ፈልግ

ቅዱስነታቸው በፖርቱጋን በበጎ ሥራ ላይ ከተሰማሩ አባላት ጋር ሲወያዩ ቅዱስነታቸው በፖርቱጋን በበጎ ሥራ ላይ ከተሰማሩ አባላት ጋር ሲወያዩ  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ጨለማ በዋጠው ጊዜም ብርሃንን ማብራት!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል እየተከበረ በሚገኝበት ሊዝበን ከተማ ዓርብ ሐምሌ 28/2015 ዓ. ም. ጠዋት በነበረው የኑዛዜ ሥነ-ሥርዓት ላይ፥ የቤተ ክርስቲያን በጎ አድራጎት ወኪሎች የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር በተግባር በመግለጽ ለሚፈጽሙት ተልዕኮ ብርታትን ተመኝተው ለወጣቶች፣ ለአረጋውያን እና ችግር ውስጥ ለወደቁት ሰዎች በሙሉ ያላቸውን ቅርበት ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በፖርቱጋል መዲና ሊዘበን ላይ እየተከበረ ባለው የዓለም ወጣቶች በዓል ላይ የተገኙት በርካታ ወጣቶች  በከተማይቱ ጎዳናዎች ላይ ደስታቸውን እየገለጹ እንደሚገኙ ሲነገር፥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር የሚከናወኑ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓቶችም በበለጠ ድምቀት መቀጠላቸው ተገልጿል። በከተማይቱ ውስጥ በሚገኘው የቫስኮ ዳ ጋማ መናፈሻ ውስጥ ለኑዛዜ ሥነ-ሥርዓት በተዘጋጁ 150 ትናንሽ የእንጨት ቤቶች ፊት ለፊት ሦስት ወጣቶች በጸጥታ ተቀምጠው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሲጠባበቁ ታይተዋል።

ዛፎች ሥር በተዘጋጁት የኑዛዜ መግቢያ ቦታዎች ወጣቶቹን ንስሐ የሚያስገቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚቀመጡበት ነጭ ወንበር መዘጋጀቱ ተመልክቷል። በወንበር ዙሪያ ከተቀመጡት ሦስት ወጣቶች መካከል የ19 ዓመቱ ወጣት ሳሙኤል ከጣሊያን፣ የ33 ዓመቷ ወጣት ዬቪ ከጓቴማላ እና የ21 ዓመቱ ወጣት ፍራንችስኮስ ከስፔን የመጡ መሆናቸው ታውቋል።

በሥፍራው ከሌሎች ዝግጅቶች በተለየ መልኩ፥ በድምጽ ይሁን በምስል የሚተላለፉ ዝግጅቶች ያልነበሩ ሲሆን፥ ለስለስ ባለ ዝቅተኛ ድምጽ ከአየር ላይ ይሰማ የነበረው ብቸኛው መዝሙር፥ “ይህ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ወጣት ነው” የሚል የታወቀው ዝማሬ እንደነበር ታውቋል። በመዝሙር አማካይነት መንፈሳዊ ነጋዲያኑ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሰዓቱ የሚያደርጉትን ወይም በየትኛው ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደሚገኙ ባያውቁም ቅዱስነታቸው በበዓሉ ላይ መገኘታቸውን ብቻ በማስታወስ ሲደሰቱ መታየታቸው ሲነገር፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከመኪናቸው ወርደው ዛፎች ሥር ወደ ተዘጋጁት የኑዛዜ መግቢያ ቦታ ሲደርሱ ታይተዋል።

በኑዛዜ መግቢያ ቦታ ላይ የሚገኝ ካህን

ለመናዘዝ የተዘጋጁ ሦስቱ ወጣቶችን አንድ በአንድ የተቀበሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ወጣቶቹ ሳይፈሩ በተረጋጋ መንፈስ ኃጢአታቸውን እንዲናዘዙ በማድረግ ካዳመጧቸው በኋላ የእግዚአብሔርን ምሕረት በመለመን የኃጢአትን ሥርኤት ሰጥተው ሸኝተዋቸዋል። ሦስቱ ወጣቶች ከኑዛዜ ሥነ-ሥርዓት በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል፥ ሁሉም ስለተሰጣቸው መልካም ዕድል ደስታቸውን ገልጸው፥ ንስሐ በመግባታቸው የተሰማቸውን ስሜት ተናግረዋል።

ከጣሊያን የመጣው ወጣት ሳሙኤል ለቫቲካን የዜና ወኪል በሰጠው አስተያየት፥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለተቀበለው የመቀራረብ እና የሰብዓዊነት ስሜት አጽንኦት ሰጥቷል። ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር ፍርሃት ውስጥ እንደነበር የገለጸው ወጣት ሳሙኤል፥  ቅዱስ አባታችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፈገግታ ተቀብለው እንደ ቤታቸው እንዲሰማቸው ማድረግ መቻላቸውን ገልጿል።

በጨለማ መካከል ብርሃንን ማምጣት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሦስቱን ወጣቶች ኑዛዜ ካስገቡ በኋላ በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት በሚገኝ አንድ አዳራሽ ውስጥ ወደ 100 ከሚሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተወካዮች ጋርም ተገናኝተዋል። በአዳራሹ ውስጥ የተሰሰቡት ሰዎች ዕድሜአቸው ከሁለት ዓመት እስከ የአዛውንት ዕድሜ ያላቸው ሲሆን፣ እነዚህ ሰዎች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ችግር ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን በሚንከባከቡ ተቋማት ውስጥ ዕርዳታን በማግኘት ላይ መሆናቸው ታውቋል።

የሴራፊና የዕርዳታ ማዕከል በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወደ 800 የሚደርሱ ዕርዳታ ጠያቂዎችን ተቀብሎ የምግብ እና የቤት ውስጥ እንክብካቤን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል። ማኅበሩ ወላጆቻቸው የተተውአቸውን ወይም በቸልተኝነት የሚመለከቷቸውን ሕፃናት እና ልጆች ተቀብሎ የሚረዳ ሲሆን፥ አክሬዲታር የተሰኘው ሌላው ማኅበር በምትኩ ልጆች እና ቤተሰቦቻቸው በካንሰር ሕመም ምክንያት የሚመጡ ለውጦችን ለመቋቋም የሚረዳ ማኅበር እንደሆነ ታውቋል። የተለያዩ ድርጅቶችን ወክለው የተገኙ ሦስት አባላት ለስብሰባው ተካፋዮች ባሰሙት ንግግር፥  ድርጅቶቻቸው ዕርዳታውን የሚያቀርቡለት እያንዳንዱ ሰው በህመም፣ በእርጅና እና በቸልተኝነት ምክንያት የሚደርሱ አስከፊ እውነታዎች ለመለወጥ እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

“መናገር የምፈልገው ነገር ሁሉ እዚህ ተጠቅሷል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ዓይኖቼን ከእውነታው ወደ ሌላ አቅጣጫ መመለስ አልፈልግም!” ሲሉ ተናግረዋል። ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ የስብሰባው ተካፋዮች በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግር የተሰማቸውን ስሜት በጭብጨባ ገለጸው፥ ቅዱስነታቸው ጨለማ በነገሠበት ሰዓት የተስፋ ብርሃን ማምጣታቸውን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ለስብሰባው ተካፋዮች የሚያደርጉትን ንግግር በመቀጠል፥ የስብሰባው ተካፋዮችን በማረጋጋት እና በማጽናናት ቤተ ክርስቲያን ለመላው ሕዝብ እንደ ውሃ ምንጭ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት እና ፍቅር እንደምታካፍል አስረድተዋል።

ቤተ ክርስቲያን ይህን የጌታች የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር በየአካባቢው ወደሚገኙ ቁምስናዎች በማድረስ   አንዳንድ ሕመማንን እና አባላትን እንደምትጎበኛቸው ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ወደ ስብሰባው በድንገት ባደረጉት ጉብኝት ለተካፋዩቹ የተስፋ ብርሃንን ማምጣታቸው ተገልጿል።

 

 

 

05 August 2023, 17:33