ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጎ ፈቃደኞች በፍቅር እና በልግስና አገልግሎት እንዲቀጥሉበት አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ላይ በተከበረው 37ኛው የዓለም ወጣቶች ፌስቲቫል መጨረሻ ከ150 አገራት የተውጣጡ 25 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ላሳዩት አስደናቂ ልግስና፣ አገልግሎት እና እምነት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ላይ ለአንድ ሳምንት ያህል ሲከበር በቆየው 37ኛው የዓለም ወጣቶች ፌስቲቫል ላይ በበጎ ፈቃድ ሲያገለግሉ ከቆዩ 25 ሺህ የ150 አገራት ወጣቶች ጋር እሑድ ሐምሌ 30/2015 ዓ. ም. ስብሰባ አካሂደዋል።

ታላቅ ደስታ የታየበት ክብረ በዓል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከወጣቶቹ ጋር ያደረጉት ስብሰባ የተከፈተው፥ ዘንድሮ በሊዝበን የተዘጋጀውን የዓለም ወጣቶች ፌስቲቫል ታላቅ የደስታ ቀናትን በሚያሳይ የቪዲዮ ምስል እንደነበር ታውቋል። ከዓለም ዙሪያ የመጡ የፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች በዓሉን በማስመልከት በቀረበላቸው ቃለ መጠይቅ በኩል ልምዳቸውን አካፍለዋል።

በቃለ መጠይቁ ላይ አስተያየታቸውን የገለጹት ሦስት ወጣቶች፥ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ራሳቸውን እና እምነታቸውን እንዴት እንደለወጠው ምስክርነታቸው ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተናግረዋል።

በወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ የተሰማራች ጀርመናዊት ወጣት ኪያራ፥ የዓለም ወጣቶች ክብረ በዓል የእግዚአብሔርን ወሰን የለሽ ፍቅር እና ተቀባይነት ተጨባጭ ተሞክሮ እንደሰጣት ተናግራ፥ በማከልም “ክብረ በዓሉ ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ እጅግ በርካታ ወጣቶችን የሚወክል፣ እግዚአብሔር በፍቅሩ የሚፈልገውን እውነተኛ ቤተሰብ፣ የሚያምር ባሕልን እና አማኞችን የምትወክል ቤተ ክርስቲያን አካል መሆኔን የሚያሳይ ነው” ብላለች።

የኮሌጅ ትምህርቱን በቅርቡ የጨረሰው ፖርቱጋላዊ ወጣት ፍራንችስኮ በበኩሉ፥ የፌቲቫሉን ቅድመ ዝግጅት ካለፈው ዓመት ጀምሮ በፈቃደኝነት ሲረዳ መቆየቱን ገልጾ፥ አገልግሎቱ ከባድ ቢሆንም አስደናቂ ውስጣዊ ዕድገትን ያገኘበት፥ ኢየሱስ ክርስቶስን በሌሎች ውስጥ በተለይም በፈገግታቸው አማካይነት ማየት የቻለበት ልምድ እንደነበረ ተናግሯል።

ከፖርቱጋል የመጣው ሌላው ወጣት ፊሊፕ ስለ ዓለም የወጣቶች ፌስቲቫል ያለውን አስተያየት ሲገልጽ፥ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ይበልጥ እንዲቀርብ ያደረገው እና በሚያገኛቸው ሰዎች ሁሉ አማካይነት ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲያውቅ የረዳው መሆኑን ተናግሯል። ወጣት ፊሊፕ በማከልም በጎ ፈቃደኝነት ለዓለም ሰላም ኢየሱስ ክርስቶስን እና ሌሎችን የሚያገለግልበት የሕይወት ዘመን ተልዕኮ መሆኑንም ገልጿል።

ሁላችሁንም አመሰግናለሁ!

 

የሊዝበን ከተማ ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ማኑኤል ክሌሜንት በፖርቱጋል ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ በዓለም የወጣቶች ቀን ላይ በመገኘታቸው ምስጋናቸውን አቅርበው፥ የዓለም ወጣቶች በሙሉ የክብረ በዓሉን የማይረሱ ትዝታዎች እና ልምዶች በልባቸው ይይዛሉ ብለዋል። ብፁዕ ካርዲናል ማኑኤል ክሌሜንት በመቀጠል በዓለም የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ከፍተኛ አገልግሎታቸውን ያበረከቱ በጎ ፈቃደኞችን አመስግነው፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ “የ 2023 ዓ. ም. ትውልድ” በማለት አወድሰዋቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም በበኩላቸው ለወጣቶቹ ባቀረቡት የምስጋና ቃል፥ ከፌስቲቫሉ ትዕይንት በስተጀርባ ለወራት ያህል አገልግሎታቸውን ሲያበረክቱ የቆዩ በርካታ የበጎ አድራጎት ተሳታፊዎችን በማስታወስ፥ ምን ጊዜም ቢሆን የማይረሱ የፌስቲቫሉ ቀናት በስኬት እንዲጠናቀቁ ላደረጉት ከፍተኛ ጥረት አድናቆታቸውን ገልጸውላቸዋል።

አገልግሎት በመስጠት የሚገኝ ደስታ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አንዳንድ በጎ ፈቃደኞች ድካም ቢታይባቸውም ዓይኖቻቸው "ከአገልግሎት በሚገኝ ደስታ" እንደሚበራ በማስተዋል፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሌሎችን ለማገልገል በመጣደፍ ላደረጉት ልግስና ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ሦስቱ ወጣቶች ማለትም ኪያራ፣ ፍራንችስኮስ እና ፊሊፕ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መገናኘታቸውን የመሰከሩበትን ቃል ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ይህ አስደናቂ ግንኙነት ሕይወታቸውን በቅንነት እንዲጓዙት፣ በእምነት እና በአገልግሎት ሕይወት ወደ ፊት እንዲራመዱ እንደረዳቸው፣ "ከኢየሱስ ጋር ያለንን የግል ግንኙነት በየቀኑ ማደስ የክርስትና ሕይወት መሠረት ነው" በማለት የሰጡትን ምስክርነት አስታውሰዋል። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፌስቲቫሉን ያገዙት ወጣት በጎ ፈቃደኞች በየቀኑ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በአዕምሮአቸው ብቻ ሳይሆን በልባቸውም ጭምር እንዲያድሱት ብርታትን ተመኝተው፥ ይህ ግንኙነት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እና እነርሱ በሚረዷቸው በሌሎች ሰዎች ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስን ያገኙበት በመሆኑ ድርብ ነው ብለዋል።

"የፍቅር ማ ዕበል መጋለብ"

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ ሰሜናዊው የሊዝበን ከተማ የባሕር ዳርቻ ከተማ ከሆነችው ናዛሬ ጋር እንደምትዋሰን አስታውሰው አንዳንድ ጊዜ ከውቅያኖሱ የሚነሳው 30 ሜትር ከፍታ ያለው ማዕበል የዓለም ጎብኝዎችን እና ዋናተኞችን እንደሚስብ በመግለጽ፥ በጎ ፍቃደኞቹ ለዓለም ወጣቶች ቀን በዓል ወደ ሊዝበን የመጡ አንድ ሚሊዮን ተኩል ወጣቶችን በእግዚአብሔር ዕርዳታ እና ልግስናን እና ድጋፍ በማድረግ አስተናግደው መሸኘት መቻላቸውን በመግለጽ፥ “የፍቅር እና የልግስና አገልግሎት ማቅረብ እንዲቀጥሉበት አሳስበዋል።

07 August 2023, 17:32