ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ "በፖርቱጋል የተከበረው በዓል ወጣቶች ከኢየሱስ ጋር የተገናኙበት ነበር!" አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ነሐሴ 3/2015 ዓ. ም. በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራስ ለተሰበሰቡት ምዕመናን በፖርቱጋል ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት ንግግር አድርገዋል። ከጣሊያን የተለያዩ ሀገረ ስብከቶች የመጡ ምዕመናን ጭምሮ ከልዩልዩ አገራት የመጡ መንፈሳዊ ነጋዲያን የቅዱስነታቸውን ንግግር አድምጠዋል። ቅዱስነታቸው ለምዕመናኑ ባደረጉት ንግግር፥ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን የተከበረው 37 ኛው የዓለም ወጣቶች ቀን ወጣቶች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የተገናኙበት እንደ ነበር ገልጸዋል። ክቡራት ክቡራን አንባቢዎቻችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ በአዳራሹ ለተገኙት ምዕመናን ያደረጉትን ንግግር ሙሉ ትርጉም ከዚህ ቀጥሎ ያገኙታል፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! ባለፉት ቅርብ ቀናት ውስጥ ለ37ኛ ጊዜ በተከበረው የዓለም ወጣቶች ቀን ላይ ለመገኘት ወደ ፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ተጉዤ ነበር። በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝቴ ወቅት ከአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጋር በመገናኘት እንዲሁም ወደ ፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ አጭር መንፈሳዊ ንግደት አድርጌ ተመልሻለሁ።

ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ላይ የተከበረው የዓለም ወጣቶች ቀን ሁልጊዜ አዲስ አድማስን የሚከፍት የእግዚአብሔር ስጦታ እንደሆነ ሁላችንም ተሰምቶናል። መንፈስ ቅዱስ፣ ከሙታን የተነሳው የኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ የዓለም ወጣቶች ልብን እና እርምጃን ወደ ቅዱስ ወንጌል መልሶታል። ይህም ለሰው ልጆች ትልቅ የተስፋ ምንጭ ነው።

ሁላችንም በሚገባ እንደምናውቀው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በማኅበራዊ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ብዙውን ጊዜ መገለልን እና መራራቅን ባስከተለው በዚህ የጤና ቀውስ በተለይ ወጣቶች ተጎድተዋል። በዘንድሮ የዓለም ወጣቶች ቀን እግዚአብሔር ሌላ አቅጣጫን አሳይቶናል። በአህጉራት ሁሉ ወጣቶች በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታላቅ መንፈሳዊ ንግደት እንዲያደርጉ አዲስ ጅምር አሳይቶናል። ከውቅያኖስ ጋር በምትዋሰን በሊዝበን ከተማ የዓለም ወጣቶች ቀን የተከበረው በአጋጣሚ አልነበረም። የሊዝበን ከተማ የታላላቅ አሳሾች ምልክት ናት። የሊዝበን ከተማ የሰው ልጅ ፍላጎት ዘልቆ አዳዲስ የዓለም ክፍሎችን የማግኘት ፍላጎት መነሻ ናት። ይህ ሁሉ ከወጣትነት ጋር ተመሳሳነት አለው። ነገር ግን እንደ ቀላል ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ምክንያቱም ውስጣዊ ፍላጎት እና ምኞት ከሌለ ወጣትነት እንኳን ሳይቀር ተዘግቶ እና ቆሞ ሊቀር ይችላል።

   እናም በዓለም የወጣቶች ቀን ቅዱስ ወንጌል ለወጣቶች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አርአያነትን አቅርቧል። እጅግ በተጨነቀችበት ጊዜ ቅድስት ድንግል ማርያም በራሷ ብቻ ተወስና አልቀረችም። ነገር ግን በእግዚአብሔር ፍቅር ተገፋፍታ ተነስታ በፍጥነት ቸኩላ ሄደች" በሉቃስ 1: 39 ላይ እንደገለጸው፤ ይህ የቅዱስ ወንጌል ጥቅስ በሊዝበን ከተማ ለተከበረው የዓለም ወጣቶች ቀን መሪ ጭብት ነበር። ቅድስት ድንግል ማርያም እራሷን ዝቅ የምታደርግ ትሑት ወጣት ነበረች። ነገር ግን እግዚአብሔር ለጥሪው “እሽ” የምትልበትን እና ራሷን ለደህንነት እቅዱ አገልግሎት እንድትሰጥ ድፍረትን ሰጣት። በዚህ መንገድ ዛሬም በሦስት ሺህኛው ዓመት ኢየሱስ ክርስቶስን በመከተል ረገድ ቅድስት ማርያም አሁንም የወጣቶችን ጉዞ በመምራት ላይ ትገኛለች። ልክ ከመቶ ዓመት በፊት ፖርቱጋል ውስጥ ፋጢማ በተባለች መንደር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሦስት ልጆችን ባነጋገረችባቸው ወቅት፣ ለቤተ ክርስቲያን እና ለዓለም በሙሉ የእምነት እና የተስፋ መልዕክት ሰጥታለች። የነፍስ በሽታ፥ ኩራት፣ ውሸት፣ ጠላትነት እና ዓመፅ ያለበትን ዓለም እግዚአብሔር እንዲፈውሰው ከታማሚ ወጣቶች ጋር በዓለም የወጣቶች ፌስቲቫል ቀናት እመቤታችን ማርያም ወደ ተገለጠችበት ቦታ መንፈሳዊ ንግደት በማድረግ ጸሎቴን ያቀረብኩበት ምክንያት ይህ ነው። በዚህም ራሳችንን፣ አውሮፓን እና መላውን ዓለምን ለእመቤታችን ማርያም ንጹሕ ልብ በማቅረብ አድሰናል።

የዓለም ወጣቶች በዓላቸውን ለማክበር በነበራቸው ከፍተኛ ጉጉት በብዙ ቁጥር ወደ ሊዝበን መጥተዋል። በእያንዳንዱ የዓለም ወጣቶች ቀን እንደሚደረገው፣ ብዙ ወጣቶችም በፖርቱጋል ውስጥ በሚገኙ በርካታ ቁምስናዎች እና ቤተሰቦች ውስጥ ወዳጅነትን እና ወንድማማችነትን አጣጥመዋል። ከዚያም በሊዝበን ከተማ ለፍጻሜው ቀን ተሰብስበዋል። ደማቅ የአቀባበል ሥነ-ሥርዓት ተደርጎ፣ የዋዜማው ጸሎት እና  እና የመጨረሻ ቀን መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ቀርቧል። የዓለም ወጣቶች ቀን የዕረፍት እና አገርን የሚጎበኙት ጊዜ ሳይሆን ወጣቶች በቤተ ክርስቲያን በኩል ከዘለዓለማዊው ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚገናኙበት ነው። አንድ ሰው በእምነት የሚያድግበት እና ብዙዎችም የእግዚአብሔርን ጥሪ የሚያቁበት፡ የጋብቻን ሕይወት፣ የምንኩስና እና የክኅነት ሕይወት ጥሪን የሚገናኙበት ነው። እያንዳንዱ ሰው በጸጋው የእግዚአብሔር ሕዝብ አካል እንዲሆን መጠራቱን ማወቁ ደስታን ያጎናጽፋል። ያለ ብሔር፣ ያል ክልል እና ያለ ቋንቋ ልዩነት፥ እግዚአብሔር የሁላችን አባት እንደሆነ እና ልጆቹንም በሙሉ እንደሚወድ፥ ደስ የሚያሰኝ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በደስታ ለማወጅ የተላከ ነው።

የዓለም ወጣቶች ቀን በሚከበርበት ወቅት በፖርቱጋል ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጌ፥ ውብ የሆነች አገር መዲናን በሰላም የወረሩ ወጣቶች የደስታ ድባብን ለመመልከት አግዞኛል። በተለይ ቁምስናዎችን እና ሀገረ ስብከቶችን በማሰብ፥ ከዓለም ዙሪያ የመጡ ወጣቶችን ተቀብለው ለማስተናገድ ያደረጉት ቅድመ ዝግጅቶች እና ከፍተኛ ጥረቶች፥ አዲስ ኃይል አግኝተው ጉዞአቸውን እንዲቀጥሉ እና በሐዋርያዊነት ስሜት መረቦቻቸውን በድጋሚ እንዲጥሉ ያደረገ በመሆኑ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።

የፖርቹጋል ወጣቶች ዛሬ ወሳኝ ናቸው፣ በዚህም መሠረት አሁን በዓለም ዙሪያ ካሉ አብያተ ክርስቲያናት በተቀበሉት ግፊት በመታገዝ የበለጠ ጠንካሮች ይሆናሉ። ይህ ደግሞ ለመላው ኅብረተሰብ መልካም ይሆናል። ቅዱስ ወንጌል በማቴ. 13፡33 ላይ እንደሚለው፥ ሁሉን እንደሚያቦካ እርሾ ይሆናሉ። ፖርቱጋል እንደ መላው አውሮፓ እና ዓለም ጠንካራ እና አስተማማኝ ተስፋን ይፈልጋል። ይህ ታዲያ ከየትኛውም ወጣት የሚመጣ ሳይሆን በቅዱስ ወንጌል በተነሳሳ ወጣትነት፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ካገኙና እርሱን ከሚከተሉ ወጣቶች ነው። የሰውን ልብ በማደስ ዓለምን የሚያድስ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነውና።

በዩክሬይን እና ሌሎች የዓለማአችን ክፍሎች ውጊያ መኖሩ እሙን ነው። በሌሎች የተወሰኑ ድብቅ አካባቢዎች ጦርነትን የማካሄድ ዕቅድ አለ። ነገር ግን የዓለም ወጣቶች ቀን ጦርነት ቀርቶ ሰላም የሚፈጠርበት ሌላ መንገድ እንዳለ ለሁሉም በገሃድ አሳይቷል። የሁሉም ሕዝቦች ባንዲራዎች አንድ ላይ የሚውለበለቡበት የወንድማማቾች እና የእህቶች ዓለም፣ ያለ ጥላቻ እና ያለ ፍርሃት እንዱ ለሌላው ክፍት በመሆን ያለ መሣሪያ ትጥቅ ያስተላለፉት የዓለም ወጣቶች መልዕክት ግልጽ ነበር። የዓለም ሃያላን ይህን መልዕክት ይሰሙት ይሆን? የወጣቶቹ መልዕክት ለዘመናችን ምሳሌ ነው። ዛሬም ኢየሱስ ክርስቶስ “ጆሮ ያለው ይስማ! ዓይን ያለው ይመልከት!" በማለት እየተናገረ ይገኛል።

ለፖርቱጋል ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት እና ለሌሎች የሲቪል ባለስልጣናት ምስጋናዬን በድጋሚ እገልጻለሁ። ለሊዝበን ፓትርያርክ፣ ለብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት፣ ለዓለም ወጣቶች ቀን አስተባባሪ ጳጳስ እና ለሁሉም ተባባሪዎች እና በጎ ፈቃደኞች፣ ሁላችሁንም እናመሰግናለን! በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እግዚአብሔር የዓለም ወጣቶችን እና የፖርቱጋል ሕዝብን ይባርክ።”

 

 

09 August 2023, 17:00