና ከራስ ችሮታ በሚመጣ አመክንዮ እንድንመካ እና ራሳችንን እንደቻልን በማሳመን የሚያሞኝን ጠላት በመቃወም ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ጋር ሳንታክት እና ሳናቋርጥ እንድንቆም የሚያደርገን  ፍላጎት ነው ብለዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐ. 15:5 ላይ፥ “ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም” ያለውን የጠቀሱት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ቅድስና እግዚአብሔር ከእኛ ለሚጠይቀው እና በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ለምናደርገው ጥረት የበለጠ ክፍት እንድንሆን የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል። አባ አልፍሬድ ዴልፕ የተባሉት፥ “እግዚአብሔር በእውነታው በኩል ያቅፈናል” በማለት የጻፉትን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ የዕለት ተዕለት ሕይወታችን “ራሳችንን እንችላለን” ከሚያሰኘን ስሜት ለሚያድነን እግዚአብሔር ቦታ የምንሰጥበት፥ የሎዮላ ቅዱስ ኢግናጢዮስ ፥ የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ወደ ሙሉ እና የተረጋጋ ደስታ የሚውስደን ነው በማለት መናገሩን አስታውሰዋል።

እነዚህን ጽሑፎች ለአንባቢያን ያቀረቡት፥ በሕይወታቸው እና በቤተ ክርስቲያን ሕይወት በማሰላሰል፥ በእግዚአብሔር ኃይል በመታገዝ ለምናመጣው መታደስ ክፍት እንድንሆን፥ ፀጥ ብለን ሳንቀመጥ እና ባገኘነው ሳንረካ እርሱን ዘወትር እንድንፈልግ መጠየቁን በማመን፥ ምቹ የሆነ የውሸት እርግጠኝነት ግድግዳ ሳያግደን ነገር ግን በቅድስና መንገድ መጓዝ እንደሚገባ ለማሳሰብ መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአዲሱ መጽሐፋቸው ውስጥ ገልጸዋል። 

 

07 October 2023, 17:16