ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “እግዚአብሔር ለኛ ካሳየን ፍቅር ልንማር ይገባል” አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እሑድ ጥቅምት 18/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ቃለ ምዕዳንን አካፍለዋል። በማቴ. 22:34-40 ላይ በተጻፈው የወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ባቀረቡት ቃለ ምዕዳን፥ እግዚአብሔር ለኛ ካለን ፍቅር ልንማር ይገባል ብለዋል። ክቡራት ክቡራን፥ ቅዱስነታቸው ያቀረቡትን ቃለ ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው ቀርቧል:-

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፥ እንደምን አረፈዳችሁ! ዛሬ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል ከሁሉ ስለሚበልጥ ትዕዛዝ ይነግረናል (ማቴ. 22፡34-40)። አንድ የሕግ መምህር ኢየሱስን ሊፈትነው ፈልጎ እንዲህ ሲል ጠየቀው፥ ‘መምህር ሆይ! ከሕግ ማንኛይቱ ትዕዛዝ ትበልጣለች?’ ኢየሱስም ስለ ታላቁ የፍቅር ትእዛዝ እንዲህ በማለት መለሰ፡- ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ሐሳብህ ውደድ…፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ’ (ቁ. 37 ፣ 39)። ‘ታላቂቱ እና የመጀመሪያይቱ ትዕዛዝ ይህች ናት፤ ሁለተኛይቱም ይህችን የምትመስል ናት፤ እርሷም:- ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል ናት’ አለው። እግዚአብሔርን መውደድ እና ባልንጀራን መውደድ ሁለቱ የማይነጣጠሉ ናቸው።  በመሆኑም አንዴ በዚህ ላይ እናሰላስል።

የመጀመሪያው:- እግዚአብሔርን መውደድ እንደሚቀድም በማስገንዘብ፥ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንደወደደን እና እንደሚራራልን (ዮሐ. 4፡19)፣ ምሕረት ሊሰጠን ዘወትር ቅርብ እንደሆነ፥ ርህሩህ እና አዛኝ ጌታ እንደ ሆነ ያስገነዝበናል። አንድ ሕፃን መውደድን ከእናቱ እና ከአባቱ እቅፍ እንደሚማር እኛም መውደድን በእግዚአብሔር እቅፍ ውስጥ  ሆነን እንማራለን። ‘ነፍሴን አሳረፍኳት፥ የእናቱንም ጡት እንዳስተውት ሕጻን ዝም አሰኘኋት’ (መዝ. 131፡2)።

በእግዚአብሔር ክንዶች ውስጥ እንደዚህ ሊሰማን ይገባል። በእግዚአብሔር እቅፍ ውስጥ ሆነን የእርሱን ፍቅር እንማራለን። በእርሱ እቅፍ ውስጥ ስንሆን ራሳችንን በልግስና እንድንሰጥ የሚገፋፋ ፍቅር ያጋጥመናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት ወደ ፍቅር የሚወስድ ኃይል እንዳለው በማስታወስ ሲናገር:- ‘አንዱ ስለ ሁሉ እንደ ሞተ እርግጠኞች በመሆናችን፥ የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናል...’   (2ቆሮ. 5፡14)። ሁሉም ነገር የሚመነጨው ከእርሱ ነው። ይህ የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር በውስጣችን ከሌለ ሌሎችን በእውነት መውደድ አንችልም።

ከፍቅር ትዕዛዙ የሚመጣው ሁለተኛው ገጽታ:- እግዚአብሔርን መውደድ ባልንጀራን ከመውደድ ጋር ይገናኛል። ይህ ማለት ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በመውደድ የእግዚአብሔርን ፍቅር መልሰን ለሌሎች እንገጻለን ማለት ነው። የእግዚአብሔርን ፍቅር ለሌሎች የማሳየቱ ዋናው ነጥቡ:- ለማናየው እግዚአብሔር ያለንን ፍቅር በምናያቸው ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በኩል እንገልጻለን። ‘ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔር ሊወድ አይችልም’ (1ዮሐ. 4 20)።

አንድ ቀን የካልካታዋ ቅድስት ቴሬዛ፣ ዓለምን ለመቀየር ምኞት ያላት እንደሆነ ተጠይቃ ስትመልስ፥ ‘አይ! ዓለምን እለውጣለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም። ነገር ግን የእግዚአብሔር ፍቅር እንዲገለጽ የንፁህ ውሃ ጠብታ መሆን ብቻ ነው የምፈልገው’ በማለት መለሰች። ትንሿ ቅድስት ተሬዛ በዚህ መንገድ  የውሃ ጠብታን የሚያህል የእግዚአብሔር ፍቅር ለሌሎች በመግለጽ በርካታ መልካም ነገሮችን ማድረግ የቻለችው።

አንዳንድ ጊዜ ቅድስት ተሬዛን እና ሌሎች ቅዱሳንን በመመልከት ልንመስላቸው የማንችላቸው ሰዎች እንደሆኑ ልናስብ እንችላለን።  ስለዚያች ትንሽ ጠብታ ውሃ ደግመን እናስብ። ትንሽ ፍቅር ብዙ ነገርን ሊቀይር ይችላል። ይህ እንዴት ተግባራዊ ሊሆን ይቻላል? የመጀመሪያውን እርምጃ መውሰድ መልካም ነው። ስለምንዘነጋ ነው እንጂ አንዳንድ ጊዜ እርምጃን ቀድሞ መውሰድ ቀላል አይደለም። ቀድመን እርምጃን እንውሰድ። እርምጃን ቀድሞ መውሰድ ማለት የፍቅር ጠብታን በፍጥነት መግለጽ ማለት ነው።

እንግዲህ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ሁልጊዜ ቀዳሚ የሆነውን የእግዚአብሔር ፍቅር በማሰብ ራሳችንን እንዲህ ብለን እንጠይቅ፡- አስቀድሞ የወደደኝን እግዚአብሔር አመሰግነዋለሁ? የእግዚአብሔርን ፍቅር በውስጤ ስለተሰማኝ እርሱን አመሰግነዋለሁ? የእርሱን ፍቅር ለሌሎች ለማሳየት እሞክራለሁ? ከፍቅር ትዕዛዙ በሚመጣውን ሁለተኛውን እርምጃ በመታገዝ ወንድሞቼን እና እህቶቼን ለመውደድ ጥረት አደርጋለሁ?

ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በመውድውድ እና እግዚአብሔር እኛን እንዲወደን በመፍቀድ ታላቁን የፍቅር ትእዛዝ በዕለት ተዕለት በሕይወታችን መካከል በተግባር እንድንኖረው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን።”

 

30 October 2023, 12:19