ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የተስፋ ቤተሰብ ማኅበር አባላትን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የተስፋ ቤተሰብ ማኅበር አባላትን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የተስፋ ቤተሰብ ማኅበር ጥሪውን እንዲንከባከብ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በብራዚል የአደንዛዥ ዕጽ አመል ያለባቸውን ሰዎች የሚረዳ የተስፋ ቤተሰብ ካቶሊካዊ ማኅበር አባላትን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ዓርብ መስከረም 18/2016 ዓ. ም. በቫቲካን የተቀበሏቸው የማኅበሩ አባላት፥ ብራዚል ውስጥ በአደንዛዥ ዕጽ ለተጠቁት ሰዎች ተስፋን የሚሰጡ፣ ካለባቸው አመል ተላቅቀው ጤናማ ማኅበራዊ ሕይወት እንዲኖሩ ዕርዳታን በማድረግ ላይ የሚገኙ እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በምዕመናን የሚታገዝ የተስፋ ቤተሰብ ማኅበርን የመሠረቱት ፍራንችስካዊ ካኅን አባ ሃንስ ስታፐል ሲሆኑ፣ የመሠረቱትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1983 ዓ. ም. እንደሆነ ታውቋል። የማኅበሩ ዋና ዓላማ በብራዚል ሳን ፓውሎ ግዛት፥ ጓራቲንጌታ ከተማ የሚኖሩ የአደንዛዥ ዕጽ ሱሰኞችን ካለባቸው ችግር ለማላቀቅ አስፈላጊውን ዕርዳታ ማድረግ እንደሆነ ታውቋል።

በቅድስት መንበር ሥር ከሚገኝ የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ድጋፍ የሚደረግለት ይህ የተስፋ ቤተሰብ ማኅበር፥ የአደንዛዥ ዕጾች ተጠቃሚ የሆኑ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን እና የኤች አይ ኤድስ ሕመም ያለባቸውን ሰዎች፥ እንዲሁም በሌሎች የተለያዩ ችግሮች ውስጥ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ዕርዳታን እንደሚያደርግ ታውቋል።

የተስፋ ቤተሰብ ማኅበር መሥራች ፍራንችስካዊ ካኅን አባ ሃንስ ስታፐል ማኅበሩን የመሠረቱት፥ ጣሊያን ውስጥ የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ሕይወት እና የፎኮላር እንቅስቃሴ መሥራች በሆነች ኪያራ ሉቢክ የድህነት እና የአንድነት ዝንባሌ ተመስጠው እንደ ታውቋል። የቤተሰብ ተስፋ ማኅበር ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ በመላው ብራዚል እና ሌሎች አገሮችም በመስፋፋት ወደ ዕርዳታ አድራጊ ማኅበርነት መለወጡ ታውቋል።

የተስፋ ዝንባሌን መተው አይገባም

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቫቲካን ውስጥ በሚገኝ በቅዱስ ዳማስዮስ ቅጥር ግቢ ለተቀበሏቸው 1,200 ለሚሆኑ የማኅበሩ አባላት ባደረጉት ንግግር፥ ለሥራቸው እና ለምስክርነታቸው ምስጋናቸውን አቅርበው፥ ፍቅራቸው እና የተስፋ ጥሪያቸው እንዳይለያቸው አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው ለማኅበሩ አባላት ባደረጉት ንግግር፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሚቀርብላቸው ጥሪ በመታገዝ የሕይወታቸውን ትርጉም የማያዩ ሰዎች ተስፋ እንዲኖራቸው፥ በማኅበራዊ ተጋላጭነት ሁኔታዎች ውስጥ በሚያገኟቸው ሰዎች መካከል እርሱን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲወዱት የተጠሩበት ጥሪ እንደሆነ ተናግረዋል።

በኅብረተሰባችን ውስጥ የሚገኝ የግዴለሽነት መቅሰፍት

“በአሁኑ ዓለም ውስጥ ከሚታዩ ታላላቅ ችግሮች መካከል አንዱ ግድየለሽነት ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የተስፋ ቤተሰብ ማኅበር፥ በዕፅ እና ሌሎች ሱሶች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ወጣቶች በተለይም ሕይወታቸው በስቃይ ውስጥ የሚገኝ ሰዎችን ተቀብሎ የሚንከባከብ ማኅበር እንደሆነ ተናግረው፥ የደጉ ሳምራዊ ምሳሌን በመከተል እነሱን በመፈወስ እና ክብራቸውን መልሰው እንዲያገኙ በመርዳት ላይ የሚገኝ ማኅበር እንደሆነ ተናግረዋል።

ቅዱስነታቸው በማከልም፥ የማኅበሩ አባላት የደጉ ሳምራዊ ምሳሌን በመከተል፥ ከመንገድ ላይ ላነሳችኋቸው ብዙ ሰዎች ወንድሞች በመሆን እነርሱን በማከም፣ በመፈወስ እና ሰብዓዊ ክብራቸውን መልሰው እንዲያገኙ አድርጋችኋል በማለት ተናግረዋል።

በኅብረተሰቡ ውስጥ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ድጋፍ ማድረግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠል፥ ተስፋን ማምጣት ማለት ሰዎችን ከመጥፎ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ማድረግ ወይም መከራን እንዲያሸንፉ ማገዝ ማለት ብቻ ሳይሆን፥ አንድ ሰው በቤተሰብ እና በኅብረተሰብ ውስጥ ቦታ እንዲያገኝ ማድረግ ማለት ነው ብለዋል።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2007 ዓ. ም. በብራዚል ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት የተስፋ ቤተሰብ ማኅበርን በማስመልከት ባደረጉት ንግግር፥  ማኅበሩ በጓራቲንጌታ ከተማ የሚያከናውነው ተግባር መንፈሳዊ ገጽታ ያለው፥ እግዚአብሔርን እንደገና ያገኘበት እና በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ንቁ ተሳትፎን ያሳየበት እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለማኅበሩ አባላት ባደረጉት ንግግር፥ “የተስፋ ዝንባሌአቸው በመካከላቸው የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ በመቀስቀስ፣ ሰዎችን በቁሳዊ፣ በመንፈሳዊ፣ በአካላዊ እና በነፍሳዊ ዕርዳታ እንዲንከባከቧቸው የሚያደርግ መሆኑን ተናግረው፥ የማኅበሩ 40ኛ ዓመት መታሰቢያ በሚከበርበት በዚህ ወቅት፥ የማኅበሩ አባላት በሙሉ የመሥራቹን የፍቅር ዝንባሌ በትህትና እና በኅብረት ማዳበርን እንዲቀጥሉበት አደራ ብለዋል።

ለቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልግ መልካም ሥራ ነው

ር ዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ የተስፋ ቤተሰብ ማኅበር አባላት በሥራቸው አማካይነት በሚሰጡት ምስክርነት እንዲሁም ካህናትን፣ የዘርዓ ክህነት ተማሪዎችን፥ ገዳማውያን እና ገዳማውያትን ለመርዳት ለሚያደርጉት ጥረት ምስጋና አቅርበው፥ ለቤተ ክርስቲያን እጅግ አስፈላጊ በሆነው በዚህ መልካም ተግባር እንዲገፉበት አሳስበዋል።

 

30 September 2023, 16:58