ፈልግ

ከሃማስ ታጣቂዎች በእስራኤል ላይ የተፈጸመ የሮኬት ጥቃት ከሃማስ ታጣቂዎች በእስራኤል ላይ የተፈጸመ የሮኬት ጥቃት  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በእስራኤል እና ፍልስጤም ሰላም እንዲሰፍን ጸሎት አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እሑድ መስከረም 27/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን እና መንፈሳዊ ነጋዲያን ጋር በእስራኤል እና ፍልስጤም ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ጸሎት አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባደረጉት ንግግርም፥ በሽብር እና በጦርነት ምንም ዓይነት መፍትሄ እንደማይገኝ፥ ነገር ግን ለብዙ ንፁሃን ሰዎች ሞት እና ስቃይ ብቻ የሚያተርፍ መሆኑን በመረዳት ሁለቱም ወገኖች የጦርነት ጥቃቶችን እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርበዋል። 'ጦርነት ሁሌም ሽንፈት ነው!' በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አጥብቀው ተናገረዋል።

እሑድ ዕለት ካቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ ባደረጉት ንግግር፥ ከእስራኤል የሚወጡ የቅርብ ጊዜ ዜናዎችን በፍርሃትና በሐዘን መከታተላቸውን የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ዓመፅ እጅግ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በመቶዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ሞት እና ጉዳት ማድረሱን መመልከታቸውን ተናግረው፥ ለተጎጂ ቤተሰቦች የተሰማቸውን ሐዘን በመግለጽ፥ ለሰዓታት ያህል በሽብር እና በጭንቀት ውስጥ የሚገኙትን በጸሎታቸው ማስታወሳቸውን በመግለጽ ሁሉም ሰው ለእስራኤል እና ለፍልስጤም ሰላም እንዲጸልዩ አደራ ብለዋል።

በእስራኤል እና በፍልስጤም ውስጥ የተከሰተው ብጥብጥ

የፍልስጤም ሃማስ ታጣቂዎች ቅዳሜ መስከረም 26/2016 ዓ. ም. ድንገተኛ ጥቃት በመሰንዘር በሺዎች የሚቆጠሩ ተወንጫፊ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል በመተኮስ በቅድስት አገር አዲስ ብጥብጥ መቅቀስቀሱ ታውቋል። እስራኤልም ወዲያው የአጸፋ የአየር ጥቃቶችን የፈጸመች ሲሆን፥ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታናሁ አገራቸው ጦርነት ውስጥ መሆኗን ገልጸዋል። በውል ያልተረጋገጠ ዘገባዎች በደቡብ እስራኤል እና በጋዛ ሰርጥ ከ 400 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን እና በደርዘን የሚቆጠሩ መማረካቸውን አስታውቋል። አንዳንድ የእስራኤል ምንጮች እንደገለፁት 300 የሚሆኑ እስራኤላውያን መገደላቸውን እና በደርዘን የሚቆጠሩ ደግሞ ታፍነው መወሰዳቸውን አስታውቀዋል።

የላቲን ፓትርያርክ አመጹ እንዲቆም ጠይቀዋል

ኢየሩሳሌም ውስጥ የላቲን ፓትርያሪክ ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፥ የብዙ ሕይወት መጥፋት እና አሳዛኝ ሁኔታዎች በፍልስጤማውያን እና በእስራኤላውያን ቤተሰቦች መካከል የበለጠ ጥላቻን እና መለያየትን ሊፈጥር እንደሚችል፥ ይህም በአካባቢው መረጋጋት እዳይኖር እንደሚያደርግ አስረድቷል። መግለጫው አክሎም፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና የሃይማኖት መሪዎች ሁኔታውን ለማርገብ፣ መረጋጋትን ወደነበረበት ለመመለስ እና የክልሉን ሕዝቦች መሠረታዊ መብቶችን ለማረጋገጥ የተቻላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቋል።

ለግጭቱ መፍትሄ ሊኖረው ያስፈልጋን

የፓትርያርኩ ጽሕፈት ቤት፥ በቅድስት አገር በተለይም በኢየሩሳሌም የሚገኙ ቅዱሳን ቦታዎችን በተመለከተ በነበሩበት እንዲቆዩ የሚለውን ደንብ የማክበር አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥቶ፥ በቅድስት አገር ለፍልስጤም-እስራኤል ግጭት ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ መፍትሄን መፈለግ አስቸኳይ ፍላጎት ያለበት መሆኑን የፓትርያርክ ጽሕፈቤት ገልጾ፥ “ኢየሩሳሌም ለሕዝቦች በሙሉ የጸሎት ሥፍራ እንድትሆን የዓለም መሪዎች ለሰላም እና ለስምምነት ተግባራዊነት የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት በርትቶ እንዲቀጥሉ ጸሎቱን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በማቅረም መግለጫውን ደምድሟል።

09 October 2023, 17:33