ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በቅዱስ ቁርባን ውስጥ የሚገኝ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ማኅበር ደናግልን በቫቲካን ሲቀበሉ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በቅዱስ ቁርባን ውስጥ የሚገኝ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ማኅበር ደናግልን በቫቲካን ሲቀበሉ   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ቅዱስ ቁርባን ድሆችን እንድንከባከብ ያሳስባናል ማለታቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የደናግል ማኅበር የተዘጋጀውን መንፈሳዊ ንግደት የተሳተፉ አባላትን በቫቲካን ተቀብለው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ለደናግላኑ ባተላለፉት መልዕክት ለቅዱስ ቁርባን ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው የኢየሱስ ክርስቶስ አካል የሆኑ ድሆችን፣ የተናቁትን እና የተገለሉትን ተቀብለው እንክብካቤን እንዲያደርጉላቸው አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅዱስ ቁርባን ውስጥ የሚገኝ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ማኅበር ደናግልን በቫቲካን ተቀብለው ባደረጉላቸው ንግግር፥ በመንበረ ታቦት ፊት ተንበርክከው በሚያቀርቡት ጸሎት በችግር እና በመከራ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞቻቸውን እና እህቶቻቸውን ለመቀበል እጆቻቸውን ሁልጊዜ ክፍት እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል።

ደናግሉ በቫቲካን ወደሚገኝ ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ መንፈሳዊ ንግደት ያደረጉት፥ በብጹዕ አቡነ ራፋኤሎ ዴሌ ኖኬ እና በሁለት ወጣት ልጃገረዶች፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥቅምት ወር 1923 ዓ. ም. የተመሠረተ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ደናግል ማኅበር መቶኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ እንደሆነ ታውቋል።

ድሆችን የሚያገልግሉ ድሃ አገልጋዮች

የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ደናግል ማኅበርን በማስታወስ ንግግር ያደረጉት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጨባጭ እና አስቸኳይ አገልግሎት እንዲያበረክቱ ያነሳሳቸው መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ገልጸው፥ ጣሊያን ውስጥ ትሪካሪኮ የሚባል ሥፍራ ለብዙ ዓመታት ያለ መሪ ካህን  በመከራ ውስጥ የኖረ፥ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1923 ዓ. ም. አካባቢ በጉንፋን ወረርሽኝ የተጠቃ አካባቢ እንደነበር ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

ብጹዕ አቡነ ዴሌ ኖኬ ወደ ሀገረ ስብከታቸው ካኅናትን እና ደናግልን እንዲጋብዙ  ከር. ሊ. ጳጳሳት ባገኙት ይሁንታ፥ ሐዋርያዊ አገልግሎትን በማበርከት ሊረዳ የሚችል የደናግል ማኅበርን ማቋቋማቸው ይታወሳል።ከአንድ መቶ ዓመት በፊት የተመሠረተው፥ በቅዱስ ቁርባን ውስጥ የሚገኝ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እና ድሆችን የሚያገልግል የድሃ ደናግል ማኅበር ዋና ዓላማ፥ ሰብዓዊ እና መንፈሳዊ አገልግሎቶችን በማበርከት ትንቢታዊ ቤዛነታቸውን ማስተዋወቅ መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገልጸዋል።

ፍቅር፣ አንድነት እና በጎነት

ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ እንደሚነግረን፥ ቅዱስ ቁርባን የፍቅር፣ የአንድነት እና የበጎነት ማሠሪያ እንደሆነ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ፍቅር፥ አንድነት እና በጎነት ለክርስትና ሕይወታችን መሠረት እንደሆኑ ተናግረው፥ ቅዱስ ቁርባን እግዚአብሔርን ለማምለክ እና ለማገልገል፥ በኅብረተሰብ ውስጥ የተፈጠረውን ቁስል ለመጠገን የሚረዳ ኃይል እንደሆነ አስረድተዋል።

በዓለማችን ውስጥ በርካታ ችግሮች በሚከሰቱበት በዚህ ወቅት በቅዱስ ቁርባን ፊት ተንበርክኮ ለብዙ ሰዓት መጸለይ ዋጋ የሌለው ሊመስል ቢችልም፥ ነገር ግን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ደናግል ማኅበር አባላት በጸሎት ያሳለፉት ጊዜ ብዙም ሳይቆይ መልካም ፍሬን ማፍራቱን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገልጸው፥ ይህም ቁሳዊ፣ ባህላዊ እና የመንፈሳዊ ቤዛነት አገልግሎቶችን ከጠበቁት በላይ እንዲበረክቱ ብርታት እንደሆናቸው አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ደናግል ድኅነትን እና ኢ-ፍታሃዊነትን በመዋጋት ፍቅር እንዲስፋፋ ማድረጉን ተናግረዋል።

ለድሆች መልካም አቀባበል ማድረግ

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም ለመንፈሳዊ ነጋዲያን እህቶች ባስተላለፉት መልዕክት፥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ምሥክርነት በተጨማሪ የቀደሙ የማኅበሩ እህቶች በተግባር ያሳዩትን ምሳሌን በመከተል፥ ወደ ቅዱስ ቁርባን ፊት በጸሎት በመቅረብ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብስትን ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ እንደሰጣቸው፥ እራሱንም ዝቅ አድርጎ እግራቸውን እንዳጠበ በማስታወስ፥ ወንድሞችን እና እህቶችን ማገልገል እንዲማሩ በመጠየቅ፥ ቅዱስ ቁርባን መከራ ውስጥ የሚገኙትን በተለይም ድሆችን፣ የተናቁት እና ከማኅበረሰቡ መካከል የተገለሉት የኢየሱስ ክርስቶስ የአካል ክፍሎችን እንዲንከባከቡ የሚጋብዝ መሆኑን አስረድተዋል።

የእህቶች ማኅበር መሥራች የሆኑት ብጹዕ አቡነ ዴሌ ኖኬ፥ ደናግሉ “የእግዚአብሔር ጽዋ” እንዲሆኑ በማለት ያቀረቡትን ጥሪን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ይህም የተልዕኮአቸው ውብ ገጽታ እንደሆነ ገልጸው፥ ደናግሉ ከራሳቸው ወጥተው በቀረበላቸው ጥሪ መሠረት ሕይወታቸውን ለሌሎች በስጦታነት እንዲያቀርቡ እና ለሰዎች መልካም አቀባበል በማድረግ በልባቸውም በመያዝ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ለማቅረብ ዝግጁዎች እንዲሆኑ አደራ ብለዋል።

26 August 2023, 16:47