ፈልግ

በሃዋይ ደሴት በሰደድ እሳት የተጎዳው አካባቢ ገጽታ በሃዋይ ደሴት በሰደድ እሳት የተጎዳው አካባቢ ገጽታ  (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሃዋይ በተነሳው የሰደድ እሳት የተጎዱን በጸሎታቸው አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሰሜን አሜሪካ ለሚገኘው ሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ባስተላለፉት የቴሌግራም መልዕክት፥ በሃዋይ በደረሰው የሰደድ እሳት አደጋ የሰው ሕይወት በመጥፋቱና በንብረት ላይ ውድመት በመድረሱ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸው፥ በአደጋው የተጎዱትን በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው አረጋግጠዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሃዋይ ማዊ ደሴት ላይ በተነሳው የሰደድ እሳት የሰው ሕይወት መጥፋቱን እና ንብረት ላይ ውድመት መድረሱን በተረዱ ጊዜ እጅግ ማዘናቸውን፥ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ በሆኑት በብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በኩል ዓርብ ነሐሴ 5/2015 ዓ. ም. በአሜሪካ የቅድስት መንበር እንደራሴ ለሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክሪስቶፍ ፒየር በላኩት መልዕክት ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በአደጋው ከሚሰቃዩት ጎን መሆናቸውን ተናግረው፥ በተለይም ዘመዶቻቸው ከሞቱባቸው ወይም ከጠፉባቸው ጋር ያላቸውን አጋርነት ገልጸዋል።

በትውልድ ውስጥ ካጋጠሙት አደጋዎች መካከል ትልቁ ነው

በሰደድ እሳቱ በትንሹ 55 ሰዎች መሞታቸውን እና በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ መፈናቀላቸውን የሃዋይ ደሴ አስተዳዳሪ አቶ ጆሽ ግሪን ተናግረው በአደጋው ለተፈላቀሉት አስቸኳይ መጠለያ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ወደ 1,000 የሚጠጉ ሰዎች የደረሱበት እንዳልታወቀ የደሴቲቱ ባለስልጣናት አስታውቀው፥ አክለውም በሃዋይ ደሴት ውስጥ ከደረሱ የተፈጥሮ አደጋዎች መካከል ይህ ትልቁ እንደሆነ ተናግረው፥  የነፍስ አድን ሠራተኞች በሕይወት የተረፉ ሰዎችን በመፈለግ ላይ እንደሚገኙ እና የሟቾች ቁጥርም ሊጨምር እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ፥ ቱሪስቶች እና ጎብኚዎች ደሴቲቱን ለቀው ለመውጣት እየሞከሩ እንዳሉ ሲነገር፥ ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት አቶ ጆ ባይደን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ “ያለንን ሁሉ ለሃዋይ ሕዝብ እናቀርባለን” በማለት ቃል ገብተዋል።

ለተጎጂዎች እና ለነፍስ አድን ሠራተኞች የሚደረግ ጸሎት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አደጋውን በማስመልከት በላኩት የቴሌግራም መልዕክታቸው በእሳት አደጋው የተጎዱትን፣ የሞቱትን፣ የተፈናቀሉትን፣ ፈጣን የዕርዳታ እጆቻቸውን የዘረጉትን እና የነፍስ አድን ሠራተኞችን በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው አረጋግጠዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም፥ ለማዊ ሕዝብ ያላቸውን መንፈሳዊ ቅርበት ገልጸው፥ የእግዚአብሔርን ብርታት፣ ጥንካሬን እና የሰላም በረከቶችን በጸሎታቸው ጠይቀዋል።

 

12 August 2023, 16:52