ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በኅብረተሰቡ ለተገለሉት መጸለይ እና ዕርዳታን ማድረግ እንደሚገባ አሳሰቡ

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዓለም አቀፉ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት በኩል ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፥ “ቤት የሌለው አንድ ድሃ መንገድ ዳር ሞቶ ቢገኝ የዜና ሽፋን ሆኖ ሲቀርብ አይታይም” ብለው፥ በአስተባባሪ ጽሕፈት ቤቱ በኩል ባቀረቡት የጸሎት ሃሳብ፥ በማኅበረሰቡ ተገልለው የሚኖሩትን ሰዎች በጸሎት እንድናስታውሳቸው ጠይቀዋል።

በዜና ማሰራጫዎች የተዘነጉ ሰዎች

የመስከረም ወር የቪዲዮ መልዕክት ትኩረቱን ያደረገው፥ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ዘንድ የተረሱትን ሰዎች የሚያስታውስ ሲሆን፥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት ጋር የቀረቡት ምስሎች በካናዳ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በኬንያ፣ በካሜሩ እና በሕንድ የእግረኛ መንገዶች ላይ ብቻቸውን ወይም በቡድን ሆነው የሚታዩ መጠለያ የሌላቸው ድሆችን የሚያሳይ እንደሆነ ተመልክቷል። የቪዲዮ ምስሉ ከዚህም በተጨማሪ ቀኑን ሙሉ መኪናን እያጠቡ የሚያሳልፉ የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎች፣ በሳን ሳልቫዶር የትራፊክ መብራቶች በሚገኙባቸው መንገዶች፣ በስፔን፣ በፊሊፒንስ እና በመካከለኛው አሜሪካ አገራት ውስጥ የሚገኙ የአካል ጉዳተኞች፣ በካናዳ ቫንኩቨር ሰማይ ጠቀስ ፎቆች አቅራቢያ፣ በአርጄንቲና ቦነስ አይረስ እና በብራዚል ሪዮ ዴ ጄኔሮ ሕንፃዎች አቅራቢያ በሚገኙ የገጠር ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ድሆችን የሚያሳይ እንደሆነ ታውቋል።

በኅብረተሰባችን ውስጥ ከማኅበራዊ ሕይወት የተገለሉ ሰዎች ቁጥር ከምናስበው በላይ ሲሆን፥ በእርግጥ እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሠረት ከ 700 ሚሊዮን በላይ፥ ይህም 10% የሚሆነው የዓለማችን ሕዝብ በከፋ የድህነት ሕይወት ውስጥ እንደሚገኝ ታውቋል።  እንደ ጤና አጠባበቅ፣ ትምህርት፣ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና የአካባቢ ንጽህና የመሳሰሉ መሠረታዊ ፍላጎቶችን በማግኘት ረገድ ትልቅ ችግር እንዳለባቸው ታውቋል። በኢንዱስትሪ የበለጸጉ አገሮችን ጨምሮ ወደ 1.6 ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በበቂ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ እንደማገኙም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አክሎ አስታውቋል። በተመሳሳይም ከዓለም የጤና ድርጅት የወጡ ዘገባዎች እንዳመላከቱት፥ ከስምንት ሰዎች አንዱ የአእምሮ ሕመም እንዳለበት እና 16 በመቶው የዓለም ሕዝብ ከባድ የአካል ጉዳት እንዳለበት ገልጿል።

ከመራራቅ ይልቅ በእንግድነት የመቀባበል ባሕልን ማሳደግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በወርሃዊ የቪዲዮ መልዕክታቸው፥ በዓለማችን ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወንዶች እና ሴቶች ከፍጆታ ቃዎች ጋር ሲነፃፀሩ ምንም ዋጋ እንደሌላቸው፥ የግድ የለሽነት ባሕል ሕይወታችንን፣ ከተሞቻችንን እና አኗኗራችንን እንዲቆጣጠረው እንዴት ፈቀድን?" በማለት መጠየቃቸውን ቀጥለዋል። ዓይናችን እነዚህን ሁኔታዎች ከመመልከት ይልቅ ወደ ሌላ አቅጣጫ መመልከትን መርጧል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፡ “በድህነት፣ በሱሶች፣ በአእምሮ ሕመም ወይም በአካል ጉዳት ምክንያት ሰዎችን ከማኅበረሰቡ እንዲገለሉ ማድረግን እንድናቆም” አሳስበዋል።

“በድህነት ሕይወት እና በተለያዩ ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የሚገኙትን ሰዎችን በመቀበል ላይ እናተኩር" በማለት ያሳሰቡት ርዕሠ ኪቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የእኛ እገዛ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች በመርዳት   የእንግዳ ተቀባይነት ባሕልን በማሳደግ፥ መጠለያ ለሌላቸው መጠለያ የመስጠት እና ፍቅርን የመስጠት ባህል ማሳደግ እንደሚገባ አደራ ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ምዕመናን በሙሉ በጸሎት እንዲተባበሩ ጠይቀው፥ “ከሰው ልጅ በታች በሆኑ የኑሮ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተቋማቱ ችላ እንዳይላቸው” በማለት አሳስበዋል።

በእንግድነት መቀባበል ከዕርዳታዎች ሁሉ በላይ ነው!

“ጸሎት በልብ ውስጥ የተሰወረውን ወደ ብርሃን ያወጣል፤ በማኅበረሰብ ተገልለው የሚኖሩ እና የማስናስተውላቸው ሰዎች በልባችን ውስጥ ቦታን ማግኘት አለባቸው፤ በቤተ ክርስቲያን ልብ ውስጥ ናቸው፤ ቤተ ክርስቲያን የሥጋ ልብ እንጂ የድንጋይ ልብ የላትም፤ የድንጋይ ልብ ሰዎችን ሲያገል የሥጋ ልብ ግን ሰዎችን በደስታ ይቀበላል” ያሉት በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለመስከረም ወር እንዲሆን በማለት ባቀረቡት የጸሎት ሃሳብ ላይ በሰጡ አስተያየት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጸሎት የማስተማር ኃይል እንዳለው ስለሚያውቁ፥ በጸሎት አማካይነት በእንግድነት የመቀባበል ባሕልን እንድናዳብር ጋብዘውናል።

‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ የማዕዘን ራስ ሆኖአል’ የሚለውን የቅዱስ ወንጌል ክፍል የጠቀሱት፥ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ፣ ይህ መልዕክት ዛሬም ቢሆን በኑሮ ውድነት ለተጎዱት እና በግድ የለሽነት ባሕል ምክንያት በማኅበረሰብ ለተገለሉት ሰዎች ጠንካራ እና ተአማኒነት ያለው ድምጽ ነው ብለዋል። በእንግድነት መቀባበል ከመርዳት ሁሉ በላይ እንደሆነ፥ ይህ ማለት ሌላውን ሰው በእኛ ደረጃ ማስቀመጥ፣ ያጣናቸውን እህቶች ወይም ወንድሞች እንደገና ማግኘት ማለት እንደሆነ ገልጸው፥ በጸሎት ኃይል አንድ አካል እንደምንሆን አስረድተዋል።

"በእንግድነት የመቀባበል ባሕል"

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ አስተባባሪ ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመስከረም ወር የጸሎት ሃሳብን መሠረት በማድረግ በሰጡት አስተያየት፥ “በግዴለሽነት ባሕል ምክንያት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ተጨባጭ መፍትሄን ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው? ብለው ጠይቀው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ድህነትን እና መገለልን በተለየ መንገድ እንድንቀርብ መጋበዛቸውን ገልጸው፥ ይህ ማለት መጸለይ ማለት እንደሆነ፣ ጸሎት ልባችንን እና አመለካከታችንም ሊለውጥ እንደሚችል፥ በተለይም ለድኅነት ሕይወት ለተጋለጡት ልባችንን እንድንከፍት ያግዘናል ብለዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ አስተባባሪ ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ በመጨረሻም፥ በእንግድነት የመቀባበል ባሕል አድጎ፥ መጠለያ የሌላቸው መጠለያን እንዲያገኙ፥ የሰው ፍቅር እና እንክብካቤ የሚያሻቸው ፍቅርን ያገኙ ዘንድ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በጸሎት እንድንተባበር አሳስበዋል።

06 September 2023, 15:28