ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሞንጎሊያ ከሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ጋር ለሰላም መጸለያቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሞንጎሊያ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከማገባደዳቸው በፊት ከዓለማችን ታላላቅ የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች ጋር ስብሰባ አካሂደዋል። ቅዱስነታቸው ከተቋማቱ መሪዎች ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ “በዚህች ምድር ላይ በምናደርገው ጉዞ ሁላችንም ፍቅርን የተጠማን፥ ደስታንም በመፈለግ ላይ የምንገኝ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ነን” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዓለማችን ውስጥ ታላላቅ የሚባሉ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ጋር በሞንጎሊያ መዲና ኡላምባታር እሑድ ነሐሴ 28/2015 ዓ. ም. ባደረጉት ጥልቅ መንፈሳዊ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ በሞንጎሊያ አብላጫ ቁጥር የሚይዘውን የቡዳ እምነት ተከታይ ማኅበረሰብን በመጥቀስ፥ ሁሉም ሃይማኖቶች ተስማምተው እንዲኖሩ አሳስበው፥ የጋራ ጥቅምን በማስከበር ጥላቻን፣ ዓመፅን እና ጦርነትን የሚቀሰቅሱ የተቃራኒ ርዕዮተ ዓለማም ሥርዓቶችን እንዲቃወሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ
ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የወንድማማችነት እና እርስ በርስ የመገናኘት ባሕል እንዲያድግ በማለት ያቀረቡት አስቸኳይ ጥሪ ልቡን የነካው የሞንጎሊያ ሕዝብ፥ ለ70 ዓመታት ያህል በኮሚኒስት አገዛዝ የተጨቆነ ቢሆንም፥ በአገሪቱ የሚገኙ የተለያየ እምነት ያላቸው የአገሪቱ ዜጎች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ከካቶሊክ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር እሑድ ነሐሴ 28/2015 ዓ. ም. በተፈጸመው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለመገኘት ወደ ዋና ከተማው ኡላንባታር ሲጓዙ ታይተዋል

በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥር ዓት የተገኙ ምዕመናን እና እንግዶች
በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥር ዓት የተገኙ ምዕመናን እና እንግዶች

የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት

እሑድ በተካሄደው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ የተሳተፉት የልዩ ልዩ እምነት ተከታዮች በኅብረት ሲዘምሩ፣ በዕለቱ የቀረቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት በትኩረት በማድመጥ የጸሎት ሥርዓቱን የተከታተሉ ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ምንባብ ላይ በማስተንተን ያቀረቡትን ስብከት በጽሞና በመከታተል የቅዱስ ቁርባን ጸሎትን በጸጥታ ሲያቀርቡ እንደ ነበር ተገልጿል።

በቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የቡዳ እምነት መነኮሳትም በብርቱካናማ ቀለም ልብሶቻቸው ደማቀው ታይተዋል። የመስዋዕተ ቅዳሴውን ሥነ-ሥርዓት የተካፈሉት 2,000 ካቶሊካዊ ምዕመናን፣ በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ያልተገኘውን እያንዳንዱን የአገሪቱን ካቶሊካዊ ምዕመን ወክለው መገኘታቸው ተነግሯል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የእስያ አኅጉር አገር በሆነች ሞንጎሊያ ውስጥ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፥ ከፊሊፒንስ፣ ከቬትናም እና አልፎ ተርፎም ከቻይና የመጡ በርካታ ካቶሊካዊ ምዕመናን ተካፋይ ሆነዋል። በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የቪዬትናም ካቶሊካዊ ነጋዲያን፥ የባሕላቸው መለያ የሆነውን እና በሮዝ ቀለም የተዋበውን ባሕላዊ ባርኔጣ በማድረግ ለቅዱስነታቸው ልዩ የሙዚቃ ዝግጅት ማቅረባቸው ተመልክቷል። የቻይና ካቶሊካዊ ምዕመናንም በበኩላቸው ወደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፊት ሲቀርቡ በአድናቆት እና በደስታ ቀይ ባንዲራቸውን ሲያውለበልቡ ታይተዋል።

ከሁለት ቀናት የመኪና ጉዞ በኋላ ወደ ኡላንባታር የደረሱት እና በሩስያ የሳይቤሪያ ግዛት ነዋሪ የሆኑ ሁለት መነኮሳት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቅዳሜ ነሐሴ 27/2015 ዓ. ም. ከካህናት እና ከሃይማኖት አባቶች ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ ተገኝተው ቅዱስነታቸውን ማነጋገራቸው ታውቋል። 

ከሩስያ ሳይቤሪያ ግዛት የመጡ ሁለት መነኮሳት
ከሩስያ ሳይቤሪያ ግዛት የመጡ ሁለት መነኮሳት

ሰላምን እንደምትፈል የተናገረችው እህት ቬራ፥ ለሰላም በመጸለይ ላይ እንደምትገኝ ለቅዱስነታቸው ተናግራለች።

05 September 2023, 17:44