ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አቡነ ሉዊጂ ቤታዚን በቫቲካን ሲቀበሏቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አቡነ ሉዊጂ ቤታዚን በቫቲካን ሲቀበሏቸው 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በአቡነ ሉዊጂ ቤታዚ ዕረፍት የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ተሳታፊዎች መካከል አንዱ በሆኑት በብፁዕ አቡነ ሉዊጂ ቤታዚ ዕረፍት የተሰማቸውን ሐዘን ማክሰኞ ሐምሌ 11/2015 ዓ. ም. በላኩት መልዕክት ገልጸዋል። ቅዳሜ ሐምሌ 8/2015 ዓ. ም. ያረፉት ብፁዕ አቡነ ሉዊጂ ቤታዚ አመጽን በመቃወም ለሰው ልጆች በሙሉ ፍትሕን እና ሰላምን ለማስፈን ደከመኝ ሳይሉ የጣሩ የቤተ ክርስቲያን አባት እንደነበሩ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለአቡነ ሉዊጂ ቤተሰቦች እና ወዳጆቻቸው በሙሉ በላኩት የሐዘን መግለጫ በጸሎት እንደሚተባበሯቸው ገልጸው፥ የቅድስት መንበር ጸሐፊ በሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በኩል በላኩት የቴሌግራም መልዕክት፥ አቡነ ሉዊጂ ቤታዚ በረጅም እና ፍሬያማ የአገልግሎት ዓመታት ወቅት የተወደዱ፣ የተደነቁ እና የተመሰገኑ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

አቡነ ሉዊጂ ቤታዚን እንደሚያስታውሷቸው የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ለድሆች ቅርብ፣ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በተለይ ፍትሕን እና ሰላምን ለማስፈን የጣሩ ታላቅ የወንጌል ወዳጅ እንደነበሩ አስታውሰው፥ ለጣሊያን ሕዝብ የፖለቲካ ሕይወት የሃሳብ ምንጭ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

በሰሜን ጣሊያ ፒዬድሞንት ክፍለ ሀገር በምትገኝ ኢቭሪያ ከተማ የተወለውዱት አቡነ ሉዊጂ ቤታዚ፥ “ፓክስ ክሪስቲ” ለተባለ ዓለም አቀፍ የሰላም ንቅናቄን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1978 እስከ 1985 ዓ. ም. ድረስ በፕሬዝዳንትነት አገልግለዋል። በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ሕይወት በመመራት ከሁከት ይልቅ ሰላምን በማራመድ በሰብዓዊ መብቶች ላይ ያተኮሩ መጽሐፍትን በመጻፍ፣ ሃብትን እና ጥቅማ ጥቅሞችን በመተው በቅዱስ ወንጌል የተመራ የድህነት ሕይወት የኖሩ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ እንደነበሩ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

አቡነ ሉዊጂ ቤታዚ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና በጣሊያን የፖለቲካ መድረክ ውይይትን በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ፥ ከሌሎች ሁለት ጳጳሳት ጋር በቀይ ብርጌድ አሸባሪዎች ታግተው የነበሩ የቀድሞው የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር አልዶ ሞሮን ለማስለቀቅ ጥረት ማድረጋቸውም ይታወሳል።

የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ደፋር ምስክር

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሐዘን መግለጫ መልዕክታቸው፥ አቡነ ሉዊጂ ቤታዚ ለሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ለሰጡት ደፋር ምሥክርነት እና ታማኝ አገልግሎት እግዚአብሔርን አመስግነው፥ በመልዕክታቸው መጨረሻ አቡነ ሉዊጂ ቤታዚን እንደ ረዳት ጳጳስነት ተቀብለው በክብር ለታዘዟቸው የቦሎኛ ሀገረ ስብከት ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ በሙሉ ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ሰጥተዋል።

19 July 2023, 10:24