ፈልግ

2023.09.04 Santa Maria Maggiore 2023.09.04 Santa Maria Maggiore 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከሞንጎሊያ ሐዋርያዊ ጉብኝት መልስ ለእመቤታችን ቅድስት ማርያም ምስጋና አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በሞንጎሊያ ከነሐሴ 25-29/2015 ዓ. ም. ያካሄዱትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ወደ ሐዋርያዊ መንበራቸው በሰላም ተመልሰዋል። ለሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ድጋፍ ተማጽነው ወደ ሞንጎሊያ የተጓዙት ቅዱስነታቸው፥ ወደ ሮም ሲመለሱ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ በመገኘት የምስጋና ጸሎት አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በተለያዩ አገራት የሚያደርጓቸውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመጀመራቸው አስቀድመው ሆነ ፈጽመው ሲመለሱ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ደርሰው የድጋፍ እና የምስጋና ጸሎት እንደሚያቀርቡ ይታወቃል። በሞንጎሊያ መዲና ኡላንባታር ያደረጉትን የአራት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ሰኞ ነሐሴ 29/2015 ዓ. ም. ከሰዓት ወደ ሮም ሲደርሱ ወደ ባዚሊካው በመሄድ፥ ቅድስት ድንግል ማርያም ላደረገችላቸው ጥበቃ እና ድጋፍ የምስጋና ጸሎት ካቀረቡ በኋላ ወደ ቫቲካን ሐዋርያዊ መንበራቸው በሰላም መመለሳቸውን የቫቲካን መግለጫ አስታውቋል።  

ከሞንጎሊያ ያመጡት ልዩ የአበባ እቅፍ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያላቸውን ልዩ ፍቅር ለመግለጽ ከሞንጎሊያ ይዘው የመጡትን የአበባ እቅፍ በመንበረ ታቦቱ አካባቢ በሚገኝ ጥንታዊ የእመቤታችን ቅድስት ማርያም መንፈሳዊ ምስል ሥር አኑረዋል።

የአበባ እቅፉ ቅዱስነታቸው ጉዞአቸውን ወደ ሮም ለመጀመራቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ከሞንጎሊያ ሕዝብ የቀረበላቸው የምስጋና መግለጫ ሰጥታ እንደ ነበር ታውቋል። ይህን የአበባ እቅፍ ስጦታ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቀረቡት የምስጋና ጸሎት ጋር፥ የእስያ አገር በሆነች ሞንጎሊያ ለአራት ቀናት ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ያገኟቸውን በርካታ ሰዎች በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

05 September 2023, 10:12