ፈልግ

በሞሮኮ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሞሮኮ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ   (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመሬት መንቀጥቀጥ የተጎዳውን የሞሮኮ ሕዝብ በጸሎት አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሞሮኮ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ሕይወታቸውን ያጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በጸሎት አስታውሰው ለሕዝቡም ያላቸውን ቅርበት ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአደጋው ማግሥት የተሰማቸውን ሐዘን በቴሌግራም መልዕክት የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በማዕከላዊ ሞሮኮ በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ ሕይወታቸውን ያጡትና ጉዳት የደረሰባቸው በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።

ሞሮኮ ውስጥ ከማራካሽ ከተማ በስተደቡብ ምዕራብ በሚገኝ አካባቢ፥ ዓርብ ጳጉሜ 3/2015 ዓ. ም. ሌሊት የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር 6.8 ማግኒቲውድ መመዝገቡ ሲነገር፥ በተራራማው አካባቢ ከፍተኛ ጉዳት እና ውድመት ማድረሱ ተነግሯል።

የቅዱስነታቸው ስጋት እና የጸሎት ድጋፍ 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ ጳጉሜ 5/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመልዓከ እግዚአብሔር ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ "ውድ ለሆነው የሞሮኮ ሕዝብ" ባሉት መልዕክታቸው ለአገሪቱ ሕዝቦች ያላቸውን ቅርበት ገልጸዋል።

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን፣ የሞቱትን በርካታ ሰዎች እና ቤተሰቦቻቸውን በጸሎታቸው አስታውሰው፥

ለነፍስ አድን ሠራተኞች እና የሰዎችን ስቃይ ለማስታገስ ጥረት በማድረግ ላይ ለሚገኙት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በዚህ አሳዛኝ ወቅት የሚደረግ የሁሉ ሰው ተጨባጭ ዕርዳታ ለተጎዱት ድጋፍ እንዲሆናቸው በማለት፥ ሁሉም ሰው ጉዳት ከደረሰበት የሞሮኮ ሕዝብ ጎን እንዲሆን አደራ ብለዋል።

የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከከባድ የመሬት መንቀጥቀጡ በኋላ የነፍስ አድን ሠራተኞች ከፍርስራሹ ሥር የቀሩ ሰዎችን በመፈለግ ላይ ሲሆኑ፥ እስከ እሑድ ከሰዓት በኋላ ድረስ ቢያንስ 2,012 ሰዎች መሞታቸው እና 2,059 ሰዎች መቁሰላቸው ተዘግቧል።

የሞሮኮ ጦር ሠራዊት አደጋው ወደተከሰተበት ሥፍራ የሚወስዱ ዋና ዋና መንገዶች በማጽዳት አስፈላጊ ዕርዳታ ሰዎችን እንዲደርስ ማድረጉ ታውቋል። ወደ አትላስ ተራሮች የሚወስደው መንገድ በመሬት መንሸራተት መዘጋቱ ሲነገር፥ ቀይ መስቀል ማኅበር ከድንገተኛ የአደጋ መከላከያ የድጋፍ ገንዘብ 1.1 ሚሊዮን ዶላር ለመመደብ ቃል ገብቷል።

በማራካች አቅራቢያ ያሉ ጥንታዊ መንደሮች ወደ ፍርስራሽነት መቀየራቸውን ያሳየው የድሮን የቪዲዮ ምስሉ፥ ከአደጋው በኋላ ያሉት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ቀናት፥ በሕይወት የተረፉን ሰዎች ለማግኘት ወሳኝ ጊዜ መሆኑን የዕርዳታ ድርጅቶች ገልጸው፥ ብዙ ሰዎች በድጋሚ ሊከሰት የሚችለውን አደጋ በመፍራት ከቤት ውጭ በየጎዳናዎች እና ሜዳዎች ላይ መሆንን መምረጣቸው ታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በማራካሽ እና አካባቢዋ ከ300,000 በላይ ሰዎች በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ መጎዳታቸውን አስታውቋል።

 

11 September 2023, 13:41