ፈልግ

ሊቢያ ውስጥ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ያስከተለው ጥፋት ሊቢያ ውስጥ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ያስከተለው ጥፋት  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በጎርፍ አደጋ የተጠቃች ሊቢያ አጋርነታችንን እንደምትፈልግ አስታወቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሊቢያ ውስጥ የጣለው ኃይለኛ ዝናብ ባስከተለው ጉርፍ ምክንያት በሺህዎች የሚቆጥሩ ሰዎች ለሞተበት እና ንብረት ለወደመበት የሊቢያ ሕዝብ ዕርዳታ እንዲደረግለት ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአደጋው ክፉኛ ለተጠቃች ሊቢያ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕርዳታን እንዲያደርግ በድጋሚ ተማጽነው፥ መከራ ውስጥ የሚገኝ የሊቢያ ሕዝብ ቀጣይነት ያለው አጋርነታችንን እንደሚፈልግ ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ዛሬ ረብዕ መስከረም 2/2016 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ማጠቃለያ ላይ፥ በአገሪቱ የጣለው ኃይለኛ ዝናብ ባስከተለው ጉርፍ ምክንያት አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች በጸሎታቸው እንድሚያስታውሷቸው ገለጸው፥ በበርካታ ሰዎች ላይ ከፍተኛ የሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

ቅዱስነታቸው በአደባባዩ ለተገኙት ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት፥ ሕይወታቸውን ላጡት እና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም የተፈናቀሉ ወገኖችን በማስታወስ በሚያቀርቡት ጸሎት ሁሉም ምዕመናን እንዲተባበሯቸው አደራ ብለዋል። "ከእነዚህ ወንድሞች እና እህቶች ጋር ያለን አጋርነት ሊጎድልባቸው አይገባም" በማለት አጥብቀው ተናግረዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሕይወታቸው አጥተዋል

ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው፥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ገልጾ፥ አደጋው ከተከሰተ ዛሬ ረቡዕ ሦስተኛ ቀኑን እንዳስቆጥረ እና ከ5,300 በላይ ሰዎች መሞታቸው በማረጋገጥ፥ በቀጣዮቹ ቀናት ውስጥ የሟቾች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ሊያሻቅብ እንደሚችል አስታውቋል።

ኃይለኛ አውሎ ንፋስ በአካባቢው የሚገኙ ግድቦችን በማፈንዳቱ ምክንያት የተከሰተው የጎርፍ አደጋው የሜዲትራኒያን ከተማ የሆነችውን ዴርናን በሩብ ወይም ከዚያ በላይ እንዳወደማት እና ሕንፃዎችን ከነዋሪዎቹ ጋር መውሰዱ ታውቋል። በዚህ አደጋ ወደ 10,000 የሚጠጉ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ የተገመተ ሲሆን፥ በርካቶች ወደ ባሕር ተወስደዋል ተብሎ ይታመናል።

ቀጣይነት ያለው አጋርነት እና ጸሎት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ማክሰኞ መሰከረም 1/2016 ዓ. ም. በቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ በሆኑት በብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ተፈርሞ በሊቢያ የሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ በሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሳቪዮ ሆ ታይ ፋይ በኩል ለሊቢያ ሕዝብ የሐዘን መግለጫ የቴሌግራም መልዕክት ልከዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአደጋው ከፍተኛ የሕይወት እና የንብረት ጥፋት በመድረሱ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው፥ በአደጋው የተጎዱትን፣ የሞቱትን እና ሐዘን ላይ የሚገኙትን በሙሉ በማስታወስ ጸሎት ማድረጋቸውን አረጋግጠዋል።

ቅዱስ አባታችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፥ በአደጋው ለተጎዱት ወገኖች፣ ሕይወታቸውን ላጡት እና ዘመዶቻቸው እንዲሁም በነፍስ አድን ዕርዳታ አቅርቦት ሥራ ላይ ለተሰማሩት የድንገተኛ አደጋ መከላከያ ሠራተኞች ያላቸውን ልባዊ መንፈሳዊ ቅርበት ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በአደጋው ለተጎዱት ሁሉ መለኮታዊ መጽናናትን፣ ጥንካሬን እና ጽናትን በጸሎታቸው ጠይቀዋል።

13 September 2023, 16:57