ፈልግ

የሮም ሀገረ ስብከት ዘርዓ ክህነት ተማሪዎች የሮም ሀገረ ስብከት ዘርዓ ክህነት ተማሪዎች  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሮም ሀገረ ስብከት ካኅናትን በሕይወት ጉዞአቸው እንደሚተባበሯቸው ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ነሐሴ 1/2015 ዓ. ም. ለሮም ሀገር ስብከት ካኅናት በሙሉ የጽሑፍ መልዕክት ልከዋል። ካኅናት በሀገረ ስብከቱ ለሚያበረክቱት ሐዋርያዊ አገልግሎት ምስጋናቸውን አቅርበው፥ በደስታም ሆነ በችግር ወቅት ከጎናቸው መሆናቸውን አረጋግጠውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር ከክኅነት ሕይወት እና ከቤተ ክርስቲያን ፍቅር በስተጀርባ ተደብቆ ከሚገኘው መንፈሳዊ ዓለማዊነት፥ ክብርን ለእግዚአብሔር ከመስጠት ይልቅ ለሰው ልጅ ከመስጠት እና የግል ደኅንነትን ብቻ ከማስጠበቅ የሚመጣ መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለካኅናቱ በቅድሚያ ባቀረቡት የምስጋና መልዕክታቸው፥ ውድ እና ብዙዎች በግልጽ ማየት ለማይችሉት የክኅነት አገልግሎት ምስጋናቸውን አቅርበው፥ በደስታ እና በመከራ ወቅት ብቻቸውን እንዳልሆኑ በማረጋገጥ፥ ከክኅነት ሕይወት እና ከቤተ ክርስቲያን ፍቅር በስተጀርባ ተደብቆ ከሚገኝ ዓለማዊነት ራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

ቅዱስነታቸው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን በከፍተኛ ሐዋርያዊ ሥልጣን ለመምራት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክህነት በመንፈሳዊ ዓለማዊነት እንዳይታለል እና በስልጣን እንዳይመካ፥ ይህም አገልግሎቱን ወደ ወደ ዝግነት፣ ወደ ግለኝነት እና ወደ አወቅሁ ባይነት አደጋ እንዳይመራው ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል። ካኅናት ይልቁን ከምዕመናን ወንድሞች እና እህቶች ጋር በመተባበር፥ ራስን ዝቅ በማድረግ ተባብረው በመሥራት እና የሲኖዶሳዊነት ጎዳናን በመከተል ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ በመልዕክታቸው አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለሮም ሀገረ ስብከት ካኅናት ነሐሴ 1/2015 ዓ. ም. የላኩት መልዕክት፥ ሐዋርያዊ ተንከባካቢነትን ያሳዩበት እና አባታዊ ስጋታቸውን የገለጹበት እንደነበር ሲነገር፥ በጥር ወር 2015 ዓ. ም. ይፋ ያደረጉት እና በሀገረ ስብከቱ በርካታ ለውጦችን ያመጣ “የቤተ ክርስቲያናት ኅብረት” የሚለውን አዲስ ሐዋርያዊ ደንብ መሠረት ያደረገ እንደነበር ተመልክቷል።

ለሮም ከተማ ሕዝብ ጠባቂ ቅድስት ማርያም የተሰጠ አደራ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዓለም ወጣቶች ቀን በዓልን ጨምሮ በብዙ ሐዋርያዊ መርሃ ግብሮች መካካል የተዘጋጀው ባለ ሰባ ገጽ መልዕክቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ነሐሴ 5/2023 ዓ. ም. ሮም ከተማ ውስጥ በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ የቀረበ ጸሎት ፍሬ እንደሆነ ተነግሯል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ በተዘጋጀው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ለሀገረ ስብከቱ ካኅናት ባስተላለፉት መልዕክት፥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካኅናትን እንድትጠብቅ እንባቸውንም እንድታብስ እና ደስታን በማጎናጸፍ በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር በመታገዝ ምዕመናንን የሚያገለግሉበትን ኃይን መለመናቸውን ገልጸዋል።

የማይታይ ሐዋርያዊ አገልግሎት

ለሮም ሀገረ ስብከትም ጭምር ጳጳስ የሆኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለካኅናት ጥሪ እና አገልግሎታቸው ትኩረትን በመስጠት በጻፉት መልዕክታቸው፥ አገልግሎቱ በብዙ ውጣውረድ ውስጥ የደስታ እና የድካም ሸክም ያለበት፣ ተስፋ ማድረግ እና ብስጭት የሚታይበት እና በአለመግባባት ውስጥ የሚቀርብ አገልግሎት እንደሆነም ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

በመሆኑም ቅዱስነታችው ለሀገረ ስብከቱ ካኅናት በጻፉት መልዕክት ሰዎች መመልከት በማይችሉት መንገድ ለሚያቀርቡት አገልግሎት ምስጋናቸውን አቅርበው፥ የካኅናት አገልግሎት የሚለካው በሐዋራይዊ ሥራ ስኬት አለመሆኑን ተናግረው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያበረክት ለነበረው አገልግሎት የሚሰጠው ቦታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን አስረድተዋል።

መንፈሳዊ ዓለማዊነት እና በስልጣን መመካት 

“ከካኅናቱ ጋር በኅብረት እንደምጓዝ ይሰማኛል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በደስታቸውም ሆነ በመከራዎቻቸው፣ በዕቅዶቻቸው ሆነ በድካማቸው፣ በምሬታቸው እና በሐዋርያዊ መጽናናታቸው ላይ አንድነትን በመግለጽ ወዳጅነትን በመግለጽ ውጤታማነታቸውን እንደሚጋሩ አረጋግጠውላቸዋል። ክኅነታዊ አገልግሎትን የሚያደናቅፉ የከፉ እንቅፋቶች መንፈሳዊ ዓለማዊነት እና በስልጣን መመካት እንደሆኑ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ እነዚህን ፈተናዎች ባለፉት አሥር የቤተ ክርስቲያን መሪነት ዓመታት ውስጥ ሲያወግዟቸው መቆየታቸውን ገልጸው፥ ከዚህ በፊት የተናገሯቸውን እነዚህን እንቅፋቶች ዛሬም በመልዕክታቸው አንዳንድ ክፍሎች ውስጥ በመድገማቸው ይቅርታን ጠይቀዋል።

ከአንገት በላይ አገልግሎት

ከአንገት በላይ አገልግሎት የሚከሰተው ዕድሜ በሌለው ነገር ሲታለሉ፣ በሥልጣት ጥማት እና በማኅበራዊ ተጽእኖዎች ለመማረክ ሲፈቅዱ እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገልጸዋል። በተጨማሪም ከአንገት በላይ አገልግሎት እና መንፈሳዊ ዓለማዊነት በከንቱ ውዳሴ፣ በማይሻሻሉ አስተምህሮዎች፣ በሥርዓተ አምልኮ ውበቶች፣ ቅርጾች እና መንገዶች ሥር ተሸፍኖ ሊቆይ እንደሚችል፥ አልፎ ተርፎም ለቤተ ክርስቲያን ያለውን ፍቅር በመደበቅ፣ ክብርን ለእግዚአብሔር ከመስጠት ይልቅ ለሰው ልጅ ከመስጠት እና የግል ደህንነትን ብቻ ከማስጠበቅ ሊመጣ እንደሚችል አስረድተዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስን በመመልከት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደተናገሩት፥ ውዳሴን እና ምስጋናን ማቅረብ በእግዚአብሔር ፍቅር የመገረም ዝንባሌዎችን ለማሳደግ እንደሚረዳ፥ ነገር ግን ከምንም በላይ የዕለት መድኃኒት የሆነውን እና ስለ እኛ የተሰቀለውን፣ ራሱን ባዶ በማድረግ እስከ ሞት ድረስ እራሱን ያዋረደውን ኢየሱስ ክርስቶስን በየቀኑ በዓይኖቻችን መመልከት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ነቅቶ መጠበቅ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሮም ሀገረ ስብከት ካኅናት በጻፉት መልዕክት፥ በቤተ ክኅነታዊ ስልጣን የመመካት ፈተናን ነቅቶ መጠብቅ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፥ በቤተ ክህነት ውስጥ በሥልጣን መመካት ሁሉንም ሰው፣ ምእመናን እና ሐዋርያዊ አገልጋዮችንም ሳይቀር ሊነካ እንደሚችል ተናግረው፥ አንድ ሰው የክኅነት አገልግሎቱን በጨዋነት የማይፈጽም ከሆነ፣ ጥሪውን በሥነ ምግባር የማይንከባከብ ከሆነ እና በኅብረት ጉዞ ወቅት እራሱን አጥሮ የሚቀመጥ ከሆነ የክኅነት ዝንባሌውን ሊያጣ እንደሚችል ተናግረዋል።

"ተስፋ መቁረት የለባችሁም!"

“ድክመት እና የአቅም ማነስ ቢታይብንም ተስፋን መቁረት የለብንም” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ አቅሙ ያለን ሁላችን ለበለጠ አገልግሎት በመዘጋጀት የመንፈስ ቅዱስን ዕርዳታ አንዱ ለሌላው መለመን እንደሚያስፈል፣ በግል ሕይወት እና በሐዋርያዊ ተግባር እግዚአብሔርን በማመስገን፣ የወንጌልን መልካም ዜና ለሌሎች በማወጅ ምዕመናንን ማገልገል እንደሚገባ ለሮም ሀገረ ስብከት ካኅናት የማበረታቻ መልዕክታቸውን ልከዋል።

 

08 August 2023, 17:23