ፈልግ

በፈረንሳይ የሚገኝ የማርሴይ ከተማ በፈረንሳይ የሚገኝ የማርሴይ ከተማ  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በማርሴይ ለሚያደርጉት ጉብኝት የምዕመናንን የጸሎት ዕርዳታ ጠየቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በትናንትናው ዕለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ካቀረቡት ስብከት በኋላ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናኑ ጋር በኅብረት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አድርሰዋል። ቀጥለው ባደረጉት ንግግርም በፈረንሳይ ማርሴይ ከተማ ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የምዕመናንን የጸሎት ዕርዳታ ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እሑድ መስከረም 6/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ያቀረቡ ሲሆን፥ ከጸሎት ሥነ ሥርዓቱ ቀጥለው ለምዕመናኑ ባሰሙት ንግግር፥ በጦርነት አደጋ ለሚሰቃዩ የዩክሬይን ሕዝቦች ሰላም እንዲወርድ ተማጽነዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም በተጨማሪ የሜዲትራኒያን አካባቢ አገራት የፈረንሳይ ከተማ በሆነች ማርሴይ ውስጥ በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ ለመገኝት ወደ ሥፍራው ለሚያደርጉት የሁለት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት የምዕመናንን የጸሎት ዕርዳታ ጠይቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የፊታችን ዓርብ መስከረም 11/2016 ዓ. ም. ፈረንሳይ ውስጥ ማርሴይ ከተማ የሚያደርጉትን የሁለት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስታወስ ባደረጉት ንግግር፥ ምዕመናኑ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በጸሎት እንዲያግዙ ጠይቀዋል። በተጨማሪም በጦርነት የተጎዳውን የዩክሬይን ሕዝብ ጭምሮ በጦርነት አደጋ ውስጥ ለወደቁ የሌሎች አገራት ሕዝቦችም ያላቸውን ቅርበት ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን የገለጹት፥ ትናንት እሁድ መስከረም 6/2016 ዓ. ም. የእኩለ ቀኑን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኅብረት ለማቅረብ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን ባደረጉት ንግግር ነው።

ቅዱስነታቸው በማርሴይ የሚያደርጉት ጉብኝት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዓርብ መስከረም 11 እስከ መስከረም 12/2016 ዓ. ም. ድረስ በፈረንሳይ ማርሴይ ከተማ የሁለት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያደርጉት ከመስከረም 6 እስከ መስከረም 13/2016 ዓ. ም. ድረስ የሚካሄደውን የሜዲቴራኒያን አገራት ስብሰባ ለመዝጋት እንደሆነ ታውቋል። የደቡብ ፈረንሳይ ከተማ በሆነች ማርሴይ ውስጥ በሚካሄደው ስብሰባ ላይ የሜዲቴራኒያ አካባቢ አገራትን የሚወክሉ ብጹዓን ጳጳሳት እና ወጣቶች እንደሚገኙ ተገልጿል። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሜዲቴራኒያን አካባቢ አገራት ተወካዮች ጋር ለመገናኘት በማርሴይ ከተማ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወንድማማችነትን ለማሳደግ መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ከመስከረም 11-12/2016 ዓ. ም. ድረስ በማርሴይ ከተማ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፥ ባለፈው ወር ላይ በሞንጎሊያ ካደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ጋር 44ኛው ዓለም አቀፍ ጉብኝት እንደሚሆን ታውቋል።

ሰላምን፣ ውህደትን እና ትብብርን ማሳደግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን ባደረጉት ንግግር፥ ስብሰባው አስደሳች ተነሳሽነት ያለው እንደሆነ በመግለጽ፥ የሜዲቴራኒያን አካባቢ አገሮች ከተሞች የሚገኙ የቤተ ክርስቲያናት እና ሕዝባዊ መሪዎችን አንድ ላይ በመሰብሰብ የሰላም፣ የትብብር እና የውህደት ጎዳናዎችን በማመቻቸት በአካባቢው ለሚታይ የስደት ቀውስ ልዩ ትኩረት የሚሰጥ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው በማከልም ስብሰባው ቀላል ባልሆኑ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚያደርግ ገልጸው፥  ይህን ቀላል ያልሆነ ፈተና በአንድነት ሊጋፈጡት እንደሚገባ አጽንኦት በመስጠት ተናግረዋል። በተለይ የስደትን ቀውስ በተመለከተ የሚካሄዱ አስቸጋሪ ውይይቶች ለወደፊት ጉዞአችን ሁሉ አስፈላጊ እንደሆኑ ገልጸው፥ “ውጤታማ የሚሆነው በወንድማማችነት ላይ ከተገነባ እና በተለይም በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ የአቅመ ደካሞች ሰብዓዊ ክብር በማስቀድም ብቻ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

መከራ ውስጥ የምትገኝ ዩክሬይን እና ጦርነት የሚካሄዱባቸው አገሮች

በጦርነት እየወደመች ያለች ዩክሬይን እና በጦርነት የቆሰሉ ሌሎች አገሮችንም ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእነዚህ ሁሉ አገራት ሰላም እንዲሰፍን ጠይቀው፥ “በጦርነት አደጋ ለሚሰቃይ የዩክሬይን ሕዝብ ሰላም እንዲወርድ የምናቀርበውን ጸሎት ሳናቋርጥ እንቀጥላለን” ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሩሲያ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት በጎረቤት አገር ዩክሬይን ያካሄደችው ወረራ እንዲያበቃ በማለት የተለያዩ ጥሪዎችን ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው በጦርነት ለተጎዱት የዩክሬይን ግዛቶች ሰብዓዊ ዕርዳታችን በተደጋጋሚ መላካቸውም የሚታወስ ሲሆን፥ የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት እና የቦሎኛ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒን ጨምሮ፣ ሌሎች የሰላም መልዕክተኞች ወደ አገራት በመላክ የሰላም ጥረቶችን ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በነሐሴ ወር ላይ ከዩክሬይን ግሪክ-ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው ሲታወስ፥ መላው ካቶሊካዊ ምዕመናን ዩክሬይን ውስጥ እርቅ እና ሰላም እንዲወርድ ጥቅምት ወር በሙሉ በጸሎት እንዲተጉ መጋበዛቸው ይታወሳል።   

 

 

 

18 September 2023, 16:46