ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ኃጢአተኛ ሰው ዘወትር የመዳን ተስፋ እንዳለው ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ መስከረም 20/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በዕለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው ለምዕመናኑ ባቀረቡት ስብከት፥ ኃጢአተኛ ሰው ዘወትር የመቤዠት የመዳን ተስፋ ያለው መሆኑን ገልጸዋል። ክቡራት ክቡራን አድማጮቻችን፥ ቅዱስነታቸው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን በዕለቱ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል በማስተንተን ያቀረቡትን ስብከት ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ዛሬ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል ስለ ሁለት ልጆች ይናገራል። አባታቸው በወይን አትክልት ሥፍራ ለሥራ እንዲሄዱ ጠየቃቸው። (ማቴ. 21፡28-32) ከመካከላቸው አንዱ 'እሽ' ብሎ የአባቱን ጥያቄ ቢቀበልም ነገር ግን ሳይሄድ ይቀራል። ሌላው ግን አልሄድም ካለው በኋላ በመልሱ ይጸጸትና ለመሄድ ይወስናል።

ስለ እነዚህ ሁለት ልጆች ባህሪ ምን ማለት እንችላለን? ወደ አእምሯችን ቶሎ የሚመጣ ነገር ቢኖር፥ በወይን አትክልት ሥፍራ መሥራት መስዋዕትነትን እንደሚጠይቅ እና ዋጋንም እንደሚያስከፍል እገነዘባለን። ሁለቱ ልጆች የአባታቸው ወራሾች መሆናቸው መልካም መሆኑን ቢያውቁትም ወደ ወይን አትክልት ሥፍራ ሄደው የመሥራት ወይም ያለመሥራት ሃሳብ እንዲሁ የሚመጣ አይደለም። ነገር ግን እዚህ ላይ ችግሩ፥ እነዚህ ሁለቱ ልጆች ከአባታቸው እና ከራሳቸው ጋር ባላቸው ቅንነት ወደ ወይን አትክልት ሥፍራ ሄደው ለመሥራት ወይም ላለመሥራት ካላቸው ፍላጎት ጋር የተገናኘ አይደለም። ምንም እንኳን የሁለቱ ልጆች ባህሪ እንከን ባይጠፋበትም አንዱ ሲዋሽ ሌላኛው ግን ቢሳሳትም ቅንነቱን ጠብቋል።

'እሽ' ብሎ የአባቱን ትዕዛዝ ከተቀበለ በኋላ ሳይሄድ የቀረውን ልጅ እንመልከት። ይህ ልጅ የአባቱን ፈቃድ ማድረግ አይፈልግም። ከዚህ በተጨማሪም ሊወያይበትም ሆነ ስለ ጉዳዩ መነጋገርም ፈጽሞ አይፈልግም። ስለዚህ ከእሽታው በስተጀርባ በሐሰት ፈቃደኝነት ለጊዜው ስንፍናውን መሰወር ፈልጓል። ይህ ልጅ ግብዝ ነው። ግጭት ሳይፈልግ፥ ነገር ግን አባቱን በማጭበርበር እና በማታለል፥ አልሄድም ብሎ ከተመለሰው ልጅ በባሰ መልኩ አባቱን አንቋሸሸው። እንደዚህ ዓይነት ባህሪ ያላቸው ሰዎች ችግራቸው ኃጢአተኞች ሳይሆኑ ነገር ግን የተበላሹ ናቸው። ምክንያቱም ምንም ዓይነት ግልጽ የሆነ ውይይት ሳያደርጉ ወይም ምላሽ ሳይሰጡ ለመሸፋፈን እና እምቢተኝነታቸውን ለመደበቅ የሚፈልጉ ናቸው።

'አልሄድም' ካለ በኋላ የሄደው ሌላኛው ልጅ ግን ቅን ነው። ይህ ልጅ ፍጹም አይደለም ነገር ግን ቅን ነው። ከዚህ ልጅ “እሽ” የሚል ምላሽ መስማት ጥሩ ነበር። ያ አልሆነም። ነገር ግን ቢያንስ እምቢተኝነቱን በተወሰነ መልኩ በድፍረት እና በግልፅ አሳይቷል። ማለትም ለባህሪው ሃላፊነት መውሰዱን በግልጽ አሳይቷል። ከዚያም ስህተት መሥራቱን እስኪረዳ እና እርምጃን እስኪወስድ ድረስ እራሱን በታማኝነት ጠይቋል። ይህ ልጅ ኃጢአተኛ ነው ማለት እንችላለን፤ ነገር ግን አልተበላሸም።

'ይህ ልጅ ኃጢአተኛ ነው። ነገር ግን አልተበላሸም!' የሚለውን ልብ እንበል። ኃጢአተኛ ሰው ዘወትር የመቤዠት ወይም የመዳን ተስፋ አለው። ለብልሹ ሰው ግን በጣም ከባድ ነው። እንደውም የተበላሸ ሰው የውሸት እሺታው የሚያምር ነገር ግን ግብዝነት ያለበት ነው። የፊት ገጽታው እና የለመደው የውሸት ማስመሰል፣ ከጀርባው በህሊና ጭንቀት ተሸፈነ ነው። ግብዞች ብዙ ክፋትን ይሠራሉ! ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ኃጢአተኞች ነን? አዎ! ሁላችንም ኃጢአተኞች ነን። ነገር ግን የተበላሽን አይደለንም!

እስቲ አሁን ደግሞ ወደ እራሳችን ተመልሰን በዚህ ሁሉ መካከል እራሳችንን አንዳንድ ጥያቄዎችን እንጠይቅ። ሐቀኛ እና ለጋስ የሆነ ሕይወት ለመኖር ችግር ሲያጋጥመን፣ እራስን ለእግዚአብሔር ፈቃድ አሳልፎ ለመስጠት ችግር ሲያጋጥመን፣ ምንም እንኳን ዋጋ ቢያስከፍለንም በየቀኑ “አዎ ወይም እሽ” ለማለት ፈቃደኞች ነን? በኃጢአት ውስጥ ስንወድቅ ያሉብንን ችግሮች፣ ስህተቶች እና ድክመቶች ወደ እግዚአብሔር ፊት ቀርበን በቅንነት እንናገራለን? “አይሆንም ወይም አሻፈረኝ” ካልን በኋላ ተመልሰን የአዎንታ ምላሽ እንሰጣለን? ይህን በማስመልከት ከእግዚአብሔር ጋር እንናገራለን? ስህተት ስንሠራ ንስሐ ለመግባት እና አካሄዳችንን ለመለወጥ ፈቃደኞች ነኝ? ወይስ ሁሉም ነገር ደህና እንደሆነ በማስመሰል ጭንብል ለብሰን እንጓዛለን? እሳችንን መልካም እና ጻድቅ ለማስመሰል እንጥራለን? እንደማንኛውም ሰው ኃጢአተኛ ነኝ ወይስ በውስጤ የተበላሸ ነገር አለ? ኃጢአተኞች ነን? አዎ! ሁላችንም ኃጢአተኞች ነን። ነገር ግን የተበላሽን አይደለንም። ይህን መርሳት የለብንም።

የቅድስና መስታዎት የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅን ክርስቲያኖች እንድንሆን ትርዳን።”

02 October 2023, 17:25