ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሞንጎሊያ ያደረጉት ጉብኝት በሕዝቦች መካከል ስምምነትን የሚዘራ መሆኑ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሞንጎሊያ ከነሐሴ 25-29/2015 ዓ. ም. ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በሕዝቦች መካከል በስምምነት አብሮ መኖርን የሚያሳድግ መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ጆርጆ ማሬንጎ ገለጹ። ብጹዕ ካርዲናል ማሬንጎ፥ ቅዱስነታቸው በሞንጎሊያ ያደረጉትን የአራት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት ለቫቲካን ዜና አገልግሎት ባካፈሉት አተያየታቸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሞንጎሊያ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በአገሪቱ ሕዝቦች መካከል አዲስ የወዳጅነት ትስስር በመገንባት ረገድ ስኬታማ መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሞንጎሊያ መዲና ኡላንባታር የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ተጠሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ጆርጆ ማሬንጎ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የእስያ አኅጉር እምብርት በሆነች ሞንጎሊያ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በሕዝቡ መካከል ታላቅ የደስታ ስሜት መፍጠሩን ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው በሞንጎሊያ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ወደ ሮም ከመመለሳቸው ቀድም ብሎ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልል ያደረጉት ብጹዕ ካርዲናል ጆርጆ ማሬንጎ፣ “የቅዱስነታቸው ጉብኝት የሞንጎሊያ ሕዝብ በተለይም በቁጥር ትንሽ ከሆነው ካቶሊክ ማኅበረሰብ ጋር አዲስ የወዳጅነት ትስስር ለመፍጠር አስደናቂ አስተዋጽዖ አበርክቷል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሞንጎሊያ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት አጭር አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁት ብጹዕ ካርዲናል ማሬንጎ፥ “ባለፉት ቀናት ውስጥ ቅዱስነታቸው በሞንጎሊያ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ሁላችንም ታላቅ ጸጋን ያገኘንበት ነው” ብለው፥ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ከወንጌል የሚገኘውን ደስታ ከመላው የአገሪቱ ሕዝብ ጋር የተካፈልንበት፥ በወንጌል አስተምህሮአቸው እና በሐዋርያዊ አባትነታቸው በሞንጎሊያ ውስጥ ከሚገኝ በቁጥር ትንሽ ለሆነው ካቶሊክ ማኅበረሰብ እና ለመላው የሞንጎሊያ ሕዝብ ያላቸውን ቅርበት የተመለከትንበት ነበር” ብለዋል። 

ብጹዕ ካርዲናል ጆርጆ ማሬንጎ በማከልም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሞንጎሊያ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፥ የአገሪቱን ካቶሊካዊ ምዕመናን ጨምሮ መላው የሞንጎሊያ ሕዝብ እና የተቀሩት ሌሎች ሕዝቦችም ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር አዲስ ወዳጅነት እንዲፈጥሩ ትልቅ አስተዋፅዖ ያደረገ ነበር” ብለዋል።

የሕዝቡ ደስታ ከሰዓት ወደ ሰዓት እያደገ የሚሄድ እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ጆርጆ ማሬንጎ፥ “ቅዱስነታቸው በኡላንባታር ጎዳናዎች ሲዘዋወሩ ሕዝቡ በደስታ ተሞልቶ ሰላምታ ሲያቀርቡላቸው ማየታቸው፥ ባለፉት ቀናት ያደረጉትን ንግግር ጠቅሰው እንደተናገሩት ሁሉ፥ የሰላም፣ የደስታ እና የወዳጅነት መልዕክት እንዳመጡ እንድገነዘብ አድርጎኛል” ብለዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ጆርጆ ማሬንጎ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሞንጎሊያ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በአገሪቱ ሕዝቦች መካከል አዲስ የወዳጅነት ትስስር እና የመግባባት ስሜት ከመፍጠር ረገድ ስኬታማ እንደሆነ ተናግረው፥ በተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት መካከል መተባበርን እና ለመንፈሳዊ እሴቶቹ ከፍተኛ ግምት የሚሰጥ ማኅበረሰብ በመገንባት፥ ሃብትን ብቻ ለማካበት ለሚጣደፍ ማኅበረሰብ የሥነ ምግባር እና መንፈሳዊ እሴቶች አስፈላጊነትን ከመግለጽ አኳያ ስኬታማ እንደ ነበርም ተናግረዋል።

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሱክባታር አደባባይ ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጋር ሲጨባበጡ መመልከታቸው ስሜታዊ ነበር” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ጆርጆ ማሬንጎ፥ በቅድስት መንበር እና በሞንግሎሊያ መካከል ለዘመናት የዘለቀው ወዳጅነት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሞንጎሊያን እንዲጎበኙ በማድረግ ምስጋናን ከማቅረብ በተጨማሪ ደስታን እንደሰጣቸው ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።

 

06 September 2023, 15:23