ፈልግ

በረሃማው ሥፍራ በረሃማው ሥፍራ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ለአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ምላሽ እንዲሰጥበት ጥሪ አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2015 ዓ. ም. ያቀረቡት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን የሚያጥናክር “ውዳሴ ለእግዚአብሔር ይሁን” በሚል ርዕሥ ቀጣይ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይፋ አድርገዋል።የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ቀውስ ለመቋቋም በቂ ምላሽ እየሰጠን አይደለም ያሉት ቅዱስነታቸው አደጋው ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸው፥ የዓለም ሙቀት መጨመር የሰው ልጅ አመጣጥ አሁን ከጥርጣሬ በላይ ሆኗል በማለት የአየር ንብረት ለውጥ ተቃዋሚዎችን ተችተው፥ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን የሚደረግ እንክብካቤ ከክርስትና እምነት እንደሚመነጭ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውዳሴ ለእግዚአብሔር ይሁን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ላይ እንደገለጹት፥ “የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ቦታ ለመውሰድ ከከጀለ ተመልሶ የራሱ ጠላት ይሆናል” በማለት፥ በአሲሲው ቅዱስ ፍራንስኮስ ዓመታዊ በዓል ዕለት ማለትም መስከረም 23/2016 ዓ. ም ባወጡት አዲሱ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን መደምደሚያ ላይ ገልጸዋል። አዲሱ ቃለ ምዕዳናቸው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2015 ዓ. ም. ይፋ ያደረጉት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ቀጣይ እና ሰፊ ይዘት ያለው እንደሆነ ተመልክቷል።

ስድስት ምዕራፎች እና 73 አንቀጾች ባሉት በዚህ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፥ በቀደመው ቃለ ምዕዳናቸው ሥነ-ምህዳርን በማስመልከት ያወጡትን ጽሑፍ ይበልጥ ለማብራራት እና ለማጠናቀቅ የፈለጉት ሲሆን፥ እንደዚሁም የአየር ንብረት ለውጥ ድንገተኛ አደጋን ለመጋፈጥ የማንቂያ ደወል ያሰሙበት እና የትብብር ጥሪን ያቀረቡበት ነው። አዲሱ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በተለይ በ2016 ዓ. ም. በኅዳር እና በታኅሳስ ወር መካከል በዱባይ የሚካሄደውን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ “COP28” ኤግዚቪሽን የሚመለከት ነው።

ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ላይ፡- “ጊዜ እያለፈ በሄደ ቁጥር የምንኖርበት ዓለም እየፈረሰ እና ለመሰባበር እየተቃረበ በሚገኝበት ጊዜ በቂ ምላሽ አለመስጠታችንን ተረድቻለሁ፤ በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ በብዙ ሰዎች እና ቤተሰቦች ሕይወት መካከል የተሳሳተ አመለካከት እንዲያድግ ማድረጉ የማይታበል ጉዳይ ነው።” (2) የአየር ንብረት ለውጥ ኅብረተሰብን እና የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብን ከሚገጥሟቸው ዋና ዋና ተግዳሮቶች መካከል አንዱ ሲሆኑ፥ ተጽእኖዎቹ በአገር ውስጥ እና በዓለም ዙሪያ ተጋላጭ በሆኑ ሰዎች በኩል የሚመጡ ናቸው።” (3)

የአየር ንብረት ለውጥ ምልክቶች ስለመታየት

የመጀመሪያው ምዕራፍ ስለ ዓለም ዓቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ የሚገልጽ ሲሆን፥ ቅዱስነታቸው በዚህ ክፍል ውስጥ የክስተቱን አደገኛነት ለመካድ፣ ለመደበቅ፣ ለመሸፋፈን ወይም እንደገና ለመመልከት ከመሞከር በላይ የአየር ንብረት ለውጥ ምልክቶች በጉልህ እየታዩ መጥተዋል” ብለዋል። ቀጥለውም፥ “ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አስከፊ የአየር ሁኔታ ክስተቶች፥ ያልተለመደ የሙቀት መጠን መጨመር፣ ድርቅ እና ምድራችን የምታሰማውን ሌሎች የስቃይ ጩኸቶችን ሰምተናል” ብለው፥ ክስተቱ ሁሉን ሰው የሚያጠቃ ድምጽ አልባ በሽታ ነው” ብለዋል።

ከዚህም በላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ እንዳሉት፣ “በሰው ልጆች የሚቀሰቀሱ ልዩ የአየር ንብረት ለውጦች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ እና እየጠነከሩ መሆናቸውን ገልጸው፥ ይህም የአደጋው መከሰት ዕድልን ከፍ ማድረጉን ማረጋገጥ ተችሏል” ብለዋል።  ቅዱስነታቸው እንዳብራሩት፥ የዓለም ሙቀት መጠን ከሁለት ዲግሪ በላይ ቢጨምር፥ የግሪንላንድ የበረዶ ክምር እና ሰፊው የአንታርክቲክ ክፍል ሙሉ በሙሉ ይቀልጥና በሰው ልጆች ላይ እጅግ አስከፊ መዘዝ እንድሚያስከትል አስረድተዋል። (5)

የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት እንደ ዋዛ የሚመለከቱ ሰዎችን በማስመልከት ቅዱስነታቸው ሲናገሩ፥ አሁን በፍጥነት እያጋጠመን ያለውን ያልተለመደ የሙቀት መጨመር ለማረጋገጥ መቶ ዓመትን ወይም ሺህ ዓመታትን የሚጠይቅ ሳይሆን አንድ ትውልድ ብቻ እንደሚወስድ ገልጸው፥ በእነዚህ እውነታዎች ምክንያት ምናልባት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ብዙ ሰዎች መኖሪያውን ለቀው ለመሰደድ እንደሚገደዱ አስጠንቅቀዋል። (6) ኃይለኛ ቅዝቃዜም የተመሳሳይ መንስኤ አማራጭ መግለጫ እንደሆነ አስረድተዋል። (7)

የድሃው ማኅበረሰብ ጥፋት አይደለም!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እውነታውን በአጭሩ ለማስረዳት፥ “በቤተሰብ ውስጥ ብዙ ልጆች ያሏቸው፥ አልፎ ተርፎም ችግሩን ለመፍታት ሲሞክር የሴቶችን አካል የሚያጎድሉ ባላደጉት አገራት ውስጥ የሚገኙ ድሆች ኃላፊነትን ሊወስዱ ይገባል” የሚሉ ሰዎች መኖራቸውን አስታውሰዋል። “እንደተለመደው ጥፋቶች በሙሉ የድሃው ማኅበረሰብ ሊመስሉ ይችላል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ እውነታው ግን ከጠቅላላው የዓለማችን ሕዝቦች መካከል ሃምሳ ከመቶ በላይ የሆነው የፕላኔታችን ድሃ ማኅበረሰብ በከፍተኛ የአየር ብክለት እንደጠቃ እና የበለፀጉ አገራት የነፍስ ወከፍ ካርበን ልቀት ከድሃው ማኅበረሰብ በእጅጉ እንደሚበልጥ አስረድተው፥ "በዓለማችን ከግማሽ በላይ ድሃ ሕዝብ የሚኖሩባት የአፍሪካ አኅጉር፥ በትንሹም ቢሆን ለታሪካዊ ልቀቶች ተጠያቂ መሆኗን እንዴት እንረሳዋለን?" (9)

የቅሪተ አካል ነዳጅ አጠቃቀም በመቀነስ የአየር ንብረት ለውጥ ለመቅረፍ የሚደረገው ጥረት የሥራ ዕድልን ይቀንሳል በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተከራክረዋል። በእውነት እየሆነ ያለው ግን፥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሥራቸውን እያጡ እንደሆነና የባሕር ከፍታ መጨመር ድርቅና ሌሎች ፕላኔቷን የሚጎዱ ክስተቶችን በማስከተል ብዙ ሰዎችን ለሞት መዳረጉን አስረድተዋል። በተመሳሳይ ወቅትም "ወደ ታዳሽ የኃይል አጠቃቀም የሚደረገውን ሽግግር በትክክል ካስተዳደሩት በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ሥፍር ቁጥር የሌለው የሥራ ዕድል ሊፈጥር እንደሚችል እና ይህም ፖለቲከኞች እና የንግድ ተቋማት መሪዎች ጥረታቸውን በዚህ ላይ እንዲያደርጉ ይጠይቃቸዋል” ብለዋል። (10)

የማይታበል የሰው ልጅ አመጣጥ

ለአየር ንብረት ለውጥ ተጠያቂው የሰው ልጅ እንደሆነ መጠራጠር እንደማይቻል የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በከባቢ አየር ውስጥ የምድራችንን የሙቀት መጠን የሚጨምሩ ጋዞች ክምችት እስከ አሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የተረጋጋ እንደ ነበር፥ ነገር ግን ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አስረድተዋል። (11) በተመሳሳይም የዓለም ሙቀት ባለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ውስጥ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት በአሥር ዓመት ውስጥ የ0.15° C የጨመረው የሙቀት መጠን ካለፉት 150 ዓመታት በእጥፍ እንደሚበልጥ እና በዚህ ፍጥነት ከቀጠለ በአሥር ዓመታት ውስጥ ብቻ ከፍተኛው የዓለም ጣራ ወደ 1.5° C ሊደርስ እንደሚደሚችል አስጠንቅቀዋል። (12) ይህም የባሕርን አሲዳማነት እና የበረዶ ግግር መቅለጥን አስከትሏል። በእነዚህ ክስተቶች እና የምድራችንን የሙቀት መጠን በሚጨምሩ ጋዞች ልቀት መካከል ያለውን ትስስር መደበቅ እንደማይቻል ቅዱስነታቸው ገልጸው፥ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው ቀውስ ታላላቅ የኢኮኖሚ ኃይሎችን ቀልብ እንደማይስብ፥ ነገር ግን ምኞታቸው በዝቅተኛ ወጭ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚገኝ ከፍተኛ ትርፍ ላይ መሆኑን አስረድተዋል። (13)

የበለጠ አስከፊ ጉዳቶችን በጊዜ ማስወገድ

“በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚያጋጥሙኝ አንዳንድ ምክንያታዊ ያልሆኑ አስተያየቶች ግልጽ የሆኑ ማብራሪያዎችን የመስጠት ግዴታ እንዳለብኝ ይሰማኛል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀጥለውም፥ ለእነዚህ አደገኛ ለውጦች ያልተለመደ ፍጥነት ምክንያቱ፥ ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት ውስጥ የሰው ልጅ ቁጥጥር ሳይደረግበት በተፈጥሮ ላይ ባሳየው ጣልቃገብነት እና አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች መሆኑን ተናግረዋል። (14) ባለፉት በርካታ መቶ ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተላቸው አንዳንድ ተፅዕኖዎች ቀድሞውኑ የማይመለሱ መሆናቸውን ቅዱስነታቸው ገልጸው፥ ዋልታዎች በሙቀት መቅለጣቸው በመቶዎች በሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥም ሊቀለበስ እንደማይችል ተናግረዋል። (16) ከዚህ የበለጡ አስከፊ ጉዳቶችን ለማስወገድ በምንችልበት የመጨረሻው ጊዜ ላይ እንገኛለን ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ አንዳንድ የጥፋት ዘመን የሚመስሉ ምርመራዎች እምብዛም ምክንያታዊ ወይም በቂ መሠረት የሌላቸው ሊመስሉ ቢችሉም ነገር ግን ምን እንደሚሆን በእርግጠኝነት መናገር አንችልም ብለዋል። (17) በአዲሱ ቃለ ምዕዳናቸው ላይ ሰፋ ያለ አመለካከት በአስቸኳይ እንደሚያስፈልግ እና ከእኛ የሚጠበቀው ይህን ዓለም ካለፍን በኋላ ለምንተወው ውርስ የተወሰነ ኃላፊነት እንዲሰማን እንጂ ሌላ አይደለም ብለዋል (18)። የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ልምድ በማስታወስ፥ “ሁሉም ነገር እርስ በርስ የተገናኘ እና ማንም ብቻውን የዳነ የለም” በማለት ደግመው ተናግረዋል። (19)

ሳይንሳዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ሞዴል-የሰው ልጅ ገደብ የለሽ ሃሳብ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ ሳይንሳዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ሞዴል በተናገሩበት ሁለተኛው ምዕራፍ ላይ፥ እውነታ፣ ጥሩነት እና እውነት ከቴክኖሎጂ እና ከኢኮኖሚያዊ ኃይል በቀጥታ እንደሚመጣ (20) እና እራሱን በራሱ እንደሚመግብ (21)፣ ተመስጦውን ያለ ገደብ ከሰው ልጅ ሃሳብ እንደሚወስድ እና የሰው ልጅ በራሱ ላይ እንደዚህ ያለ ስልጣን ኖሮት እንደማያውቅ እና ዛሬ ግን ጥበብ ጥቅም ላይ እንደሚውል የሚያረጋግጥ ምንም ነገር እንደሌለ፥ በተለይ እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል ስናስብ ለትንሽ የስብዕና ክፍል በጣም አስጊ መሆኑን አስረድተዋል። (23) እንደ አለመታደል ሆኖ በአቶሚክ ቦምብም እንደታየው፥ ግዙፍ የቴክኖሎጂ እድገታችን በሰው ልጅ ሃላፊነት፣ እሴቶች እና የሕሊና ዕድገት አለመታገዙን ተናግረዋል። (24)

በዙሪያችን የሚገኘው ዓለም የብዝበዛ፣ ያልተገራ ጥቅም እና ገደብ የለሽ ምኞት (25) እንዳልሆነ በድጋሚ በማረጋገጥ፥ እኛ የተፈጥሮ አካል መሆናችንን ያስታውሰናል ብለዋል። ይህ ደግሞ “የሰው ልጅ ከውጪ የመጣ፣ አካባቢን ሊጎዳ የሚችል ባዕድ አካል ነው የሚለውን ሃሳብ አያካትትም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ የሰው ልጅ የተፈጥሮ አካል መሆኑ መታወቅ እንዳለበት፥ (26) "የሰው ልጆች ስብስብ ብዙውን ጊዜ አካባቢን እንደሚፈጥሩ አስረድተዋል። (27)

የሥነ-ምግባራዊ ኃይል ውድቀት፥ ግብይት እና የሐሰት ዜና

አስደናቂ የቴክኖሎጂ ዕድገት ብናሳይም በተመሳሳይ ሁኔታ የብዙ ፍጥረታት ሕይወት እና የራሳችንን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥሉ ወደሚችሉ ከፍተኛ አደገኛ ፍጥረትነት መለወጣችንን ገና አልተገነዘብንም ብለዋል። (28) የእውነተኛ ኃይል ሥነ-ምግባራዊ ውድቀት ለገበያ ኤኮኖሚ እና ለሐሰት መረጃ ምስጋና ይግባውና ከፍተኛ ሃብት ባላቸው ሰዎች እጅ ያሉ ጠቃሚ መሣሪያዎች የሕዝብን አስተያየትን ለመቅረጽ ይውላሉ ብለዋል።

በእነዚህ ስልቶች አካባቢን የሚበክሉ ፕሮጄክቶች በሚተገበሩባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎችን በማታለል፥ ሰዎቹ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን እና የሥራ ዕድሎችን እንደሚያማጣላቸው ቢያምኑም ነገር ግን ፕሮጀክቱ ባድማ እና ለመኖሪያ ምቹ ያልሆነ መልክዓ ምድር እንደሚያመጣ በግልፅ ባለመነገራችው በሕይወት ጥራት ላይ ግልጽ ማሽቆልቆል እንደሚያስከትል አስረድተዋል። (29)

በአመክንዮአዊነት፣ በእድገት እና በምናባዊ ተስፋዎች ውስጥ በመደበቅ በትንሽ ወጪ ከፍተኛ ትርፍ የማግኘት አስተሳሰብ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን ምንም ዓይነት ልባዊ አሳቢነት እና በኅብረተሰባችን የተገለሉ ድሆችን እና ችግረኞችን ለመርዳት ማሰብ የማይቻል እንደሚያደርገው፥ የሐሰተኛ ነቢያት ተስፋ ድሆች ራሳቸው ለእነርሱ ባልተሠራው ዓለም እንዲታለሉ ያደርጋቸዋል። (31) እንግዲህ፣ “ብዙ ዕድልና ጥቅም ባላቸው የተወለዱ ሰዎች የሚገዙበት ሁኔታ እንዳለ፥ (32)  ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እነዚህ ግለሰቦች በድርጊታቸው ለደረሰባቸው ጉዳት የሚከፍሉትን ልጆች በመመልከት (33)፥ የሕይወታቸው ትርጉም ምንድን ነው ብለው እራሳቸውን እንዲጠይቁ ጋብዘዋል።

ደካማ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በአዲሱ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ቀጣዩ ምእራፍ ላይ፣ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ድክመት በመጥቀስ፥ በመንግሥታት መካከል ያሉ የባለብዙ ወገን ስምምነቶችን (34) ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል። “በሕግ የሚመራ ዓለም አቀፋዊ ሥልጣን ሊኖር እንደሚችል ስንነጋገር የግድ የግል ባለሥልጣንን ማሰብ አይኖርብንም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ይልቁንም ዓለም አቀፍ የጋራ ጥቅምን ለማስገኘት የሚያስችል ኃይል ስላላቸው እና ይበልጥ ውጤታማ ስለ ሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ማሰብ እንደሚገባ እና ረሃብን እና ድህነትን በማስወገድ መሠረታዊ የሆኑ ሰብዓዊ መብቶችን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል። እነዚህ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አንዳንድ አስፈላጊ ግቦችን ለማሳካት በሚያስችል መንገድ እውነተኛ ሥልጣን ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል። (35)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ዓለም አቀፍ ቀውሶች ጠቃሚ ለውጦችን ለማምጣት ጥሩ አጋጣሚ የሚሆኑበት ጊዜ በከንቱ እየባከነ መሆኑን በጸጸት ገልጸው፥ ይህ የሆነው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2007-2008 የፋይናንስ ቀውስ ወቅት እና በድጋሚ በኮቪድ-19 ቀውስ ወቅት እንደ ነበር አስታውሰው፥ ይህም ወደ ትልቅ ግለኝነትን፣ ውህደት መቀነስን እና ሁልጊዜም ጉዳት ሳይደርስባቸው በቀላሉ የሚያመልጡበትን መንገድ ለሚያገኙ ኃይሎች ነፃነትን እንደጨመረላቸው አስረድተዋል። (36) ብዙ የሲቪል ማኅበረሰብ ስብስቦች እና ድርጅቶች የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ድክመቶች ለማካካስ እንደሚረዱ በመገንዘብ፥ የቀድሞውን የብዙ መንግሥታት ኅብረት ከማዳን በተጨማሪ አሁን ያለው ፈተና አዲሱን የዓለም ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት እንደገና ማዋቀር እና መፍጠር እንደሆነ ቅዱስነታቸው ተናግረው፥ (37) የተቀበሩ ፈንጂዎችን በማምከን ሂደት የኦታዋ ስምምነትን በመጥቀስ ይህም የሲቪል ማኅበረሰብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያላሳካቸውን ቀልጣፋ እንቅስቃሴ እንዴት መፍጠር እንደሚችል ያሳያል ብለዋል።

ጠንካራ ተቋማትን የሚደግፉ ደካማ ተቋማት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቀረቡት ሃሳብ የብዙ መንግሥታት ኅብረት ከታች ያለው ሁለገብነት በቀላሉ በስልጣን ልሂቃን የሚወሰን ሳይሆን የአየር ንብረት ቀውስን በተመለከተ እንደሚሆን ተስፋ ማድረግ ነው። በዚህ ምክንያት ዜጎች የፖለቲካ ስልጣንን በብሄራዊ፣ በክልላዊ እና በማዘጋጃ ቤት ደረጃ ካልተቆጣጠሩት በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መቆጣጠር አይቻልም። (38)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰውን ልጅ ቀዳሚነት ካረጋገጡ በኋላ፥ በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ ስለ ሰብዓዊ ክብር ጥበቃ ሲናገሩ፥ "ፖለቲካን የመተካት ጉዳይ ሳይሆን ነገር ግን ጎልተው እየወጡ ያሉ ኃይሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸውን መገንዘብ ነው" በማለት አስረድተዋል። "የችግሮች መልሶች ከየትኛውም አገር ሊመጡ እንደሚችሉ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ምንም እንኳን ትንሽ ቢሆንም የብዙ መንግሥታት ኅብረት የማይቀር ሂደት ነው" በማለት አስረድተዋል። (40)

ስለዚህ ለውጤታማ ትብብር የተለየ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልገው፥ የኃይል ሚዛኖችን ብቻ ማሰብ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ነገር ግን ለአዳዲስ ችግሮች ምላሽ መስጠት እና ከዓለም አቀፋዊ ዘዴዎች ጋር ምላሽ ማግኘት አስፈላጊ ነው" ብለው፥ ይህም ዓለም አቀፍ እና ውጤታማ ደንቦች ማቋቋምን የሚመለከት ነው” በማለት ተናግረዋል። (42)

ይህ ሁሉ ለውሳኔ አሰጣጥ አዲስ አሠራርን አስቀድሞ ማሳደግ እንደሚገባ የሚያሳይ፥ የሚፈለጉት የውይይት፣ የምክክር፣ የግልግል ዳኝነት፣ የግጭት አፈታት እና ቁጥጥር ቦታዎች እና በመጨረሻም፣ በዓለም አቀፍ አውድ ውስጥ አንድ ዓይነት ዲሞክራሲን በመጨመር የተለያዩ ሁኔታዎች ሊገለጹ እና ሊካተቱ እንደሚችሉ በመግለጽ፥ ለሁሉ ሰው የሚጨነቁ ተቋማትን ሳንንከባከብ የኃያላንን መብቶች ለማስጠበቅ ተቋማትን መደገፍ ለእኛ ጠቃሚ አይሆነንም” ብለዋል። (43)

የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ

በቀጣዩ ምዕራፍ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እስከ ዛሬ የተካሄዱትን የተለያዩ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤዎችን በመግለጽ፥ በፓሪስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ኅዳር ወር 2016 ዓ. ም. ተካሂዶ የነበረውን እና የተደረሱ ስምምነቶችን አስታውሰው፥ በተጨማሪም አሳሪ ስምምነቶችን ለማስፈፀም የሚያስገድዱ ውጤታማ ደንቦች፣ እውነተኛ ማዕቀቦች እና ተገዢነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ውጤታማ መሣሪያዎች አለመኖራቸውን በመግለጽ፥ በተጨማሪም ለክትትሉ ተጨባጭ ሂደቶችን ለማጠናከር እና የተለያዩ አገራት ዓላማዎች ለማነፃፀር አጠቃላይ መስፈርቶችን ለማመቻቸት አሁንም እየተሠራ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። (48)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማድሪድ በተካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ (COP) ጉባኤ ላይ የተሰማቸውን ቅሬታ በመግለጽ፥ የግላስጎው ጉባኤ የፓሪስ ግቦችን እንደሚያንሰራራ በማስታወስ፥ የቀረቡት ብዙ ምክረ ሃሳቦች ፈጣን እና ውጤታማ ሽግግርን ወደ አማራጭ እና አነስተኛ ብክለት የኃይል ዓይነቶች በማምጣት ምንም መሻሻል አለማምጣታቸውን ገልጸዋል። (49)

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2022 በግብፅ የተካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP27) “አንድ ተጨማሪ እና አስቸጋሪ የድርድር ምሳሌ እንደ ነበር እና ምንም እንኳን “በአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች በጣም በተጠቁ አገራት ኪሳራ እና ጉዳትን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ አንድ እርምጃ ወደፊት ቢያሳይም፣ ይህ በብዙ ነጥቦች ላይ ትክክል ሳይሆን ቀርቷል። (51)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አዲሱን ቃለ ምዕዳናቸውን ሲያጠቃልሉ፣ ዓለም አቀፍ ድርድሮች፣ ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን ከዓለም አቀፉ የጋራ ጥቅም በላይ የሚያስቀምጡ አገሮች በሚወስዱት አቋም ምክንያት ከፍተኛ ዕድገት ማምጣት እንዳልቻሉ ገልጸዋል። “እኛ ለመደበቅ እየሞከርን ባለነው ውጤት የሚሰቃዩ ሰዎች የሕሊና እና የኃላፊነት ውድቀትን አይረሱትም” (52) ብለዋል።

ከዱባይ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ምን ይጠበቃል?

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ወደ ፊት ሊካሄድ የታቀደውን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (COP) በማሰብ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል። "ራስን ከማጥፋት በቀር ተስፋ የምናደርግበት ሌላ ምንም እንደሌለው መናገር ሁሉም የሰው ልጅ በተለይም በጣም ድሆችን ለአየር ንብረት ለውጥ አስከፊ ተፅእኖዎች ማጋለጥ ማለት ነው" ብለውል። (53)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀጥለውም፥ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP28) ወሳኝ የሆነ የኃይል ሽግግርን ለማፋጠን እና ቀጣይነት ባለው ክትትል የሚደረግ ውጤታማ ቁርጠኝነት እንደሚኖር ተስፋ ማድረግ እንደሚገባ እና ይህ ጉባኤ የአቅጣጫ ለውጥን ሊያመጣ እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። (54) “አስፈላጊው ሽግግር ወደ ንፁህ የኃይል ምንጮች ማለትም ወደ ንፋስ እና የፀሐይ ኃይል በመውሰድ የቅሪተ አካል ነዳጆችን ወደ መተው በፍጥነት እየሄደ አይደለም” ብለዋል። ስለዚህ የሚደረገው ማንኛውም ነገር ትኩረትን ለማዘናጋት እንደ ተንኮል ብቻ የመታየት አደጋ እንዳለው ገልጸዋል። (55) “ለችግሮቻችን ቴክኖሎጂያዊ መፍትሄ ብቻ መፈለግ አንችልም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ከስር የበኩላችንን አስተዋፅኦ የምናደርግበት ቀጣይ ሥራ እየተበላሸ እያለ ስንጥቅ ውስጥ ተጣብቀን አእምሮን በወረቀት በመክደን የመቆየት አደጋ ላይ እንገኛለን ብለዋል። (57)

ከአሁን በኋላ በአካባቢ ጥበቃ ጥያቄ ላይ መፌዝ ይቁም

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአዲሱ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ላይ፥ ይህን ጉዳይ እንደ ንጹሕ ሥነ-ምህዳራዊ፣ አረንጓዴ እና የፍቅር ንግግር፣ በኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች በተደጋጋሚ የሚሳለቁበትን ኃላፊነት የጎደለው ቀልድ እንድናቆም ጠይቀናል።

በመጨረሻ በማንኛውም ደረጃ የሰው እና ማኅበራዊ ችግር መሆኑን እንድንቀበል እና በዚህ ምክንያት የሁሉንም ተሳትፎ እንደሚጠይቅ አስረድተዋል። በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ላይ ተቃውሞአቸውን የተገለጹ ቡድኖች በአሉታዊ መልክ እንደ ጽንፈኛ መታየታቸውን ተናግረው፥ በእውነቱ ከሆነ በኅብረተሰቡ ባዶ የቀረውን ቦታ ጤናማ ግፊት በማድረግ እየሞሉት መሆኑን በመግለጽ እያንዳንዱ ቤተሰብ የልጆቻቸው የወደፊት ዕጣ ፈንታ አደጋ ላይ መውደቁን ሊገነዘቡት ይገባል ብለዋል። (58)  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በኮንፈረንሱ ላይ የሚሳተፉት አባላት ከአንዳንድ አገራት ወይም የንግድ ድርጅቶች የአጭር ጊዜ ጥቅም በላይ የልጆቻቸውን የጋራ ጥቅም እና የወደፊት ዕጣ ፈንታ ማጤን የሚችሉበትን ዘዴ ቀያሾች እንዲሆኑ ጠቀው፥ ይህ መንገድ የፖለቲካውን ልዕልና ማሳየት እንጂ አሳፋሪ አለመሆኑን አስገንዝበዋል። “ይህን ጥያቄ ለኃያላኑ በድጋሚ ማቅረብ እችላለሁ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ማንንም ሰው በዚህ ደረጃ ሥልጣን ላይ እንዲቆይ የሚያነሳሳው፥ አስቸኳይ እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እርምጃ መውሰድ አለመቻሉን ሲያታውስ ብቻ ነው ወይ?” (60)

ከክርስትና እምነት የሚፈልቅ ተነሳሽነት

በመጨረሻም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ለዚህ ቁርጠኝነት የሚነሳሱት ከክርስትና እምነት እንደሚወጡ አንባቢዎችን አሳስበው፥ “የሌሎች ሃይማኖቶች ወንድሞቼ እና እህቶቼም እንዲሁ እንዲያደርጉ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል። (61) “የአይሁድ-ክርስቲያን ራእይ የሰው ልጅ ልዩ እና ማዕከላዊ እሴት የሆነውን የእግዚአብሔር ፍጥረታት አስደናቂ ዜማ መካከል እንደሚሟገት፥ ነገር ግን የአጽናፈ ዓለሙ ክፍል እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም በማይታዩ ትስስሮች በመቆራኘት አንድ ላይ ሆነን ሁለንተናዊ ቤተሰብ፣ የተቀደሰ፣ አፍቃሪ፣ ደግ እና በትህትና አክብሮት የተሞላን የላቀ ኅብረትን እንፈጥራለን” ብለዋል። (67)

“ይህ የራሳችን ፍላጎት ውጤት አይደለም፤ እግዚአብሔር በዙሪያችን ካለው ዓለም ጋር በቅርብ የተገናኘ በመሆኑ መነሻው በሕይወታችን ጥልቀት ውስጥ ነው።” (68) አስፈላጊው ነገር፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደጻፉት፥ “ያለ ባሕላዊ ለውጦች፣ በማኅበረሰቦች ውስጥ ያለ የአኗኗር ዘይቤ እና እምነት ካልዳበረ ዘላቂ ለውጥ እንደሌለ እና ከግል ለውጦች ውጭ ምንም ዓይነት የባሕል ለውጦች የሉም” በማለት ተናግረዋል። (70) “የአባወራ ቤቶች ብክለትን እና ብክነትን ለመቀነስ እና በጥንቃቄ ለመመገብ የሚያደርጉት ጥረት አዲስ ባሕል እየፈጠረ እንደሆነ፥ የግል፣ የቤተሰብ እና የማኅበረሰቡ ልማዶች እየተለወጡ መሆናቸው ብቻ ትልቅ የለውጥ ሂደቶችን ከኅብረተሰቡ ውስጥ ለማምጣት እየረዳ ይገኛል።” (71)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን ሲያጠናቅቁ፥ “በዩናይትድ ስቴትስ እያንዳንዱ ሰው የሚያወጣው የልቀት መጠን ቻይና ውስጥ የሚኖሩት ግለሰቦች ከሚያውጡ በሁለት እጥፍ ገደማ እንደሚበልጥ እና ከድሃ አገሮች ጋር ሲለካ በአማካይ ሰባት እጥፍ እንደሚበልጥ አስረድተዋል።  በመቀጠልም ከምዕራባዊው ሞዴል ጋር በተገናኘ ኃላፊነት በጎደለው የአኗኗር ዘይቤ ሰፊ ለውጥ ላይ ከፍተኛ የረጅም ጊዜ ተፅእኖ እንደሚኖረው አረጋግጠው፥ በውጤቱም አስፈላጊ ካልሆኑ የፖለቲካ ውሳኔዎች ጋር፣ አንዳችን ለሌላው እውነተኛ እንክብካቤ ለማድረግ በምናደርገው ጉዞ ላይ እድገትን እናመጣለን” ብለዋል። (72)

 

05 October 2023, 21:23