ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “እኛ ክርስቲያኖች ጊዜን ሳናባክን የዘመናችንን ታላላቅ ችግሮች ለመፍታት ተጠርተናል" አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ መስከረም 2/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን አቅርበዋል። ከጣሊያን የተለያዩ ሀገረ ስብከቶች የመጡ ምዕመናን ጭምሮ ከልዩልዩ አገራት ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን ባቀረቡት አስተምህሮ፥ “ክርስቲያኖች በፍሬ አልባ ንግግር ጊዜያቸንን ሳናባክን በዘመናችን የሚታዩ ታላላቅ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት ተጠርተናል” ብለዋል።

ክቡራት እና ክቡራን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት ያቀረቡትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ከማቅረባችን አስቀድመን አስተንትኖ ያደረጉበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እናቀርብላችኋለን፥

“እንግዲህ ከሁሉ በፊት እንዲደረግ የምመክረውነገር ቢኖር ልመናና ጸሎት፥ ምልጃና ምስጋና ስለ ሰዎች ሁሉ እንዲደረግ እመክራለሁ፤ እንዲሁም እግዚአብሔርን በመምሰልና በተገባ አካሄድ ሁሉ፣ ጸጥታ በሰፈነበትና ሰላማዊ የሆነ ሕይወት እንዲኖረን ስለ ነገሥታትና በከፍተኛ ሥልጣን ላይ ስላሉ ሁሉ ጸሎት እናቅርብ። ይህም በአዳኛችን በእግዚአብሔር ፊት መልካም እና ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው። እርሱም ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲመጡ ፈቃዱ የሆነ አምላክ ነው።”  (1ኛ ጢሞ. 2: 1-4)

ክቡራት ክቡራን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመስከረም 2/2016 ዓ. ም. ያቀረቡትን ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! በዛሬው ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአችን ለወንጌል ስብከት የሚያነሳሱ ምስክርነቶችን መመልከት እንቀጥላለን። ዛሬ የላቲን አሜሪካ አገር ወደ ሆነው ቬነዙዌላ በመሄድ፥ ከምዕመናን ወገን የሆነውን የብፁዕ ሆሴ ግሬጎሪ ሄርናንዴዝ ሲስኔሮስ ታሪክ እንመለከታለን። ብፁዕ ሆሴ ግሬጎሪ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1864 የተወለደ እና ስለ እምነት ምንነት ከእናቱ የተማረ ሰው ሲሆን፥ እናቱ በጎነትን ከሕፃንነቱ ጀምሮ እንዳስተማረችው፥ እግዚአብሔርን አውቆ እንዲያድግ እና በጎነትን የሕይወት መመሪያ አድጋ እንደሰጠችው ተናግሯል።

በእርግጥም በጎነት ለብፁዕ ሆሴ ግሬጎሪ ሕልውናው እና የሕይወት መምሪያው ነበር፤ መልካም፣ ብሩህ እና ደስተኛ ባህሪ ያለው ብፁዕ ሆሴ ግሬጎሪ፥ ጥሩ የማሰብ ችሎታ የነበረው ሰው ነበር። ዶክተር፣ የዩኒቨርሲቲ መምህር እና ሳይንቲስት ለመሆን የበቃ ሰው ነበር። ነገር ግን ከሁሉ አስቀድሞ ለአቅመ ደካሞች ቅርብ ስለነበር በትውልድ አገሩ 'የድሆች ሐኪም' በመባል ይታወቅ ነበር። ከገንዘብ ባለጠግነት ይልቅ ከቅዱስ ወንጌል የሚገኘውን ሃብትን መረጠ፤ ሕልውናው በሙሉ የተቸገሩትን ሰዎች መርዳት ነበር። ይህን ሲያደርግ ታዲያ ሆሴ ግሬጎሪ፥ በድሆች፣ በበሽተኞች፣ በስደተኞች እና መከራ ውስጥ በሚገኙ ሰዎች መካከል ኢየሱስ ክርስቶስን ለማግኘት ቻለ። በሚኖርበት ዓለም ውስጥ ፈጽሞ ያላገኘውን እና በኋላም በብዛት እያገኘ የመጣው ስኬት፥ እርሱን ‘የሕዝብ ቅዱስ’፣ ‘የበጎነት ሐዋርያ’ እና ‘የተስፋ ልኡክ’ ተብሎ እንዲጠራ አደረገው።

ሆሴ ግሬጎሪ ትሁት፣ ደግ እና የተቸገሩትን የሚረዳ ሰው ነበር። እግዚአብሔርን እና ጎረቤቱን እንዲያገለግል በሚገፋፋ ውስጣዊ ፍላጎት የተሞላ ሰው ነበር። በዚህ ስሜት ተገፋፍቶ ገዳማዊና ካህን ለመሆን ብዙ ቢሞክርም በተለያዩ የጤና እክሎች ምክንያት ምኞቱን ለማሳካት አልቻለም ነበር። የተለያዩ የጤና ችግሮችም ወደዚህ ደረጃ እንዲደርስ አላደረጉትም። አካላዊ የጤና ችግሮች ቢኖሩትም በዚህ ሳይሸነፍ ነገር ግን የሌሎችን ፍላጎት ይበልጥ የሚረዳ ዶክተር በመሆን፥ በጎነትን ከሕይወቱ ጋር በማዛመድ አስፈላጊ ወደ ሆነው ነገር ይበልጥ ቀረበ። ሐዋርያዊ ቅንዓት የሚባለው እንግዲህ ይህ ነው። ሆሴ ግሬጎሪ የራስን ምኞት ከመከተል ይልቅ የእግዚአብሔርን ዕቅድ ለመፈጸም ወሰነ። እናም ብፁዕ ሆሴ ግሬጎሪ፥ ድውያንን በመንከባከብ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በተግባር እንደሚያውል ተገነዘበ። መከራ ውስጥ የሚገኙትን በማጽናናት፣ ለድሆች ተስፋን በመስጠት፣ እምነቱን በቃላት ብቻ ሳይሆን መልካም ምሳሌ በመሆን እንደሚመሰክር ተረዳ። ስለዚህ የሕክምና ሞያን እንደ ክህነት አገልግሎት ለመቀበል ወሰነ፥ ‘የሰውን ሕመም የሚጋራ ክህነት” ማለት ነው። ‘ሆሴ ግሬጎሪ የድሆች ሐኪም፣ የማኅበራዊ ፍትህ ሐዋርያ እና የተስፋ ልኡክ’ በሚለው የሕይወት ታሪኩ፣በገጽ 107 ላይ እንደተጻፈው። ነገሮችን በቸልተኝነት በመመልከት መከራን መቀበል ሳይሆን፥ ነገር ግን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚሉት፥ ሁሉን ነገር በመልካም መንፈስ በማከናወን እግዚአብሔርን ማገልገል ምንኛ አስፈላጊ ነው! 'ሥራችሁንም ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉት እንዲሁ በትጋት ፈጽሙት’ (ቆላ. 3፡23)።

እስቲ እራሳችንን እንጠይቅ፥ ሆሴ ግሬጎሪ ይህን ሁሉ ምኞት፣ ይህን ሁሉ ቅንዓት ያገኘው ከወዴት ነው? ከእርግጠኝነቱ እና ከጥንካሬው ነው ያገኘው። ‘በዓለም ላይ ጥሩ እና መጥፎ ሰዎች ያሉ ከሆነ፥ መጥፎዎቹ መጥፎ ለመሆን የበቁት በመጥፎነታቸው ሲሆን፥ ነገር ግን ጥሩ ሰዎች ጥሩ ለመሆን የበቁት በእግዚአብሔር ዕርዳታ ብቻ ነው’ በማለት፥ እርግጠኝነት እና ጥንካሬ የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን በጽሑፉ ገልጿል። ብጹዕ ሆሴ ግሬጎሪ ከሁሉ አስቀድሞ ጸጋ እንደሚያስፈልገው እና እግዚአብሔርም አብዝቶ እንዲሰጠው ይለምን ነበር። ስለዚህ በየመንገዱ የሚለምኑትን፥ በየቀኑ ከኢየሱስ ክርስቶስ በነፃ በሚያገኘው ፍቅር መርዳት እና መንከባከብ ልማዱ ነበር። ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በመቅረብ ጥንካሬንም ያገኘው ከዚህ መንገድ ነበር። ሆሴ ግሬጎሪ የጸሎት ሰው ነበር። የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን በመሳተፍ በየዕለቱ የመቁጠሪያ ጸሎት ያቀርብ ነበር። የኢየሱስ ክርስቶስን መስዋዕትነት በሕይወቱ ካጋጠሙት ነገሮች ጋር በማጣመር፥ የሚረዳቸውን ድውያንንና ድሆችን፣ ተማሪዎቹን እና የምርምር ሥራውን ልቡ ውስጥ ከሚገኙት ችግሮች ጋር በማድረግ ወደ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ያቀርብ ነበር።

ሆሴ ግሬጎሪ፥ በመሠዊያው ላይ ራሱን ለሰው ልጆች በሙሉ ካቀረበው ከኢየሱስ ጋር በመገናኘት፥ ሕይወቱን ለሰላም እንዲሰጥ የተጠራ መሆኑ ተሰማው። በእርግጥም ልቡ ውስጥ ያለውን ሰላም ከቅዱስ ቁርባን የተቀበለው መሆኑን ከመመስከር ወደኋላ አላለም። ስለዚህም እራሱን 'የሰላም ሐዋርያ' በማድረግ አውሮፓ ውስጥ የሰላም መልዕክተኛ መሆን ይፈልግ ነበር። አውሮፓ እርሱ የተወለበት አህጉር አይደለም። ነገር ግን በወቅቱ አንደኛው የዓለም ጦርነት በአውሮፓ ውስጥ እየተቀጣጠለ ነበር። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሰኔ 29/1919 ሊጠይቀው የመጣ  ጓደኛውን በማግኘቱ በጣም ተደሰተ። ሆሴ ግሬጎሪ የአውሮፓ ጦርነት እንዲያበቃ ስምምነት ላይ መደረሱን ሰማ። መሥዋዕቱ ተቀባይነትን አግኝቶ በምድር ላይ የፈጸማቸው ሥራዎች እንደተከናወኑ ተገነዘበ። የዚያን ዕለት ጠዋት እንደተለመደው በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ነበር። ቀጥሎም ለታመሙት ሰዎች መድኃኒት ሊያደርስ ወጣ። ነገር ግን መንገድ ሲያቋርጥ መኪና ገጭቶት ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ሕክምና ላይ እያለ የእመቤታችንን ስም እየጠራ አረፈ። ምድራዊ ጉዞው፥ መንገድ ላይ በሚያበረክተው የምሕረት ሥራ እና መልካም ሥራውን ይፈጽምበት በነበረው ሆስፒታል ውስጥ አከተመ።

ወንድሞቼ፣ እህቶቼ፣ ይህን ምስክርነት መሠረት በማድረግ ራሳችንን እንጠይቅ። አጠገቤ በሚገኙ ድሆች መካከል የሚገኘውን ኢየሱስ ክርስቶስ አገኘዋለሁ? በዓለም ላይ እጅግ የሚሰቃዩ ሰዎችን አይቼ የምሰጠው ምላሽ ምንድነው? የምችለውን ሁሉ አደርግላቸዋለሁ ወይንስ ተመልካች ብቻ ነኝ? ብፁዕ ሆሴ ግሬጎሪ በዘመናችን ውስጥ ከሚታዩ ታላላቅ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር እንድንገናኝ ያበረታታናል። ብዙ ሰዎች ስለ ችግር ያወራሉ፣ ብዙዎች ያማርራሉ፣ ሁሉ ነገር እየተበላሸ መሆኑን በመናገር ወቀሳቸውን ያቀርባሉ። ነገር ግን ክርስቲያን የተጠራው ለዚህ አይደለም። ይልቁንም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ወንዱም ሴቱም እጆቹን እንዲያጨቀይ ተጠርቷል። ከሁሉ አስቀድሞ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚናገረን መጸለይ ያስፈልጋል። 'እንግዲህ ከሁሉ በፊት እንዲደረግ የምመክረው ነገር ቢኖር ልመና እና ጸሎት፥ ምልጃ እና ምስጋና ስለ ሰዎች ሁሉ እንዲደረግ እመክራለሁ፤ እንዲሁም እግዚአብሔርን በመምሰል እና በተገባ አካሄድ ሁሉ፥ ጸጥታ የሰፈነበት እና ሰላማዊ የሆነ ሕይወት እንዲኖረን ስለ ነገሥታት እና በከፍተኛ ሥልጣን ላይ ስላሉ ሁሉ ጸሎት እናቅርብ። ይህም በአዳኛችን በእግዚአብሔር ፊት መልካም እና ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው። እርሱም ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ እና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲመጡ ፈቃዱ የሆነ አምላክ ነው’ (1ጢሞ. 2፡1-4)።

ሥራ ፈት ሆነን በፍሬ አልባ ንግግር ሳንያዝ፥ ነገር ግን መልካምን በማራመድ፥ ሰላምን እና ፍትህን በእውነት ላይ መገንባት ይኖርብናል። ይህም ከሐዋርያዊ ቅንዓት መካከል አንዱ እና የቅዱስ ወንጌል ምስክርነት ነው። ክርስቲያናዊ ብጽዕናም ነው። ‘ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና’ (ማቴ 5፡9)።”

 

13 September 2023, 16:35