ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የኮሪያ መንፈሳዊ ነጋዲያንን በቫቲካን በተቀበሏቸው ወቅት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የኮሪያ መንፈሳዊ ነጋዲያንን በቫቲካን በተቀበሏቸው ወቅት   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ወንጌል መከፋፈልን እና መሰናክሎችን እንደሚያሸንፍ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችኮስ፥ የቅዱስ አንድሪው ኪም ታጎን ሐውልት በቫቲካን ውስጥ ባቆሙበት ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የኮሪያ ክርስቲያኖች መከፋፈልን በወንጌል ተስፋ እንዲያሸንፉ ብርታትን ተመኝተው፥ ቅዱስ ወንጌል መከፋፈልን እና መሰናክሎችን ሊያሸንፍ እንደሚችል ተናገርዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ "ለመላው ዓለም የወንጌል ተስፋ ለመስጠት ያለን ጉጉት፥ ልባችንን በመክፈት ብዙ መሰናክሎችን እንድናልፍ ይረዳናል።" ብለዋል። ቅዱስነታቸው ይህን የተናገሩት ቅዳሜ መስከረም 5/2016 ዓ. ም. በቫቲካን ለተገኙት የደቡብ ኮሪያ መንፈሳዊ  ነጋዲያን እንደሆነ ታውቋል። የኮሪያ መንፈሳዊ ነጋዲያኑ ወደ ሮም የመጡት የአገራቸው የመጀመሪያ ካኅን እና ሰማዕት፥ የቅዱስ አንድሪው ኪም ታጎን ሐውልት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተባርኮ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የቆመበትን ዕለት ለማክበር እንደሆ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከመንፈሳዊ ነጋዲያኑ ጋር የተገናኙት የቅዱስ አንድሪው 177 ኛ የሰማዕትነት መታሰቢያ በዓል ላይ ሲሆን፥ ቅዱስነታቸው ሐውልቱን ቀርጾ ለዚህ ላበቃው ለፕሮፌሰር ማሪያ ኮ ጆንግ-ሂን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኮሪያ ወጣት እና ሕያው እምነት

በ6ኛው የእስያ ወጣቶች ቀን ላይ ለመገኘት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2014 ዓ. ም. በደቡብ ኮሪያ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉዞ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ፥ ቅዱስ አንድሪው ኪም ተወልዶ ባደገት ሥፍራ የሚገኘውን የሶልሜ ቤተ መቅደስ ጎብኝተው በተለይም ለኮሪያ እና ለኮሪያ ወጣቶች ጸሎት ማቅረባቸው አስታውሰው፥ የቅዱስ አንድሪውን ክርስቲያናዊ ምስክርነት በማወደስ፥ ቅዱስ አንድሪው የኮሪያ ቤተ ክርስቲያን ጥሪዋን ተቀብላ የእግዚአብሔርን ፍቅር እንድትገልጽ መጋበዙን ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው ክዚህም ጋር በማያያዝ የኮሪያ ምዕመናን በእግዚአብሔር እና በጎረቤት ፍቅር ለታነመ ለሕያው እምነት ስጦታ የተጠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሰማዕትነት ፊት የሚታይ የመንፈስ ልዕልና

ቅዱስ አንድሪው ኪም ተልዕኮውን በመንፈሳዊ ልዕልና በመወጣት፥ ለሚያጋጥመው አደጋ ሁሉ ሳይበገር፥ ስቃይንም ሳይፈራ ቅዱስ ወንጌልን ለሌሎች ለማዳረስ ከፍተኛ ምኞት እንደ ነበረው ገልጸው፥ የቅዱሱ አያት እና አባት ሁለቱም በሰማዕትነት እንደሞቱ እና እናቱም በልመና እንድትኖር መገደዷንም አውስተዋል። ቅዱስ አንድሪው ኪም፥ ክርስቲያኖች ሐዋርያዊ ቅንዓትን እንዲያዳብሩ በመጋበዝ፥ የቅዱስ ወንጌልን ፍሬ በደስታ ለማዳረስ መጠራታቸውን በተግባር አሳይቷል ብለዋል።

በወንጌል ውስጥ የሚገኝ አንድነት

በሰማዕታት ደም ላይ የታነጸች የኮሪያ ቤተ ክርስቲያን የምእመናኖቿን ተነሳሽነት ተገንዝባ ከሥሯ በመነሳት መታደስ እንዳለባት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተናግረው፥ የሐዋርያዊ አገልግሎት የትብብር አድማስን በማስፋት፣ የወንጌል ምስክርነትን በጋራ ለማስፋፋት ካህናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም ምእመናን በጋራ እንዲሠሩ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል። “ቅዱስ ወንጌል በክርስቲያኖች መካከል አንድነትን እንጂ ክፍፍልን አይፈጥርም” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ወንጌል በታሪክ ውስጥ ወደ እያንዳንዱ ባህል በየዋህነት እና በአገልግሎት መንፈስ ለመቅረብ እንደሚፈልግ አስረድተዋል።

ወጣቶች ሰፋ ያለ እይታን ይፈልጋሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኮሪያን ሕዝብ የሰላም ፍላጎት ለቅዱስ አንድሪው ኪም ታጎን በማቅረብ በኦፒየም ጦርነቶች ወቅት ቅዱስ አንድሪው በማካዎ ውስጥ ይማር እንደነበር አስታውሰው፥ በንግግራቸው ማጠቃለያ እንደ ጎሮጎሮሳውያኑ በ2027 ዓ. ም. የሚከበረው የሚቀጥለው የዓለም ወጣቶች ቀን በደቡብ ኮሪያ መዲና ሴኡል ውስጥ እንደሚሆን አስታውሰዋል።

"የወጣቶች ልብ ሰፊ ነው" ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ደቡብ ኮሪያ ውስጥ የሚገኙ ካቶሊክ አገልጋዮች ወጣቶችን እንዲንከባከቧቸው፣ እንዲፈልጉአቸው፣ እንዲያቀርቡአቸው፣ እንዲያዳምጧቸው እና የወንጌልን ውበት እንዲያበስሩላቸው፣ ወደ ውስጣዊ ነፃነት እንዲደርሱ እና ለእውነትና ለወንድማማችነት አስደሳች ምስክሮች እንዲሆኑ እንዲያበረታቷቸው” አደራ ብለዋል።

16 September 2023, 16:08