ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ሲያቀርቡ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ሲያቀርቡ   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የእግዚአብሔር ፍቅር ወሰን እንደሌለው አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት እሑድ መስከረም 13/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በዕለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው ለምዕመናን ባቀረቡት ስብከት፥ የእግዚአብሔር ፍቅር ወሰን የሌለው መሆኑን አስገንዝበዋል። ክቡራት ክቡራን፥ ቅዱስነታቸው በትናንትናው ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን በዕለቱ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል በማስተንተን ያቀረቡትን ስብከት ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! በዛሬ ዕለት የተነበበው ቅዱስ ወንጌል አስገራሚ ምሳሌ ይነግረናል። በማቴ 20:1-16 ላይ የተጻፈው፥ የወይን አትክልት ሠራተኞችን በሚገልጽ ምሳሌ ላይ፥ የወይን አትክልት ጌታ ከንጋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ በወይን እርሻው የሚሠሩ አንዳንድ ሠራተኞችን ለመጥራት ይወጣል። ነገር ግን ሥራቸውን ጨርሰው የጉልበት ዋጋ ሊቀበሉ ለመጡት ሠራተኞች አንድ ሰዓት ብቻ ለሠሩትም ሆነ ቀኑን ሙሉ ሲሠሩ ለዋሉትም እኩል ከፈላቸው። ይህ ፍትሃዊነት የሌለው ይመስላል። ነገር ግን ምሳሌው መታየት ያለበት በደመወዝ መብለጥ ወይም ማነስ ሳይሆን የእግዚአብሔርን መመዘኛ ሊያሳየን አስቧል። እግዚአብሔር የሚመለከተው ብቃታችንን ሳይሆን እንደ ልጆቹ አድርጎን መውደዱን ነው።

ከዚህ የወንጌል ታሪክ ውስጥ የወጡ ሁለት መለኮታዊ ሥራዎችን በጥልቀት እንመልከታቸው። የመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር እኛን በማንኛውም ሰዓት እንደሚጠራን፥ ሁለተኛ፥ አንዱን ከሌላው ሳያበላልጥ ለሁሉም ሰው እኩል የሚከፍል መሆኑን እንመለከታለን።

በመጀመሪያ ደረጃ፥ እግዚአብሔር እኛን በሁሉም ሰዓት ይጠራናል። በምሳሌው ላይ እንደተገለጸው፥ የወይን አትክልት እርሻ ባለቤት ሠራተኞችን ሊቀጥር ማልዶ ወጣ” ይላል። (የማቴ. 20:1) በኋላ ግን በቀን በተለያዩ ጊዜያት ውስጥ ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ ሥራ ያላገኙትን መቅጠር አላቋረጥጠም። ምሳሌው ሠራተኞችን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ሰዎችን ሳያቋርጥ ለመጥራት እንደሚወጣ ያስረዳል። እንግዲህ የእግዚአብሔር ፍቅር እንደዚህ ነው። እግዚአብሔር የእኛን ጥረት ብቻ አይጠብቅም። ወይም ብቃታችን ምን ያህል እንደሆነ መገምገም ወይም መመራመር አይፈልግም። ለእርሱ ምላሽ ልንሰጥ ብንዘገይም እንኳ ተስፋን አይቆርጥም። በተቃራኒው፣ እርሱ እራሱ ተነሳሽነትን በመውሰድ ፍቅሩን ሊያሳየን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ እኛ መጥቷል። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ታላቁ በስብከቱ እንደገለጸው፥ እግዚአብሔር በሕይወታችን የተለያዩ ደረጃዎች እና ወቅቶች እስከ እርጅናችንም ድረስ በየቀኑ እና በየሰዓታቱ ይፈልገናል። (የወንጌል ስብከት ቁ.19)። እርሱ ምንም ቢሆን አይዘገይም፤ ሁል ጊዜ ይፈልገናል፤ ይጠብቀናልም። ይህን መዘንጋት የለብንም።

በትክክልም ደግሞ እግዚአብሔር ለልጆቹ በሙሉ የሚራራ ትልቅ ልብ አለው። በወይን አትክልት ሠራተኞች ምሳሌ ላይ እግዚአብሔር የፈጸመው ሁለተኛው ድርጊት፥ አንዱን ከሌላው ሳያበላልጥ፥ ከፍቅሩ የተነሳ ለሁሉም ሰው እኩል መክፈሉ ነው። የምሳሌው ከፍተኛ ትርጉም የሚገኘው እዚህ ላይ ነው፡ ባለቀ ሰዓት ላይ ለሥራ የተሰማሩት ሠራተኞች ከማለዳ ጀምሮ ሲደክሙ ከዋሉት ጋር እኩል ይከፈላቸዋል። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ፍትህ ከሁሉም የላቀ ነውና። የሰው ልጅ ፍትህ ግን ለእያንዳንዱ የሚገባው ያህል የሰጠው ይላል። የእግዚአብሔር ፍትህ ግን ፍቅርን እኛ በፈጸምነው መልካም ሥራ ወይም ውድቀት መጠን የሚለካ አይደለም። እግዚአብሔር ይወደናል፣ የሚወደንም ልጆቹ በመሆናችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በነጻ ፍቅሩ ነው።

ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ አንዳንድ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ሰጥቶ የመቀበል ዓይነት ግንኙነት መመሥረትን እንፈልጋለን። እግዚአብሔር ሁሉን ሰው በተመሳሳይ ፍቅር የሚወድ መሆኑን ሳናስተውል፥ ለሰዎች በሙሉ እጆቻችንን ዘወትር ከመዘርጋት ይልቅ ቤታችን ውስጥ ሆነን በሌሎች ላይ እንደምንፈርድ ያህል ይሰማናል። የኅብረተሰባችን ፅንሰ-ሀሳብ በሆነው የእርስ በርስ ግንኙነትም ቢሆን፥ የምንተገብረው ፍትህ አንዳንድ ጊዜ በሂሳብ ቀመር የተሰላ እና በተቀበልነው መጠን በመስጠት ላይ እንወሰናለን። ከምንጠየቀው ርቀት በላይ መጓዝ እንዳለብን ሳናውቅ፥ በነጻ የተደረገልንን መልካም ነገር እና በሰፊ ልብ የቀረበልንን ፍቅር ሳንረዳ እንቀራለን። ወንድሞቼ እና እህቶቼ እስቲ እራሳችንን እንጠይቅ! ክርስቲያን የሆንኩ እኔ ወደ ሌሎች ዘንድ መሄድ እንዳለብኝ አውቃለሁ? ለሁሉም ሰው ለጋስ ነኝ? ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኔ እንዳደረገልኝ ያንን ተጨማሪ መረዳት እና ይቅርታን ለሌሎች መስጠት እንደሚገባኝ አውቃለሁ?

በመጠን የማይለካውን የእግዚአብሔር ፍቅር ለሌሎች ማሳየት እንድንችል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን።”

 

25 September 2023, 16:54