ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ሕግ አውጪዎች ኅብረት ልዑካንን በቫቲካን ሲቀብለው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ሕግ አውጪዎች ኅብረት ልዑካንን በቫቲካን ሲቀብለው  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የምሁራን የፖለቲካ ሥልጣን ሥርዓት ሰብዓዊነትን እንዲያከብር አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዓለም አቀፉ የካቶሊክ ሕግ አውጪዎች ኅብረት የልዑካ ቡድንን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ለልኡካን ቡድኑ ባደረጉት ንግግር የምሁራን ባለ ሥልጣናት ሥርዓት አምባገነንነት የማኅበረሰቦችን ሰብዓዊ ክብር ማሳነስ እንደሌለበት አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቅዳሜ ነሐሴ 20/2015 ዓ. ም. ዓለም አቀፉ የካቶሊክ ሕግ አውጪዎች ኅብረት ልዑካን ቡድንን በቫቲካን ተቀብለው ባደረጉት ንግግር፥ ከምሁራን የፖለቲካ ሥልጣን ሥርዓት የሚመነጩ እና በተለይም በኅብረተሰቡ መካከል ድሃ እና ተጋላጭ በሆኑ ሕዝቦች ላይ የሚታዩ በርካታ ሰብዓዊነት የጎደላቸው አዝማሚያዎችን አውግዘዋል። ቅዱስነታቸው ለካቶሊክ የህግ አውጭዎች ቡድን ባደረጉት ንግግር፥ የምሁራን የፖለቲካ ሥልጣን ሥርዓት በሰው እና በሥነ-ምህዳር ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንዳለው ገልጸው፥ ሰዎችን እና ሥነ-ምኅዳርን በተመለከተ በዓለማችን ውስጥ ጥልቅ ጥያቄዎችን እንደሚያስነሳ ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ሕግ አውጪዎች ማኅበር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሮም አቅራቢያ በሚገኝ ፍራስካቲ ከተማ በተካሄደው አሥራ አራተኛው የዓለም አቀፍ የካቶሊክ ሕግ አውጪዎች ማኅበር ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የተገኙትን ተሳታፊዎች በቫቲካን ተቀብለው አነጋግረዋል። በሕዝባዊ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ አዳዲስ ትውልዶችን እና ክርስቲያን መሪዎችን ለማስተማር እና ለማበረታታት፥ የፖለቲካ አቋማቸው ምንም ይሁን ምን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮችን እንዲከተሉ ለማበረታታት እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዕድሎችን ለመስጠት በሚል ዓላማ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2010 ዓ. ም. ለትርፍ ያልተቋቋመ ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ሕግ አውጪዎች ማኅበሩ፥ ችግር ውስጥ በሚገኝ ዓለም ውስጥ የፖለቲካ መሪዎችን፣ ብሔረሰቦችን፣ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶችን እና አብያተ ክርስቲያናትን አገናኝቶ በመርዳት ላይ የሚገኝ ማኅበር ነው።

የምሁራን የፖለቲካ ሥርዓት አምባገነንነት ሰብዓዊ ክብርን የቀንሳል

የሥልጣን ትግል፣ የተለያዩ ሕዝባዊ ድርጅቶች እና የምሁራን የፖለቲካ ሥልጣን ለሰብዓዊ ክብር ለሚሰጡት ዝቅተኛ ግምት የቤተ ክስቲያን ምላሽ” በሚለው የዘንድሮው መሪ ሃሳብ ላይ ያስተነተኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የምሁራን የፖለቲካ ሥልጣን ሥርዓት የሰዎችን ስሜት በስውር በማጥቃት በተለይም ወጣቶች ነፃነታቸውን አላግባብ እንዲጠቀሙ የሚገፋፋ አንዱና ዋነኛው ሥርዓት እንደሆነ ተናግረዋል።

በግልጽ የምንመለከተው ይህ ሥርዓት ወንዶች እና ሴቶች በኢኮኖሚያዊ ቁሳቁሶች የጋራ መኖሪያ ምድራቸውን የተፈጥሮ ሃብቶችን በኃላፊነት ከመጠበቅ ይልቅ እንዲቆጣጠሩ ሲያበረታታ መታየቱን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም፥ እንዲህ ዓይነቱ ሥርዓት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በተግባር ሊዋቀር እንደሚችል ገልጸው፥ ገለልተኛ የሚመስሉ የዕለት ተዕለት ምርጫዎች መገንባት በሚፈለገው ማኅበረሰብ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አስረድተዋል። (“ውዳሴ ላንትተ ይሁን” ቁ. 107)

የሂሳብ ቀመር እና የሐሰት ዜና

የካቶሊክ የሕግ አውጭዎች ቡድን ዋና ዓላማ የምሁራን የፖለቲካ ሥልጣን ሥርዓትን በተጨባጭ የሚቃወሙ ሰዎችን ለማገናኘት በርካታ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮችን ማመቻቸት ቢሆንም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደተናገሩት ማኅበራዊ ሚዲያዎችን የሚጠቀም የምሁራን የፖለቲካ ሥርዓት ሰብዓዊነት የጎደላቸው የሐሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ጥላቻን እና መለያየትን ማስፋፋት እና የሰዎችን ግንኙነት ወደ ቀመር በመቀነስ የባለቤትነት ስሜትን በሐሰት በተለይም በወጣቶች ዘንድ መገለልን እና ብቸኝነት ሊያስከትል እንደሚችል ተገልጿል።

እውነተኛ ግንኙነት እና ምናባዊ ግንኙነት

ምናባዊ ግንኙነትን አላግባብ መጠቀም ማሸነፍ የሚቻለው በእውነተኛ የእርስ በርስ መገናኘት ባሕል እንደሆነ የገለጸው ማኅበሩ፥ መስማማት የሚቻልባቸው የፖለቲካ አቋሞችን ጨምሮ እርስ በርስ የመከባበር እና የመደማመጥ ባሕል በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎችን ተጨባጭ እና እውነተኛ በሆነ መንገድ እንዲገናኙ በማድረግ መልካም ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል ገልጿል።

ሰዎችን ለጋራ ዓላማ ማገናኘት

“የማኅበሩ አውታረ መረብ ሰዎችን መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን አንድ ዓላማ ላይ ለመድረስ እንዲተባበሩ ማስቻል ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለማኅበሩ ባቀረቡት የማበረታቻ ሃሳባቸው፥ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ሕዝቦች በኅብረት ወንጌልን ለሌሎች ለማዳረስ የተመጠሩ መሆናቸን ገልጸው፥ ካቶሊካዊ አውታረ መረቡ ሰብዓዊነት ለጎደላቸው የምሁራን የፖለቲካ ሥልጣን ማኅበረሰቦች መልስ እንደሆነ አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም፥ እውነተኛ ዓለም አቀፍ የካቶሊክ አውታረ መረብ፥ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ዕቃዎች ከሚያደርጋቸው፣ ውሳኔ የማድረግ ወይም እውነተኛ ሕይወትን የመምራት አቅማቸውን ከሚቀንስ የምሁራን የፖለቲካ ሥርዓት አምባገነንነት ይልቅ ሌላ አማራጮችን የሚያሳይ ማኅበር መሆኑን ገልጸዋል።

የዓለም አቀፉ የካቶሊክ ሕግ አውጪዎች ኅብረት ተልዕኮ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዓለም አቀፉ የካቶሊክ ሕግ አውጪዎች ኅብረት የልዑካ ቡድን ያደረጉትን ንግግር ሲደመድሙ እንደተናገሩት፥ የዓለም አቀፉ የካቶሊክ ሕግ አውጪዎች ኅብረት ተልዕኮ የቤተ ክርስቲያንን ማኅበራዊ እና ሥነ-ምግባራዊ ትምህርቶችን ለሕዝብ በማስተዋወቅ ቁርጠኛ የሆነ አዲስ የተማረ ትውልድን እና ታማኝ ካቶሊካዊ መሪዎች ለማቋቋም የሚያደርገውን ጥረት እንዲቀጥል ብርታትን ተመኝተውለታል።

 

28 August 2023, 17:11