ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ሰዎችን በወንድምነት መገሠጽ ታላቅ የፍቅር መግለጫ መንገድ መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እሑድ ጳጉሜ 5/2015 ዓ. ም. የእኩለ ቀኑን የመልዓከ እግዚአብሔር ጸሎት በኅብረት ለማቅረብ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ስብከታቸውን አቅርበዋል። ከጣሊያን የተለያዩ ሀገረ ስብከቶች እና ከሌሎች አገራትም ለመጡት ምዕመናን በዕለቱ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ባቀረቡት ስብከት፥ ሰዎችን በወንድምነት መገሠጽ ታላቅ የፍቅር መግለጫ መንገድ መሆኑን ገለጹ። ክቡራት ክቡራን ተከታታዮቻችን፥ የቅዱስነታቸው ስብከት ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚተለው ቀርቧል፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! በዛሬው ዕለት ከማቴ. 18፡ 15-20 ተወስዶ የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል፥ ወንድምን ስለመገሠጽ ይነግረናል። ይህም ከፍቅር መግለጫ መንገዶች መካከል አንዱ እና ተነሳሽነትን የሚጠይቅ ነው። ምክንያቱም ሌሎችን መገሠጽ ወይም ማረም ቀላል አይደለምና። እምነትን የሚጋራ አንድ ወንድም ቢበድለን ያለ ነቀፋ መርዳት፣ ማረም እና መገሠጽ ያስፈልጋል።

ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ስህተትን በሚፈጽሙ ሰዎች ዙሪያ የሚከሰት የመጀመሪያው ነገር ሐሜት ነው። ጉዳዩ ከሚመለከተው ሰው ሌላ ስህተቱን ሁሉም ሰው በዝርዝር የሚያውቅበት ሁኔታ ይከታል። ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ይህ ትክክል አይደለም። እግዚአብሔርም በዚህ አይደሰትበትም። ሃሜት በሰዎች እና በኅብረተሰብ ሕይወት ውስጥ መቅሰፍት እንደሆነ ደጋግሜ መናገር አይሰለቸኝም። ምክንያቱም ሃሜት መለያየትን በማስከተል ወደ መከራ እና ወደ ውርደት ይመራል። ለመታረምም ሆነ ለማደግ ፈጽሞ አያግዝም። ታላቅ መንፈሳዊ ሊቅ ቅዱስ ቤርናርዶስ፥ ዋጋ የሌለው ጉጉት እና ከአንገት በላይ የሆኑ ቃላት ሰውን ወደ ከፍታ የሚያወጡ ሳይሆን ወደ ጥፋት እና ወደ ጉድጓድ የሚያወርድ መሰላል የመጀመሪያ ደረጃዎች ናቸው። (አሥራ ሁለቱ የትሕትና እና የትዕቢት ደረጃዎች)

ይልቁንም ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ መንገድ እንድንመላለስ አስተምሮናል። ዛሬም ቢሆን እንዲህ ይለናል፥ “ወንድምህ ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ገሥጸው” (ማቴ. 18:15)። ፊት ለፊት ተነጋገሩ፤ ያጠፋ ሰው ከስሕተቱ እንዲታረም በትክክለኛው መንገድ ንገሩት። ይህን የምታደርጉት ለእርሱ ጥቅምና ነውርን አሸንፎ እውነተኛ ድፍረትን እንዲያገኝ ነው። ስሙን በማጥፋት ሳይሆን በየዋህነትና በጨዋነት መንገድ ይሁን።

ነገር ግን ይህ በቂ ካልሆነስ?፥ ካልገባውስ? የሌሎችን እገዛ መፈለግ አለብን። እገዛን የምንፈልገው  ከሃሜተኞች መካከል እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብን። ኢየሱስ፥ “ባይሰማህ ግን አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር ቃል ነገር ሁሉ ይጸናልና” (ማቴ. 18:16) በማለት ተናግሯል። ይህም የተሳሳተ ወንድማቸውንን ለመርዳት ያለንን ልባዊ ፍላጎት ይገጻል።

አሁንም ስህተቱን ካልተረዳስ? ማኅበረሰቡን ማሳተፍ እንደሚገባ ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል። ነገር ግን ይህ ማለት አንድን ሰው በአደባባይ ማዋረድ ማለት ሳይሆን፥ ከስህተቱ እንዲታረም የሁሉንም ሰው ጥረት ማስተባበር ማለት ነው።

ጣትን ወደ ሌሎች መቀሰሩ ጥሩ አይደለም። እንዲያውም ይህ ብዙውን ጊዜ በዳዩ ስህተቱን እንዳይገነዘብ እንቅፋት ይሆንበታል። ከዚህ ይልቅ ማኅበረሰቡ የተሠራውን ስህተት ሲያወግዝ ወደተሳሳተው ግለሰብ በጸሎት እና በፍቅር በመቅረብ፣ ሁልጊዜም ይቅርታን ለማድረግ፣ ለመረዳት እና መልካም ግንኙነትን መልሶ ለመጀመር ዝግጁነት መኖሩ እንዲሰማው ማድረግ ያስፈልጋል።

ስለዚህ፥ “ለሚበድለኝ ሰው ምን ማድረግ አለብኝ?” ብለን እራሳችንን እንጠይቅ። ቂም እይዝበታለሁ? መልሼ እከፍለዋለሁ? "ምን እንዳደረኝ ታውቃለህ?" እያልን ስላደረሰብኝ በደል ከጀርባ ለሌሎች አወራለሁ? ወይስ ከበደለኝ ሰው ጋር ፊት ለፊት በመገናኘት ለመነጋገር እሞክራለሁ? ለእርሱ ወይም ለእርሷ እጸልያለሁ? መልካምን ማድረግ እንድችል የሌሎችን ዕርዳታ እጠይቃለሁ? የተሳሳቱት ከስሕተታቸው ተመልሰው አዲስ ሕይወት እንዲጀምሩ ማኅበረሰቦቻችንስ እንክብካቤን ያደርጉላቸዋል? ጣቶቻቸውን ይቀስሩብቻዋል ወይስ እጆቻቸውን ዘርግተው ይቀበሏቸዋል? ምን ታደርጋላችሁ?

ሰዎች ልጇን እንደሚኮንኑት ብትሰማም ፍቅሯን ያላቋረጠች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፥ ሁል ጊዜ መልካም መንገድን እንድንሻ ዕርዳታዋን ትስጠን።”

 

11 September 2023, 11:54