ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ 'የምሕረት ቤት' የተሰኘውን የበጎ አድርጎት መስጫ ተቋም መርቀው ከፈቱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሞንጎሊያ መዲና ኡላንባታር የሚገኘውን ‘የምሕረት ቤት’ መርቀው ሲከፈቱ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች አባላት ንግግር አድርገዋል። የተቸገሩትን ለመርዳት ያላቸውን ቁርጠኝነት በማክበር የተናገሩ ሲሆን፥ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኞ ነሐሴ 29/2015 በኡላንባታር ከተማ ባደረጉት የመጨረሻ ቀን ጉብኝታቸው፥ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተወካዮች ፊት ቆመው፣ የሞንጎሊያን ባሕላዊ ዘፈን እና ውዝዋዜን ያካተተ ልባዊ አቀባበል ላደረጉላቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል። “ተርቤ አብልታችሁኛል፣ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል” ከሚለው የኢየሱስ ቃል በመነሳት ንግግራቸውን የጀመሩት ቅዱስነታቸው፥ "በዚህ ቃል ጌታችን ኢየኡሱ ክርስቶስ በዓለማችን ውስጥ መገኘቱን እና በመጨረሻው የፍርድ ቀን ወደ መንግሥቱ በከፍተኛ ደስታ የምንገባበትን ሁኔታ እንድናውቅ መስፈርቱን ይሰጠናል" ብለዋል።

ሞንጎሊያ ውስጥ ያለች ቤተ ክርስቲያን

በመቀጠልም በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያለውን የረዥም ጊዜ የበጎ አድራጎት ወግ በማጉላት፥ የጥንቶቹ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ያሳዩት ቁርጠኝነት ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎቷን በኅብረት፣ በቅዳሴ እና በምስክርነት ምሰሶዎች ላይ ለመገንባት እንዴት እንደረዳው አጽንኦት ሰጥተዋል። የበጎ አድራጎት መንፈስ በሞንጎሊያ ሕያው በሆነችው ትንሿ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዴት እንደሚንፀባረቅ ገልጸው፣ ይህም የኅብረት፣ የጸሎት፣ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ አገልግሎት እና የእምነትን ዘላቂ እሴት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

የምህረት ቤት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀጥለውም ትኩረታቸውን ወደ “የምሕረት ቤት” አዙረው፥ ይህም ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሌሎች ያላትን ተቆርቋሪነት የሚያሳይ ተጨባጭ መግለጫ ነው ብለው፥ "ለጎረቤቶቻችን የምናደርገው ልግስና የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከምሥረታው ጀምሮ ለማገልገል ያነሳሳ መሆኑን በማስረዳት፥ “ከእነዚህ መነሻዎች ለተፈጠሩት በርካታ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ውጥኖቹ ዕውቀታቸውን፣ ልምዳቸውን፣ ሃብታቸውን እና በተለይም ፍቅራቸውን ለአገልግሎት በማዋል፥ ከብዙ አገራት የመጡ ሚስዮናውያን ቁርጠኝነታቸውን ለሞንጎሊያ ማኅበረሰብ ማሳየት ቀጥለዋል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የ ‘ምህረት ቤትን’ ሁሉም የሚቀበሉበት ቦታ እንደሆነ ሲገልጹ፥ በጎ ፈቃደኞች ወደፊት እንዲራመዱ እና ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ አገልግሎትን እንዲያበረክቱ በማለት አሳስበዋል። የበጎ ፈቃደኝነት ሥራ ለሃብታሞች ብቻ ሳይሆን ለሌሎች በፍቅር ተነሳስተው ጊዜያቸውን እና ንብረታቸውን ለሌሎች ለማዋል ለሚመርጡ ትሑት ሰዎች መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል።

የውሸት አፈ ታሪኮችን አለመቀበል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በበጎ አድራጎት ሥራ ዙሪያ የተለመዱ ብዙ አፈ ታሪኮችን ውድቅ አድርገው፥ “በመጀመሪያ በበጎ ፈቃድ ሥራ ላይ መሠማራት የሚችሉት ሃብታሞች ብቻ ናቸው” የሚለው ተረት እንደሆነ ተናግረው፥ “እውነታው ግን በተቃራኒው መልካም ለመሥራት ሃብታም መሆን አስፈላጊ እንዳልሆነ በማስረዳት፥ ይልቁንም ሁልጊዜ ማለት ይቻላል ጊዜያቸውን እና ችሎታቸውን ለሌሎች ማዋልን የሚመርጡት ትክክለኛ ሰዎች መሆናቸውን እና ሌሎችን ለመንከባከብ ልጋስ መሆን ያስፈልጋል" ብለዋል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ ዕድገትን ለማስተዋወቅ የምታሳየው ቁርጠኝነት በሃይማኖታዊ ተቋም እምነት የሚመራ ሳይሆን የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን የተጠራው የእያንዳንዱ ሰው ግዴታ እንደሆነ አስረድተዋል።

በጎ አድራጎት መቼም ቢሆን ንግድ መሆን የለበትም

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም፥ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሥራ መሆን እንደሌለበት አሳስበው፥ "የበጎ አድራጎት ሥራዎች ሙያዊ ብቃትን እንደሚጠይቁ እና ወደ ንግድ መቀየር እንደሌለባቸው በማሳሰብ ይልቁንስ፣ ምንም ዓይነት ክፍያ፥ ምንም ይሁን ምን የተቸገሩ ሰዎችን በርኅራኄ ለማዳመጥ ዝግጁ የሆኑ ሰዎች የሚገኙበት የበጎ አድራጎት ሥራ ሆነው ትኩስነታቸውን ማቆየት አለባቸው" በማለት በአጽኖት ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ ከገንዘብ ጥቅም ይልቅ ለእግዚአብሔር ባላቸው ፍቅር የተነሣ ሕሙማንን በመንከባከብ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ምሳሌ የሆነችውን የካልካታዋ ቅድስት ቴሬዛን አስታውሰው፥ የዚህ ዓይነቱ ፍቅር የምሕረት ቤት መሪ ኃይል እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የርኅራኄን ልብ ለማግኘት መጸለይ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማጠቃለያው ንግግራቸው ላይ፥ በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ለተሳተፉት ሁሉ ምስጋናቸውን እና ቡራኬአቸውን አቅርበው፥ በበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች እንዲጸልዩላቸው የጠየቁ ሲሆን፥ የሞንጎሊያ ዜጎች የበጎ ፈቃድ ሥራን ተቀብለው ለጋራ ጥቅም በማዋል የመተሳሰብ ባሕላቸውን እንዲያሳድጉ ጠይቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሞንጎሊያ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የመጨረሻ ሕዝባዊ ዝግጅት ወቅት፣ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር የግል እና የኅብረተሰብ ዕድገት መንገድ እንደሆነ በመልዕክታቸው ገልጸዋል።

 

 

 

 

04 September 2023, 19:20