ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ "ለእግዚአብሔር ምሕረት ወሰን የለውም" በማለት አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት እሑድ መስከረም 6/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በዕለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ከተለያዩ አገራት ለመጡ ምዕመናን ባቀረቡት ስብከት፥ ለእግዚአብሔር ምሕረት ወሰን የለውም በማለት አስገንዝበዋል። ክቡራት ክቡራን፥ ቅዱስነታቸው በትናንትናው ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን በዕለቱ የወንጌል ክፍል በማስተንተን ያቀረቡትን ስብከት ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! በዛሬ ዕለት ከማቴ. 18፡21-35 ተውስዶ የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ይቅርታን ስለማድረግ ይነግረናል። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፥ ‘ጌታ ሆይ! ወንድሜ ስንት ጊዜ ቢበድለኝ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?’ ብሎ ጠየቀው። (ማቴ. 18፡21) ሰባት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሙሉነትን የሚያመለክት ቁጥር ነው። ስለዚህ ጴጥሮስ ጥያቄውን ለኢየሱስ ስያቅርብለት ይህንንም ግምት ውስጥ በማስገባት በለጋስነት ነበር። ኢየሱስ ግን በለጋስነቱ ከጴጥሮስ ስለሚበልጥ፥ ‘እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም’ ብሎ መለሰለት። (ማቴ. 18:22) ኢየሱስ ክርስቶስ ለጴጥሮስ ይህን ሲናገር፣ አንድ ሰው ይቅታን ሲያደርግ መመጠን ወይም ማስላት እንደሌለበት፥ ነገር ግን ሁሉንም ነገር ይቅር ማለት ጥሩ እንደሆነ እና ሁል ጊዜ ይቅር ማለት እንደሚገባ ለመግለጽ ነበር። እግዚአብሔር እኛን ዘወትር ይቅር እንደሚለን ማለት ነው። የእግዚአብሔርን ፍትህ የሚከተሉ ሰዎች ሁል ጊዜ ይቅር ማለት ይጠበቅባቸዋል። እግዚአብሔር ይቅር እንደሚለን ሁሉ ምዕመናንን የሚያናዝዙ ካህናት ሰዎችን ሁል ጊዜ ይቅር እንዲሉ ይህን ብዙ ጊዜ እናገራለሁ።

ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን እውነታ በድጋሚ ከቁጥር ጋር በተገናኘ ምሳሌ ያስረዳል። ንጉሡ ለአገልጋዩ ካዘነለት በኋላ የ10,000 መክሊት ዕዳ ይቅር አለው። ይህም ከመጠን ያለፈ እና እጅግ በጣም ብዙ ዋጋ ያለው፥ ክብደቱም ከ200 እስከ 500 ቶን የሚደርስ ብር ነው። ዕድሜ ልኩን ቢሠራ እንኳ ከፍሎ መጨረስ የማይችለው ዕዳ ነበር። ነገር ግን ጌታው ለአገልጋዩ አዘነለትና ለቀቀው፥ ዕዳውንም ተወለት። (ማቴ. 18:27) የእግዚአብሔርም ልብ እንዲህ ነው። እርሱ መሐሪ ስለሆነ ሁል ጊዜም ይቅር ይላል፤ የእግዚአብሔር ማንነት መዘንጋት የለብንም። እርሱ ለእኛ ቅርብ እና ርኅሩኅ ነው። የእግዚአብሔር መንገድ ይህ ነው። ነገር ግን ዕዳው የተሰረየለት ይህ አገልጋይ 100 ዲናር ዕዳ ላለበት አብሮት ላለው ወዳጁ ዕዳውን አልተወለትም። የአንድ መቶ ዲናር ዕዳም ትንሽ አልነበረውም። ምናልባት የሦስት ወር ደመወዝ ድምር ሊሆን የሚችል ብዙ ገንዘብ ነው። ይህ ማለት በሌላ አነጋገር ሌሎችን ይቅር ማለት ዋጋን እንደሚያስከፍል  ለማሳሰብ ነው። ነገር ግን ጌታው ይቅር ካለለት ከቀዳሚው የገንዘብ መጠን ጋር ሲስተካከል ፈጽሞ ሊወዳደር አይችልም።

ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያተላልፍ የፈለገው መልዕት ግልጽ ነው፡- የእግዚአብሔር ይቅርታ ሊገመት የማይችል እና ከምንም በላይ እንደሆነ ይናገራል። እግዚአብሔር ይቅር የሚለን ከፍቅሩ የተነሳ እንጂ ሌላ ልዩ ምክንያት የለውም። እግዚአብሔር አይገዛም፡ ነፃ ስጦታችን ነው። ልንከፍለውም አንችልም፤ ነገር ግን ወንድምን ወይም እህትን ይቅር ስንል እርሱን እንመስላለን። ስለዚህ ይቅር ማለት ልንመርጠው ወይም ይቅርታን ላለማድረግ የምንመርጠው ተግባር አይደለም። ይቅርታን ማድረግ ለክርስቲያኖች በሙሉ መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታ ነው። እያንዳንዳችን ይቅር መባላችንን መርሳት የለብንም። እግዚአብሔር ለእኛ ሲል እራሱን አሳልፎ ሰጥቷል። ይህን ከልቡ የማይጠፋ ምሕረቱን በምንም መልኩ መመለስ አንችልም። ነገር ግን ከቸርነቱ ጋር በማዛመድ እርስ በርሳችን ይቅር በመባባል፣ በዙሪያችን አዲስ ሕይወት በመዝራት ስለ እርሱ መመሥከር እንችላለን። ከይቅርታ ውጭ ምንም ተስፋ የለምና፤ ከይቅርታ ውጪ ሰላም የለም። ይቅርታ የጥላቻን አየር የሚያጠራ አስትንፋስ ነው። ይቅርታ የቂም መርዝ የሚፈውስ መድኃኒት፣ ቁጣን የሚያረግብ እና ማኅብረተሰብን የሚበክሉ ብዙ የልብ በሽታዎችን የሚፈውስ መንገድ ነው።

እስቲ መለስ ብለን እራሳችንን እንጠይቅ፡- ታላቅ የይቅርታ ስጦታን ከእግዚአብሔር እንደተቀበልኩ አምናለሁ? ሌሎችም ይቅርታን ማድረግ ባይችሉ፣ እኔም እራሴን ይቅር ማለት ባልችል፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ይቅር ሊለኝ ዝግጁ እንደሆነ በማወቄ ደስታ ይሰማኛል? እግዚአብሔር ይቅር ባይ ነው። እርሱ ይቅር እንደሚለኝ አምናለሁ? የእርሱን ምሳሌ በመከተል እኔ በተራዬ የበደሉኝን ይቅር ማለት እችላለሁ? በዚህ ረገድ ትንሽ ልምምድ የምናደርግበት አንድ ሃሳብ ማቅረብ እፈልጋለሁ። አሁን እያንዳንዳችን የበደሉንን ሰዎች ለማሰብ እንሞክር።  ለእግዚአብሔር ካለን ፍቅር በመታገዝ የበደሉንን ወንድሞቻቸን እና እህቶቻችን ይቅር እንበል። ይህ ለእኛ መልካም ይሆነናል። በልባችን ውስጥ ሰላምን ይፈጥርልናል።

የእግዚአብሔርን ጸጋ ተቀብለን እኛም እርስ በርሳችንም ይቅር እንድንባባል የምሕረት እናት የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን።”

 

18 September 2023, 16:37