ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሊዝበን ከሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ጋር ስብሰባ ሲያካሂዱ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሊዝበን ከሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ጋር ስብሰባ ሲያካሂዱ  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በፖርቱጋል-ሊዝበን የተለያዩ ሃይማኖታዊ ስብሰባዎችን ማካሄዳቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ላይ ከሐይማኖት ተቋማት ተውካዮች ጋር የተለያዩ ስብሰባዎችን በማካሄድ ሁሉም ሰው ወንድማማችነትን እንዲያበረታታ እና የወጣቶችን መንፈሳዊ ደህንነት እንዲጠብቅ በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓርብ ሐምሌ 28/2015 ዓ. ም. ከምሳ ሰዓት አስቀድመው በቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ከሦስት የተለያዩ ልኡካን ጋር ተከታታይ ስብሰባዎችን ማካሄዳቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ ጽ/ቤት አስታውቋል።

ቅዱስነታቸው በቅድሚያ፥ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት በሆኑት በብፁዕ ካርዲናል ሚጌል አንጄል አዩሶ ከተመራው የዓለም አቀፍ የውይይት ማዕከል ልዑካን ቡድን ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው ታውቋል።

ቅዱስነታቸው ለልዑካን ቡድኑን ባቀረቡት ሰላምታ፥ የዓለም አቀፍ ማዕከ አባላት ወደ ሊዝበን ላደረጉት ጉብኝት ያላቸውን አድናቆት ገልጸው፥ ስለ ወንድማማችነት እና ስለ ውይይት እሴት በማስመልከት እንዲሁም የተናጠልነት እና ሃይማኖትን የማስለወጥ አደጋ በማስመልከት ለልኡካን ቡድኑ አጭር ንግግር ማድረጋቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ ጽ/ቤት አክሎ አስታውቋል። የንጉሥ አብዱላህ ቢን አብዱላዚዝ ዓለም አቀፍ የሃይማኖቶች እና የባሕል ውይይቶ ማዕከል ወይም “KAICIID” በመባል የሚታወቀው ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ውስጥ መመሥረቱ ይታወቃል።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2007 ዓ. ም. የሳውዲ አረቢያ ንጉሥ አብዱላህ ጋር ያደረጉትን ስብሰባ ተከትሎ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2012 ዓ. ም. በሳውዲ አረቢያ፣ በኦስትሪያ እና በስፔን መከፈቱ ሲታወቅ፥ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ በድረ-ገጹ ቅድስት መንበር የማዕከሉ መሥራች ታዛቢ እንደሆነች ይልጿል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በሊዝበን ከተማ ከሚገኝ የኢስማኢሊ ማኅበረሰብ መሪ ልጅ ከሆኑት ከአቶ ራሂም አጋ ካን ጋር በግል ተወያይተዋል።

የክርስቲያኖች የአንድነት ጥረት እና ለወጣቶች የሚደረግ እንክብካቤ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፖርቱጋል የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮችን እና በሃይማኖቶች የጋራ ውይይት ጥረቶች ላይ የሚሳተፉ የተለያየ እምነት ያላቸውን ቡድኖች ተቀብለው አነጋግረዋል።ቅዱስነታቸው የልኡካን ቡድኑ በወንድማማችነት መንፈስ ለመኖር እና በጋራ ውይይት ላይ ለመሳተፍ ላደረጉት ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው በተጨማሪም፥ የልኡካን ቡድኑ ወጣቶችን እንዲንከባከብ እና በዙሪያቸው ላለው ፈታኝ ዓለም እንዳይጋለጡ ማገዝ እንደሚገባ አደራ ብለው፥ ከወጣቶች ጋር ከነበራቸው የምሳ ግብዣ ሥነ-ሥርዓት ቀደም ብለው ባደረጉት የመጨረሻ ስብሰባ፥ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ዘጋቢ ከሆነው እስራኤላዊው ጋዜጠኛ ሄንሪክ ሳይመርማን ቤናሮክ ጋርም ተገናኝተው ተነጋግረዋል።

 

05 August 2023, 17:44