ፈልግ

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሞንጎሊያ ሐዋርያዊ ጉብኝ የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሞንጎሊያ ሐዋርያዊ ጉብኝ   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ባሕልን የሚያስረሱ ርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰቦች አደገኛ እንደሆኑ አስጠነቀቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሞንጎሊያ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው በመመለስ ላይ እያሉ በርካታ ርዕሠ ጉዳዮችን መሠረት በማድረግ ከጋዜጠኖች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል። በቅርቡ በቫቲካን የሚካሄደውን ሲኖዶሳዊ ጠቅላላ ጉባኤን ጨምሮ ለቀረቡት ሌሎች ጥያቄውች ምላሽ የሰጡት ቅዱስነታቸው፥ በቤተ ክርስቲያን ሆነ በዓለማችን ውስጥ ባሕልን የሚያስረሱ አደገኛ የርዕዮተ ዓለም አስተሳሰቦችን መጠንቀቅ እንደሚገባ አሳስበው፥ የሩሲያ ካቶሊክ ወጣቶች የባሕል ቅርሶቻቸውን እንዳይረሱ በማለት የለገሱትን ምክርንም በድጋሚ አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተለያዩ አገራት የሚያካሂዱትን ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝቶችን ፈጽመው ወደ ሮም ሲመለሱ፥ አብረዋቸው ከተጓዙ ጋዜጠኞች ለሚቀርብላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጡበት ይታወቃል። በዚህ መሠረት ቅዱስነታቸ በሞንጎሊያ ያደረጉትን በ43ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ወደ ሮም በመመለስ ላይ እንዳሉ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ሞንጎሊያን የመጎብኘት ሐሳብ የመጣው በአገሪቱ የሚገኙ በቁጥር ጥቂት የሆኑት ካቶሊካዊ ምዕመናን ሳስብ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በሞንጎሊያ ሐዋርያዊ ጉብኝት ያደረጉበት ምክንያት በአገሪቱ የሚገኘውን ካቶሊካዊ ማኅበረሰብን ለመጎብኘት እና እንዲሁም ከሕዝቡ ታሪክ እና ባሕል ጋር ለመተዋወቅ እንደሆነ አስረድተዋል።

ወንጌል የሚሰበከው ሰዎችን ሃይማኖታቸውን ወይም የፖለቲካ አቋማቸውን እንዲለውጡ ለማድረግ በመሞከር እንዳልሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ የተናገሩትን በመጥቀስ፥ ወንጌል የሚሰበከው እምነትን ማሰራጨት የሚቻለው ሃይማኖትን በማስለውጥ ሳይሆን፥ በተጨባጭ በሚያሳዩት ተግባር በመማረክ እንደሆነ አስረድተዋል። ባሕልን ከወንጌል ምስክርነታ ጋር በማዛመድ የሚቀርብ የወንጌል ስብከት መኖሩን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ክርስቲያኖች ክርስቲያናዊ እሴቶችን ከባሕላቸው ጋር በማዛመድ ስለሚገልጹ በባሕል እና በስብከተ ወንጌል መካከል መወራረስ እንደሚኖር ገልጸው፥ ይህ የሌለበት ስብከተ ወንጌል በተቃራኒው የሃይማኖት ቅኝ ግዛትን እንደሚያስከትል አስረድተዋል።

በዚህ መሠረት በሞንጎሊያ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋና ዓላማ ከሕዝቡ ጋር ለመተዋወቅ፣ ለመነጋገር፣ ባሕላቸውን ለመቀበል እና ቤተ ክርስቲያናቸውን ከባሕላቸው ጭምር በማክበር አብረዋቸው ለመጓዝ ስለነበር በውጤቱም መርካታቸውን ገልጸዋል። የሞንጎሊያ መዲና ኡላንባታር ከባሕር ርቃ የምትገኝ አገር ዋና ከተማ እንደሆነች እና በሁለት ታላላቅ ኃያላን አገራት ሩሲያ እና ቻይና መካከል የምትገኝ እንደሆነች የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ ሞንጎሊያ ከሁለቱም ሃያላን ጎረቤት አገራት ጋር ለመነጋገር እና ለመወያየት መሞከር ከሁለቱም ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖር በማድረግ ዓለም አቀፋዊነትን በማሳደግ፥ እሴቶቻቸውን በመለዋወጥ ወደ ውይይት የሚያስገባ መንገድን ለመፍጠር እንደሆነ ተናግረው፥ ዛሬ በሥልጣኔዎች መካከል የሚነሳው ግጭት የሚፈታው በውይይት ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ የሰላም መልዕክተኛ አድርገው በመሰየም ሞስኮን፣ ኪየቭን፣ አሜሪካን እና ቤጂንግንም እንዲጎበኙ ተልዕኮ የሰጡት፥ ብጹዕ ካርዲናል ዙፒ ታላቅ የውይይት እና የሁለንተናዊነት ራዕይ ያላቸው በመሆናቸው፥ የግል ታሪካቸው በሞዛምቢክ ውስጥ ሰላምን ለማስፈን ያደረጉትን ጥረት የሚያካትት መሆኑን ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

ከቻይና ጋር ያለው ግንኙነት እጅግ መልካም እና የተከበረ መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ በግል ለቻይና ሕዝብ ትልቅ አድናቆት እንዳላቸው ተናግረው፥ የመልካም ግንኙነት መንገዶች ክፍት መሆናቸውን ገልጸው፥ የጳጳሳትን ሹመት በተመለከተ ከቻይና መንግሥት እና ከቫቲካን ጋር ለረጅም ጊዜ ሲሠራ የቆየ የጋራ ኮሚሽን መኖሩን ገልጸው፥ ወደ ቻይና ዩኒቨርሲቲዎች እየተጋበዙ የተለያዩ ኮርሶችን የሚሰጡ አንዳንድ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ካኅናት መኖራቸውን አብራርተዋል። ይህን የሁለቱን አገራት ወዳጃዊ ግንኙነት በኮሚሽን ደረጃ የሚመሩት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን መሆናቸውን አስረድተዋል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከቬትናም ጋር ጥሩ የውይይት ተሞክሮዎች እንዳላት የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ በውይይቱ መካከል የጋራ መተሳሰብ እንዳለ ገልጸው፥ ሁለቱም ወገኖች እርስ በርስ ለመረዳዳት እና በኅብረት ወደፊት ለመራመድ ምቹ መንገዶችን ለማመቻቸት ጥሩ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረው፥ በቬትናም ውስጥ ችግሮች እየተወገዱ መምጣታቸውን ገልጸዋል። ከአራት ዓመታት በፊት የቬትናም የፓርላማ አባላት ቡድን በቫቲካን ጉብኝት ማድረጉን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከእነርሱም ጋር ጥሩ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በቅርቡ ከሩስያውያን ካቶሊካዊ ወጣቶች ጋር መወያየታቸውን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ወጣቶቹ የባሕል ቅርሶቻቸውን እንዳይረሱ በማለት የለገሱትን ምክር አስታውሰው፥ የውይይታቸው የመጀመሪያው ነጥብም ስለ ባሕል ውርስ እንደ ነበር እና ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት በአያቶች እና በልጅ ልጆች መካከል ውይይትን በመፍጠር የልጅ ልጆች ከአያቶቻቸው ቅርሶችን መውሰድ እንደሚገባ ምክር መለገሳቸውን ገልጸዋል። ሁለተኛው ነጥብ የትሩፋትን ትርጉም መግለጽ እንደ ነበር የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ ከሩስያ ሊሚገኝ የሚችል ውርስ እጅግ መልካም እንደሆነ ተናግረው፥ ሩስያ ውስጥ የምናገኛቸው ስነ-ጽሁፎች እና የሙዚቃ ድርሰቶች፥ የዶስትቪስኪ ድርሰቶች ሲመለከቷቸው ሰብዓዊነትን በማስመልከት ጥልቅ መልዕክቶችን የያዙ መሆናቸውን ተናግረዋል። ሦስተኛው ነጥብ ምናልባትይህን ያህል አስፈላጊ ባይሆንም ነገር ግን ስለ ታላቋ ሩሲያ የሚናገር፥ በመልክዓ ምድር አቀማመጥ ሳይሆን ባሕሏን በተመለከተ በትምህርት ቤት የተማሯቸውን ፒተር ቀዳማዊን እና ካትሪን ዳግማዊትን ጠቅሰዋል።

ወጣት ሩሲያውያን ቅርሶቻቸውን እንዲንከባከቧቸው፥ ይህም ማለት ከሌላ ቦታ መግዛት እንደሌለባቸው፥ ታላቋ ሩስያ ምን ዓይነት ቅርስ ትታልናለች? የሩስያ ባሕል ውበት እና ጥልቀት ምን ያህል ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች መድገም እንደሚገባ ተናግረው፥ ሩስያ የጨለማ ዓመታትን ያቋረጠች ብትሆንም ትሩፋቶቿ ሁልጊዜ ሳይበላሹ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

እውነት ነው ርዕዮተ ዓለማዊ ጫናን ለማሳደር የሚፈልግ ኢምፔሪያሊዝም ሥርዓት መኖሩን የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ የሕዝቦች ባሕል ተነጥቆ ወደ ርዕዮተ ዓለማዊነት ሲቀየር መርዝ እንደሚሆን እና ባሕል ጥቅም ላይ የሚውል ቢሆንም ነገር ግን ወደ ርዕዮተ ዓለም ሊዛባ እንደሚችል፥ የአንድን ሕዝብ ባሕል ከአንዳንድ ፈላስፋዎችን እና ፖለቲከኞችን ለይቶ ማወቅ እንደሚገባ ተናግረው፥ ይህን ምክረ ሃሳብ ከዓለማዊ እና ከቤተ ክርስቲያን ተቋማት ጭምርም እንደሚጋሩ ገልጸዋል። ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍሉ ርዕዮተ ዓለሞች መኖራቸውን የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ እነዚህ ርዕዮተ ዓለሞች ቤተ ክርስቲያንን ከመንፈስ ቅዱስ ለመለየት ተጽኖ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል። “ርዕዮተ ዓለም ሃሳብ ብቻ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ነገር ግን ርዕዮተ ዓለም ጥንካሬን አግኝቶ ወደ ፖለቲካ አጀንዳነት በመለወጥ አብዛኛውን ጊዜ ወደ አምባገነናዊ ሥርዓት እንደሚሸጋገር ተናግረዋል።

ወጣቶች ስለ ወደፊቱ ጊዜያቸው ማሰባቸው መልካም ሆኖ ሳለ ነገር ግን ርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰብ ሲገባበት ወይም የፖለቲካ ጫና ሲደረግበት ጥቅም ላይ ከመዋል ይልቅ ውድቀት እንደሚያጋጥመው ገልጸው፥ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” የሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ሁለተኛው ክፍል መስከረም 23/2016 ዓ. ም. ይፋ እንደሚሆን አብሥረው፥ ይህም ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ጀምሮ ምን እንደተከሰተ የሚዳስስ እና እስከ ዛሬ ድረስ ምን ፍሬያማ ሥራዎች እንደተሠሩ፥ እስካሁን ያልተፈቱ አንዳንድ ችግሮችን ለይቶ እነሱን ለመፍታት አስቸኳይ ጥሪን የሚያቀርብ መሆኑን ተናግረዋል።

በመጭው ጥቅምት ወር በሮም የሚካሄደውን ሲኖዶሳዊ ጉባኤን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ርዕዮተ ዓለም በሲኖዶሳዊ ሂደት ውስጥ ቦታ እንደሌለው ተናግረው፥ ሲኖዶሳዊ ሂደት ለውይይት ቦታን እንደሚሰጥ እና እንደ ወንድሞች እና እህቶች እርስ በርስ በመነጋገር ስለ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት የሚወያዩበት መድረክ መሆኑን አስረድተዋል። በመቀጠልም “የሲኖዶሳዊነት ጉዞ የእኔ ውሳኔ አይደለም” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ ወስነው ማስጀመራቸውን በማስታወስ፥ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሲያበቃ የምዕራቡ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የሲኖዶሳዊነትን ልኬት ያጣች ብትሆንም በምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ግን አሁንም ድረስ መኖሩን ገልጸዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ ውሳኔ ሃምሳኛ ዓመት ሲሞላው ሲኖዶስ ምን እንደሆነ እና እንዴት እንደቀጠለ የሚያሳይ ሠነድ ፈርመው ማሳተማቸውን ተናግረዋል።

 

 

05 September 2023, 17:27