ፈልግ

ምዕመናን ዩክሬይን ውስጥ ለሰላም ሲጸልዩ ምዕመናን ዩክሬይን ውስጥ ለሰላም ሲጸልዩ  (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በዩክሬን ቅርብ ጊዜ ውስጥ ሰላም እንዲመጣ በማለት የጋራ ጸሎት አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት ለምዕመናን ባደረጉት ንግግር ማጠቃለያ ላይ በጦርነት ለሚሰቃይ የዩክሬይን ሕዝብ ሰላም እንዲወርድ በማለት የአውሮፓ አኅጉር ባልደረባ ለሆነች የቅዱስ መስቀል ወዳጅ የሆነች የቅድስት ተሬዛ ቤነዴታ ተማጽኖን ለምነዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም፥ "የእርሷ ምስክርነት ማንኛውም ዓይነት ጥቃት እና መድልዎ ለሚፈጸምባቸው ሰዎች ብርታት ይሆናቸዋል” ብለዋል። በፖላንድ ውስጥ በሚገኙ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደሶች መንፈሳዊ ንግደት በማድረግ ላይ የሚገኙ የፖላንድ ምዕመናንም ለሰላም ጸሎት እንዲያቀርቡ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበው፥ የአማዞን ደኖችን በማስመልከት በብራዚል በሚካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለተገኙት ሰላምታቸውን ልከዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአውሮጳ አኅጉር ረዳት እና የቅዱስ መስቀል ወዳጅ ለሆነችው ቅድስት ተሬዛ ቤነዴታ ባቀረቡት የመማጸኛ ጸሎት፥ ለዩክሬይን ሕዝብ ሰላምን እንታማልድ አደራ ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ለተሰበሰቡት ታዳሚዎች ባስተላለፉት መልዕክት፥ ቤተ ክርስትያን የናዚዎች ግድያ ሰለባ የሆነችውን ቀርሜሎሳዊት መነኩሴ ኤዲት ስታይን ነሐሴ 3 የምታስታውስ መሆኑን ገልጸው፥ "የእርሷ ምስክርነት በሕዝቦች መካከል የወንድማማችነት ውይይቶችን በማድረግ ማንኛውም ዓይነት አመጽ እና መድልዎ ለመዋጋት ይረዳል” ብለዋል።

የኤዲት እስታይን ምልጃ

የፍልስፍና ሊቅ እና አይሁዳዊ መሠረት ያላት ኤዲት እስታይን የክርስትና እምነትን በወጣትነ ዕድሜ ከተቀበለች በኋላ ወደ ቀርሜሎሳውያን ገዳም ገብታ ከእህቷ ጋር ሆላንድ ውስጥ በሚገኘው ኤክት ገዳም እያለች በናዚ ወታደሮች ተይዛ ጀርመን ውስጥ ወደሚገኝ ኦሽዊትዝ ማጎሪያ ካምፕ መወሰዷ ይታወሳል። ኤዲት እስታይን እስር ቤት ውስጥ እያለች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ነሐሴ 9/1942 ዓ. ም. ሕይወቷ አልፏል።

ከሃምሳ ዓመት በሁአላ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የአውሮፓ አኅጉር ባልደረባ በማለት ያወጁ ሲሆን፥ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባሰሙት ንግግር፥ "በጥንታዊው የአውሮፓ አኅጉር ውስጥ እርስ በርስ የመከባበር፣ የመቻቻል እና አንዱ ሌላውን ተቀብሎ የማስተናገድ እውነተኛ የወንድማማችነት ማኅበረሰብን መመሥረት ያስፈልጋ" በማለት መናገራቸው ይታወሳል። ዛሬም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእርሷ ላይ እምነትን በመጣል የውይይት እና የወንድማማችነት መንገድ የጠፋ በሚመስለው አውሮፓ ውስጥ ሰላም እንዲገኝ፣ የአውሮፓ አደራ ለንጽሕተ ልበ ማርያም በመስጠት ዕርዳታዋን ጠይቀዋል።

በዋጋ የማይተመን የሰላም ስጦታ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ውስጥ ለተገኙት የፖላንድ ምዕመናን ሰላምታቸውን ባቀረቡበት ወቅት የዩክሬይን ሕዝብ በማስታወስ፥ ምዕመናኑ ዩክሬይንን በጸሎታቸው እንዲያስታውሷት አደራ ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም በፖላንድ ውስጥ ወደሚገኝ የያስና ጎራ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ በመንፈሳዊ ንግደት በማድረግ ላይ የሚገኙ የፖላንድ ምዕመናንም ለዩክሬይን ሰላም እንዲጸልዩ በማለት ጥሪያቸውን በድጋሚ አቅርበዋል።

ፍጥረትን ለመንከባከብ ያለውን ቁርጠኝነት ማደስ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም በብራዚል በሌም ዶ ፓራ ከተማ ውስጥ ከነሐሴ 2/2015 ዓ. ም. ጀምሮ በመካሄድ ላይ ባለው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለተገኙት በሙሉ ሰላምታቸውን ልከዋል።የአማዞን ደኖች ደኅንነትን ለመጠበቅ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1995 ዓ. ም. የተመሠረተው የአገራት አንድነት ደኑ የሚያዋስናቸው የደቡብ አሜሪካ አገራትን፥ ቦሊቪያን፣ ብራዚልን፣ ኮሎምቢያን፣ ኤኳዶርን፣ ጉያናን፣ ፔሩን፣ ሱሪናምን እና ቨነዙዌላን እንደሚያዋስን ይታወቃል።  

 

09 August 2023, 17:16