ፈልግ

በሊዝበን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን የተዘጋጀ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በሊዝበን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን የተዘጋጀ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ምዕመናን ስለ ሰላም እና ስለ ሲኖዶስ ጉባኤ ጸሎት እንዲያደርጉ ጠየቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እሑድ መስከረም 20/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ካቀረቡ በኋላ ንግግር አድርገዋል። ቅዱስነታቸው ከጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ቀጥለው ባደረጉት ንግግር፥ እሑድ መስከረም 20/2016 ዓ. ም. እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር የጥቅምት ወር የገባበት ዕለት መሆኑን በማስታወስ፥ ወሩ ስለ ሰላም እና ስለ ተልዕኮ የመቁጠሪያ ጸሎት የሚደረግበት ወር እንደሆነ ገልጸው፥ መላው ካቶሊክ ምዕመናን በዚህ ወር ጸሎት እንዲያቀርቡ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው በተጨማሪም ዩክሬንን ጨምሮ ጦርነት በተከሰቱባቸው አካባቢዎች ሰላም እንዲወርድ፥ እንዲሁም በቫቲካን ከመስከረም 23 እስከ ጥቅምት 18/ 2016 ዓ. ም. ድረስ የሚካሄደውን የሲኖዶስ ጉባኤ በጸሎት እንዲያስታውሱት አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለጸሎት ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመልዓከ እግዚአብሔር ጸሎት ካቀረቡ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር የጥቅምት ወር ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ የመቁጠሪያ ጸሎት የሚቀርብበት ወር መሆኑን በማስታወስ፥ “በጦርነት ስቃይ ውስጥ በሚገኙ፥ በዩክሬን እና ሌሎች አገራት ሰላም እንዲሰፍን እንዲሁም ለተልዕኮ እንጸልይ" ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በዚህ መልዕክታቸው፥ ምዕመናን በሙሉ የመቁጠሪያ ጸሎት የሚያስገኘውን ፍሬ በመረዳት፥ከእመቤታች ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር በመሆን፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ምስጢራት ላይ ማሰላሰል እና የቤተ ክርስቲያን እና የዓለም ወቅታዊ ጥያቄዎች እንዲመለሱ በመለመን የመቁጠሪያ ጸሎት ውበትን እንዲለማመዱ አሳስበዋል።

መላው ምዕመናን ለሰላም እና ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ስኬታማነት ጸሎት እንዲያደረጉ የጠየቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በቫቲካን ከመስከረም 23 እስከ ጥቅምት 18/ 2016 ዓ. ም. ድረስ የሚካሄደውን የሲኖዶስ ጉባኤን አስታውሰው፥ በቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት ላይ የሚካሄደውን የሲኖዶስ ጉባኤ በጸሎት እንድንደግፈው አደራ አብለዋል።

 

02 October 2023, 17:36