ፈልግ

የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በሂደት ላይ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በሂደት ላይ   (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ምዕመናን ለሰላም እና ለሲኖዶሳዊ ጉባኤ ጸሎት እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረቡ

የጥቅምት ወር ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ የመቁጠሪያ ጸሎት የሚደረግበት እንደሆነ ያሳታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ መላው ካቶሊካዊ ምዕመናን በሚገኙበት የዓለም ዳርቻ በሙሉ ለዓለም ሰላም እንዲጸልዩ ግብዣቸውን አቅርበው፥ በሂደት ላይ የሚገኘውን የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ለመንፈስ ቅዱስ አደራ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እሑድ መስከረም 27/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን እና መንፈሳዊ ነጋዲያን ጋር ሆነው ካቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ ባደረጉት ንግግር፥ የጥቅምት ወር ለተልእኮ እና ለመቁጠሪያ ጸሎት የተሰጠ ወር መሆኑን አስታውሰው፥ በጦርነት እና በግጭት ውስጥ ለሚገኙ በርካታ የዓለም አገሮች የሰላም ስጦታን ከልጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ እንድታማልድ ምእመናን ሳይሰለቹ ጸሎታቸውን እንዲያቀርቡ ጋብዘው፥ በተለይም በየቀኑ ብዙ ስቃይ የሚደርስባትን ዩክሬንን በጸሎታቸው እንዲያስታውሷት አደራ ብለዋል።

የሲኖዶስ ጉባኤን በጸሎት ማገዝ ይገባል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የሲኖዶስ ጉባኤን በመከታተል ላይ የሚገኙትን፣ በተለይም የጸሎት ድጋፍ በማድረግ ላይ ለሚገኙት በሙሉ ምስጋናቸውን በማቅረብ፥ በሂደት ላይ የሚገኘው የሲኖዶስ ጉባኤ የመደማመጥ፣ መንፈስ ቅዱስ የሚናገረውን የማካፈል እና የወንድማማችነት መንፈስ ያለበት ጉባኤ” እንደሆነ በማስረዳት፥ ሁሉም ምዕመናን ለመንፈስ ቅዱስ አደራን እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

 

09 October 2023, 17:28