ፈልግ

በማዕከላዊ ጋዛ ሰርጥ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት የወደመው መስጊድ እና የቤቶች ፍርስራሽ በማዕከላዊ ጋዛ ሰርጥ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት የወደመው መስጊድ እና የቤቶች ፍርስራሽ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት አገር የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ጥቅምት 18/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ያደረጉትን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ማጠቃለያ ላይ ባደርጉት ንግግር፥ በቅድስት አገር በተለይም ጋዛ ውስጥ በሰዎች ላይ የሚፈጸም ግፍ እንዲቆም፣ እንዲሁም በሃማስ ታጣቂዎች የተያዙ የእስራኤል ታጋቾች እንዲፈቱ በማሳሰብ ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በቅድስት አገር ውስጥ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበው፥ እሑድ ጥቅምት 18/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ባቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ማጠቃለያ ላይ፥ በፍልስጤም እና በእስራኤል መካከል ያለው አሳሳቢ ጦርነት እንዲያበቃ ምዕመናን በሙሉ የጸሎት ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ በማለት አደራ ብለዋል። ቅዱስነታቸው በተለይም ሰብዓዊ ዕርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ እና በሐማስ ታጣቂዎች የታገቱት እስራኤላውያን እንዲፈቱ በማለት ጠይቀዋል።

በጋዛ ያለው ቀውስ ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ መባባሱ ሲገለጽ፥ ሃማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ካደረሰበት ከመስከረም 26/2016 ዓ. ም. በኋላ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በወሰደችው የአየር እና የምድር የአጸፉ ምላሽ ከ7,200 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተረጋግጧል።

ቅዱስነታቸው፥ በኢየሩሳሌም የፍራንችስካውያን ገዳም አለቃ የሆኑት አባ ኢብራሂም ፋልታስ በቅርቡ በጣሊያን ቴሌቭዥን ቀርበው፥ “ተኩስ ይቁም!” ሲሉ ማሳሰባቸውን በማስታወስ፥ “እኛም እንደ አባ ኢብራሂም ተኩስ እንዲቆም በማሳሰብ እናሳስባለን” በማለት፥ ጦርነት ምን ጊዜም ሽንፈት መሆኑን ተገንዝበው የሐማስ ታጣቂዎች እና የእስራኤል ጦር ሠራዊት በመካከላቸው የሚደረገውን ጦርነት እንዲያቆሙ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

 

30 October 2023, 13:19