ፈልግ

ለዩክሬይን የተደረገ የሰላም ጸሎት ለዩክሬይን የተደረገ የሰላም ጸሎት  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሰላም መማጸኛ ጸሎታቸውን ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በነሐሴ 09/2015 ዓ. ም በተከበረው የፍልሰታ ማርያም ዓመታዊ በዓል ዕለት የሰላም መማጸኛ ጸሎታቸውን ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም አቀረቡ። ባሁኑ ወቅት ጦርነት የሚካሄድባት ዩክሬንን ጨምሮ አመጽ እና አለመረጋጋት በሚታይባቸው የዓለም ክፍሎች በሙሉ ሰላም እንዲወርድ በማለት የሰላም ጥሪያቸውን በማደስ መላው ምዕመናን ተስፋቸውን ሳይቆርጡ በጸሎት እንዲተጉ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የፍልሰታ ማርያም ዓመታዊ በዓል በተከበረበት ነሐሴ 09/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባሰሙት ንግግር፥ ዩክሬንን ጨምሮ ጦርነት፣ አመጽ እና አለመረጋጋት በሚታይባቸው የዓለም ክፍሎች በሙሉ ሰላም እንዲወርድ የሰላም ተማጽኖአችንን ወደ ሰማይ ላረገች እመቤታችን ቅድስት ማርያም ዘንድ እናቀርባለን ብለዋል። 

በዓለም ላይ በጦርነት የተጠቁ ብዙ አካባቢዎች መናራቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ የጦር መሣሪያ መርዝ የውይይት ጥረቶችን እያደናቀፈው እንደሚገኝ ተናግረው፥ በአንዳንድ ቦታዎች ኃይልን የመጠቀም መብት በሰላም የመኖር መብት ላይ የበላይነትን እያገኘ መምጣቱንም በምሬት ተናግረዋል። ቢሆንም ተስፋ አንቆርጥም ብለው፥ ጸሎታችንን የሚሰማ የታሪክ ሁሉ ጌታ እርሱ እግዚአብሔር ስለሆነ ተስፋ ማድረግን እንቀጥላለን ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በመላው ጣሊያን የበጋ ዕረፍት ቀን በሆነው ነሐሴ 09/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ለተሰበቡት በመቶዎች ለሚቆጠሩ ምዕመናን ሰላምታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፥ በሰሜን ጣሊያን ከቬሮና ሀገረ ስብከት ለመጡ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ማኅበር ወጣቶችም ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት በሙሉ መልካም በዓልን ተመኝተው፥ እንደተለመደው ምዕመናኑ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው በመጠየቅ ንግግራቸውን አጠቃለዋል።

 

17 August 2023, 17:01