ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ጆርጆ ማሬንጎ በሞንጎሊያ መዲና ኡላምባታር ከሚገኙ ምዕመናን ጋር ሆነው ብጹዕ ካርዲናል ጆርጆ ማሬንጎ በሞንጎሊያ መዲና ኡላምባታር ከሚገኙ ምዕመናን ጋር ሆነው 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሞንጎሊያ የሚያደርጉት ጉብኝት የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንደሚገልጽ ተነገረ

በሞንጎሊያ መዲና ኡላምባታር የጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ እና የኮንሶላታ ሚሲዮናዊ ማኅበር አባል የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ጆርጆ ማሬንጎ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከነሐሴ 25-29/2015 ዓ. ም. በሞንጎሊያ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የቤተ ክርስቲያን አንድነት ከመግለጽ በተጨማሪ በቅድስት መንበር እና በሞንጎሊያ መንግሥት መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት ለማጠናከር የሚረዳ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከነሐሴ 25-29/2015 ዓ. ም. በምሥራቅ እስያ አገር ሞንጎሊያ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት "ልዩ ጸጋ እና ታላቅ ክብር ነው” በማለት ለቫቲካን የዜና አገልግሎት የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ጆርጆ ማሬንጎ፥ “የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ የሆኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በመካከላችን ማግኘት ትልቅ ስጦታ ነው” ሲሉ ገልጸው፥ “ሞንጎሊያ የካቶሊክ እምነት የተቀበለችበት ሠላሳኛ ዓመት ማክበር ብቻ ሳይሆን ከኮሚኒስት ሥርዓት ውድቀት በኋላ አንድ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አገሪቱን ለመጀመሪያ ጊዜ መጎብኘታቸው ትልቅ ታሪካዊ ዋጋ ያለው ነው” በማለት ተናግዋል።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ኢኖሴንቶስ አራተኛ፥ ከስምንት መቶ ዓመታት በፊት ጆቫኒ ዳ ፒያን ዴል ካርፒን የሰላም መልዕክተኛ አድርገው ወደ ሞጎሊያውያ መላካቸው ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ጆርጆ ማሬንጎ፥ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እና በሞንጎሊያ ንጉሣዊ ቤተሰብ መካከል የመጀመሪያ ግንኙነት የተካሄደው በአሥራ ሦስተኛው ክፍለ-ዘመን እንደነበር አስታውሰዋል። 

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሞንጎሊያ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የአገሪቱ ካቶሊክ ምዕመናን በቤተ ክርስቲያን ልብ ውስጥ መሆናቸው በእውነት እንዲሰማቸው ይረዳል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ጆርጆ፥ “በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሩቅ ብንሆንም የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ለቤተ ክርስቲያን ቅርብ እንድንሆን ያደርገናል” ብለው፥ በማከልም “በቅድስት መንበር እና በሞንጎሊያ መንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር አስፈላጊ ይሆናል” ብለዋል።

የአገሪቱ ካቶሊካዊ ምዕመናን የቅዱስነታቸውን ሐዋርያዊ ጉብኝት በታላቅ ጉጉት፣ በመንፈሳዊነት ስሜት እና በጸሎት በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ጆርጆ ማሬንጎ፥ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት አስፈላጊ እና ከተወሰነ ጊዜ በፊት በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በአንዲት ክርስቲያን ባልሆነች ሴት ቆሻሻ ውስጥ የተገኘውን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሐውልት እንደሚጎበኙ ገልጸው፥ በርካታ ካቶሊካውያን ወደ ሥፍራው መንፈሳዊ ንግደት በማድረግ በመቁጠሪያ ጸሎት በረከትን መለመናቸውን ገልጸዋል።

ሦስት ሚሊዮን ተኩል ያህል ነዋሪዎች ባሉባት እና ስፋቷም ከአንድ ሚሊዮን ተኩል ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ በሚሆናት ሞንጎሊያ ውስጥ ወደ 1,500 የተጠመቁ ም ዕመናን በስምንት ቁምስናዎች እና በአንድ ጸሎት ቤት ለጸሎት እንደሚሰበሰቡ፣ ከእነዚህም መካከል አምስቱ ቁምስናዎች በዋና ከተማው ውስጥ ሲገኙ የተቀሩት ቁምስናዎች ሩቅ በሆኑ አካባቢዎች እንደሚገኙ ታውቋል።

በሞንጎሊያ የምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በአገሪቱ ከምታበረክታቸው አገልግሎቶች መካከል ሰባ ከመቶ የሚሆነው በሁለንተናዊ የሰው ልጅ ዕድገት ላይ እንደሆነ እና በዚህም የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶችን በማበርከት አቅመ ደካማ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በመንከባከብ ላይ እንደምትገኝ ታውቋል።

በሞንጎሊያ የምዕመናን ክርስቲያናዊ ሕይወት ለማሳደግ ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፥ እነዚህን አገልግሎቶች ለማዳረስ ወደ ሰባ የሚጠጉ ሚስዮናውያን እንደሚገኙ እና ከእነዚህ መካከል ሃያ አምስት ካህናት፣ ሠላሳ መነኮሳት እና ብዛት ያለው የምእመናን ቡድን መኖሩን ብጹዕ ካርዲናል ጆርጆ ማሬንጎ ገልጸዋል።

ቅዱስ ወንጌልን በተግባር መኖር የመጀመሪያው እና ዋናው ጥሪ መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ጆርጆ ማሬንጎ፥ የእያንዳንዱ ማኅበረሰብ ትልቁ ፈተና ደቀ መዝሙር እና ሚስዮናዊ መሆን ነው” ብለዋል። ሌላው ተግዳሮት የመሠረተ ልማት አለመጠናከር እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ጆርጆ፥ በተወሰነ የባህል አውድ ውስጥ እምነትን ማስረጽ እና ማሳደግ ረጅም ጊዜን የሚፈጅ መሆኑን ገልጸው፥ የአገር ተወላጅ የሆኑ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራንን፣ ካኅናትን እና ሚሲዮናውያንን ማሰልጠን ሌላው ፈተና ነው” ብለዋል።

አብዛኛው ሕዝብ የቡዳ እምነት የሚከተልባት እንዲሁም ትንሽ የማይባል የሙስሊም ቁጥር ባለባት ሞንጎሊያ ውስጥ በሃይማኖቶች መካከል ውይይት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ የተናገሩት ብጹ ዕ ካርዲናል ጆርጆ፥ ቤተ ክርስቲያን ከሌሎች ሃይማኖቶች፣ ሃይማኖታዊ ወጎች እና ባሕሎች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት በማድረግ ላይ እንደምትገኝ አስረድተው፥ በሃይማኖት መሪዎች መካከል በየዓመቱ ይካሄድ የነበረው ስብሰባ አሁን በየሁለት ወሩ እንደሚዘጋጅ ገልጸዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተጠናከረ የመጣው ግንኙነት እና በመዲናዋ ኡላንባታር ላይ የሚካሄዱት ስብሰባዎች እርስ በርስ ለመተዋወቅ እና የሕይወት አካሄድን ለመለዋወጥ ማገዛቸውን አስረድተዋል።

 

26 August 2023, 16:57