ፈልግ

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሰላም ልኡክ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፤ የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሰላም ልኡክ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፤ 

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ፥ ፍትሐዊ የሰላም ተልዕኮን ይዘው ወደ ቤጂንግ መጓዛቸው ተገለጸ

በሩስያ እና ዩክሬን መካከል የሚካሄደው ጦርነት አብቅቶ በሁለቱ አገራት መካከል ሰላም እንዲሰፍን የሚያግዝ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰላም ጥረት በኪየቭ፣ በሞስኮ እና በዋሽንግተን አድርገው የነበሩት የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፥ በዩክሬን ውስጥ ያለውን ውጥረት ለማርገብ የሚግዝ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሃሳብ ይዘው ወደ ቤጂንግ ተጉዘዋል። ቅድስት መንበርም የብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ የቤጂንግ ጉዙ፥ ሰብዓዊ ተነሳሽነቶችን እና ወደ ፍትሃዊ ሰላም የሚያመሩ መንገዶችን ለመደገፍ ተጨማሪ እርምጃ እንደሚሆን ገልጻ፥ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ በበኩላቸው፥ "የብዙ ሰዎች ጸሎት አስቸጋሪ የሆነውን የሰላም ጥረት በድል እንድወጣው ያግዘኛል" ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከወራት ቆይታ በኋላ፥ በሮም እንዳደረጉት ሁሉ የሰላም ተልዕኮን ለመፈጸም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰላም መልዕክተኛ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ማሪያ ዙፒ፥ በዩክሬን ውስጥ ያለውን ውጥረትን ለማርገብ የሚያግዝ የሰላም ተልዕኮ በቻይና ውስጥም ቀጥለዋል። የብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ የቤጂንግ ቆይታ ከመስከረም 2 – 4/2016 ዓ. ም. ድረስ እንደሚሆን ቅድስት መንበር ያስታወቀች ሲሆን፥ ካርዲናል ማቴዮ ካለፈው ሰኔ ወር እስከ ሐምሌ ወር ባሉት ጊዜያት መካከል ወደ ኪየቭ፣ ሞስኮ እና ዋሽንግተን በማጓዝ የሰላም ጥረቶችን ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል።

በጣሊያን የቦሎኛ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ ወደ ቤጂንግ የተጓዙት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክተኛ ሆነው እንደሆነ የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል። መግለጫው አክሎም፥ ብጹዕነታቸው በቤጂንግ የሚያደርጉት ጉብኝት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰብዓዊ እምጃዎች እና ወደ ፍትሃዊ ሰላም የሚመሩ መንገዶችን ለመደገፍ ለሚደረገው ተልዕኮ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚሆን አስታውቋል።

በቤርሊን የተደረገው የሰላም ጸሎት እና ውይይት

ብዙ ሰዎች በግል የሚያቀርቡት ጸሎት፥ የአብያተ ክርስቲያናት እና የሃይማኖት ተቋማት ጸሎት፥ ለሰው ልጆች በሙሉ የተሰጠውን የሰላም ስጦታን ለመፈለግ ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነ የተናገሩት ብጹዕ ካርዲና ማቴዮ ዙፒ፥ የቤጂንግ ጉዟቸው ይፋ ከሆነ በኋላ በሰጡት አስተያየት፥ አዲሱ ጉዞአቸው አስቸጋሪ የሆነውን የሰላም ጥረት ለማሳካት ተስፋ የተጣለበት እንደሆነ አስረድተዋል። “የሰላም ጥረት” በሚል መሪ ሃሳብ በቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ አስተባባሪነት፥ ከጳጉሜ 6/2015 ዓ. ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት ቤርሊን ከተማ በተጋጀው ሥነ-ሥርዓት ላይ ዋና ዋና የዓለም ሃይማኖቶች መሪዎች ከ40 የፖለቲካ እና የባሕል ተወካዮች ጋር በመሆን የጋራ ጸሎት በማቅረብ ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል። በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከተገኙት እንግዶች መካከል ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ አንዱ ሲሆኑ፥ ከቀትር በኋላ በጣሊያን ኤምባሲ ተገኝተው ከጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ አንቶኒዮ ታጃኒ ጋር ረጅም የግል ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል።

ከውይይታቸው ቀጥለው ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ እንደገለጹት፥ "የብዙ ሰዎች ጸሎት አስቸጋሪ የሆነውን የሰላም ጥረት በድል እንድወጣው ያግዘኛል" ብለው፥ በጀርመን ዋና ከተማ ቤርሊን የተካሄደው ውይይት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአደራ በሰጧቸው የሰላም ተልዕኮ ላይ በዋናነትም ከአገራቱ የፖለቲካ እና የቤተ ክርስቲያን ተወካዮች ጋር ውይይት ማካሄዳቸውን ገልጸዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከየካቲት ወር 2022 ጀምሮ ዩክሬንን እየያሰቃያት ያለውን ጦርነት ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት በማስመልከት በሰጡት አስተያየት፥ የሰላም ጥረቱ በአንድ ወገን ጫንቃ ላይ የሚጣል ሳይሆን፥ በዩክሬናውያን የተመረጠው የሰላም ዋስትና እና ቁርጠኝነት የሁሉንም ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረው፥ በዚህ ሂደት ውስጥ የቻይና መንግሥት ሚና ምናልባት እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት መካከል አንዱ እንደሆነ አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው ከሞንጎሊያ በመመለስ ላይ እያሉ ያደረጉት ቃለ ምልልስ

ቻይና ሰላምን በማስከበር ተልዕኮ መርሃ ግብር ውስጥ መካተቷን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለፈው ነሐሴ ወር “ቪዳ ኑዌቫ” ከተባለ የስፔን መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አረጋግጠዋል። ቅዱስነታቸው በቃለ ምልልሳቸው ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን አስታውሰው፥ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ የሰላም ውይይቱ በመምራታ በርትተው እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። አክለውም፥ ካርዲናሉ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1992 በሞዛምቢክ ውስጥ ለተደረጉት ስምምነቶች ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።

“ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ ታላቅ የውይይት እና ዓለም አቀፋዊ ራዕይ ያላቸው ሰው ናቸው" ያሉት ቅዱስነታቸው ቀጥለውም፥ በአሁኑ ወቅት ከቻይና ጋር ያለው ግንኙነት በመልካም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2018 የተደረሰው የጳጳሳት ሹመት ስምምነት እስከ ዛሬ ለሁለት ጊዜ መታደሱን ተናግረዋል። "ከቻይና መንግሥት እና ከቫቲካን የተወጣጣው ኮሚሽን ለረጅም ጊዜ አብሮ ሲሠራ መቆየቱን ተናግረው፥ የጋራ ምክር ቤቱ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ በሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን የሚመራው መሆኑንም ገልጸዋል። እርስ በርስ ለመረዳዳት እና የቻይና ሕዝቦች ባህል እና እሴቶቻቸውን ቤተ ክርስቲያን እንደምትቀበል እና የቻይና ሕዝብ ቤተ ክርስቲያን በሌላ የውጭ ሃይል ላይ የተመሠረተች አድርጎ እንዳያስቧት፥ በብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን የሚመራው ኮሚሽን ይህንን የወዳጅነት መንገድ በጥሩ ሁኔታ እያከናወነ እንደሚገኝ፥ በቻይና በኩልም ጥሩ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረው፥ ለቻይና ሕዝብም ታላቅ አክብሮት እንዳላቸው አስረድተዋል።

 

14 September 2023, 17:11